ችግር ለመፍጠር የሚንቀሳቀስ ማንኛውንም አካል አንታገስም – የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር

“…በፈተናው ዙሪያ ችግር ለመፍጠር የሚንቀሳቀስ ማንኛውንም አካል አንታገስም” – የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አበረ አዳሙ

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አበረ አዳሙ የካቲት 29/2013 በሚጀምረው የ12ኛ ክፍል ፈተና ዙሪያ በክልሉ ችግር ለመፍጠር የሚንቀሳቀስ ማንኛውንም አካል አንታገስም አሉ።

ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ይህን ያሉት ዛሬ በባህርዳር በነበረ የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ላይ ትኩረት ያደረገ የምክክር መድረክ ላይ ነው።

ኮሚሽነሩ የክልሉን ሰላም የማይፈልጉ አካላት ፈተናውን እንዳያደናቅፉ በቅንጅትና በልዩ ትኩረት ይሰራልም ብለዋል።

በተጨማሪ ተማሪዎች የረጅም አመት ውጤታቸውን የሚያዩበት ጊዜ በመሆኑ የፀጥታ መዋቅሩ በልዩ ትኩረት ይሰራል ሲሉ ተናግረዋል።

በተለይም የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ልዩ የፀጥታ ሀይል ስምሪት ይደረጋል ያሉ ሲሆን የፀጥታ ተቋሙ ችግሮች ሲፈጠሩ ፈጣን ውሳኔዎችን መስጠት ይገባል ብለዋል፡፡

ፈተናውን የሚያውኩ ማንኛውም መረጃ ፈጥኖ ለፖሊስ አካላት መስጠት ከህብረተሰቡ የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በዛሬው የምክክር መድረክ ተማሪዎች በማህበራዊ ሚዲያ የሚናፈሱና ትክክለኛ ምንጫቸው ከማይታወቁ መረጃዎች ራሳቸውን በመጠበቅ የተዘጋጁበትን ፈተና እንዲፈተኑ ጥሪ ቀርቧል።

በ2012 ዓ.ም በኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ምክንያት ሳይሰጥ የቀረው የ2012 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ሊሰጥ 10 ቀናት ብቻ ቀርቶታል።