መንግሥት የዜጎችን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ማንኛውንም ተግባር እንደማይታገስ ገለጸ

በትግራይ ክልል እየተካሄደ ስላለው የምርመራ ሂደት በተመለከተ መንግሥት መግለጫ ሰጥቷል፡፡ትህነግ በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ በፈጸመው ጥቃት ምክንያት መንግሥት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማዕቀፍ ውስጥ ሕግ የማስከበር እርምጃ መውስዱን መግለጫው ጠቅሷል፡፡የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ የፌዴራል ፖሊስ፣ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና የሚመለከታቸው አካላት በትግራይ ክልል ተፈጸሙ ስለተባሉ ወንጀሎች እና የሕግ ጥሰቶችን የሚመለከቱ ምርመራዎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል ብሏል፡፡
በምርመራ ሂደቱ የተገኙ ውጤቶችን ተቋማቱ ለሕዝብ ይፋ አድርገዋል፡፡ በተጨማሪም በእነዚህ የምርመራ ግኝቶች መሠረት ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ አስፈላጊ እርምጃዎች ተወስደዋል ብሏል፡፡በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ ለተፈፀመው ጥቃት ተጠያቂ በመሆናቸው እና በማይካድራ በተፈፀመው ጭፍጨፋ የተጠረጠሩ በሚቀጥሉት ሳምንታት አግባብ ባላቸው ፍርድ ቤቶች ክስ እንደሚመሰረትባቸው መግለጫው ጠቅሷል፡፡

መንግሥት የሕግ የበላይነትን እና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ባለው ቁርጠኝነት የሚመለከታቸው ተቋማት እውነታዎችን ለማጣራት እና ወንጀሎች መከሰታቸውን በማረጋገጥ ተጠያቂነት ለማስፈን ምርመራዎች መከናወናቸውን ይቀጥላሉ ብሏል መግለጫው፡፡ወሲባዊ ጥቃት ጨምሮ የተለያዩ አካላት ሪፖርት ካቀረቡባቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ቀደም ብሎ ምርመራ እያካሄደ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ እነዚህን ምርመራዎች የሚያካሂደው በብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ተቋማትና አሠራሮች ቅድሚያ በሚሰጣቸው መርህ መሠረት ከዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ነው ብሏል፡፡በተጨማሪም የፌዴራል ፖሊስና ዐቃቤ ሕግ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ አስፈላጊውን ምርመራ እያደረጉ እንደሆነም ገልጿል፡፡ እነዚህ ተቋማት ያገኙትን ውጤት ለሕዝብ ማሳወቃቸውን የሚቀጥሉ ሲሆን በእነዚህ ግኝቶች ላይ በመመስረት የኢትዮጵያ መንግሥት በሕጉ መሠረት ተገቢውን እርምጃ ይወስዳል ብሏል፡፡በግጭቶች ውስጥ አሳዛኝ ክስተቶች የሚፈጸሙ ቢሆንም መንግሥት በምንም መልኩ የዜጎችን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ማንኛውንም ተግባር እንደማይታገስም መግለጹን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ አስታውቋል፡፡