“ፍልሰታ፣ እኛም ማየት አለብን” በቀሲስ አስተርአየ ጽጌ

ክቡር ጠቅላይ ምኒስቴር ዓቢይ አህመድ “ከኦርቶዶክስ ውጭ ኢትዮጵያ የለችም” እንዳሉት፤ ቀሲስ አስተርአየም በኢትዮጵያ ውስጥ ኦርቶዶክስን፤ በኦርቶዶክስ ውስጥ ኢትዮጵያን ሳያሳዩ የጻፏቸው ጦማሮች የለም። በዚህ ጥረታቸው ኢትዮጵያ እንዳትረሳ ሲያደርጉ። ቤተ ክርስቲያናቸው ለኢትዮጵያ ያደረገችውን ጥረት ለማሳየት ሞ ክረዋል። ከጻፏቸው ብዙ ጦማሮች አንዱ “እኛም ማየት አለብን” በሚል ርእስ ከዛሬ ሰባት ዓመት በፊት ነሀሴ 2003 ዓ.ም. ያቀረቧት ናት። በፍልሰታ ጾም የምትዘራው ትንሿ የጤፍ ፍሬ ተዘርታ ፈርሳ በስብሳ በቅላ አፍርታ እንደገና በዝታ ታጭዳ ተወቅታ በውስጧ የተሸከመችውን ሕይወት ሁሉ ውጣ ውረድ አልፋ፤ እሷነቷን ለሚቀጥለው ዘሯ ለማቀበል በምታልፍበት አንጻር፥ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የፍልሰታ ሰሞን ከናቶቻችን ማሕጸን ከወጣንባት ደቂቃ ጀምሮ እንደ ጤፏ ቅንጣት እየወደቅን እየተነሳን አድገን፥ እኛነታችንን ለሚቀጥለው ዘሮቻችን ለማቀበል በዚህ ምድር ላይ መዘራታችንን የምንመረምርበት የጥሞና ወቅታችን ናት::

ሐዋርያት “እኛም ማየት አለብን” ብለው የፍልሰታን ጾም እንደጾሙ እኛም መንፈሳችን ከሥጋዊ ስሜትና ፍላጎት ገተን፤ ያጣነውን እኛነታችንን ፈልገን ለማግኘት ይህች የፍልሰታ ሰሞን የምንጥርባት ወቅት ናት:: የጥንት ኢትዮጵያዊያን በጤፏ ቅንጣት ምሳሌነት በፍልሰታ ሱባዔ ለህጻናቱ የሚስተምሩትን የሕይወት ምሥጢር በዓለም ዙሪያ የተበተነው ሁሉ ወጣት ረስቶ Fast Food Nation ሆኖ እንዳይቀር፥ እንደ ጤፏ ቅንጣት የመበተኑ፥ የመዘራቱ፥ የመታጨዱና የመወቃቱ መከር አልፎ የመሰብሰቡ ወቅት አሁን እንደሆነ የማስተማርና የማስጨበጥ አቅሙና ችሎታው የሚፈቅደለት ኢትዮጵያዊ ሁሉ ኀላፊነት አለበት:: በማለት ከሰባት አመት በፊት ያቀረቧትን ጦማር ወቅቱ ስለሆነ አቀረብንላችሁ።

እኛም ማየት አለብን

የመንፈስና የሞራል መምሕርነታቸውንና ምሳሌነታቸውን እየገለጹ በኅብረተ ሰቡ መካከል የሚኖሩ አያቶችና ቅድመ አያቶች ልጆቻቸውንና የልጅ ልጆቻቸውን ተሰናብተው ጥራጥሬ ስንቃቸውን፥ የውሐ ቅላቸውን፥ አንጥፈው የሚተኙበትን ምንጣፍ ይዘው ወደ ገዳማቱና አድባራቱ መቃብር ቤት የሚሄዱባት ወቅት ናት:: ከትዳር ርቀው ዓለምን ንቀው የመነኮሱ ደግሞ ለሱባዔ ከያቅጣጫው የሚመጡትን ምእመናን ለመቀበል፥ ለመርዳትና መመሪያ ለመስጠት የሚዘጋጁባት ወቅት ናት:: መርዳትም ከሱባዔ ያልተለየ የተቀደሰ አገልግሎት ነውና፥ ወሩ አዝርእት በተለይም ጤፍ የሚዘራበት ስለሆነ ወቅቱን በመሻማት በእርሻ በጉልጓሎና በጤፍ ዘር ላይ ያሉትን ምግብ በማብሰልና ልጅ በመንከባከብ ለመርዳት ወደ መቃብር ቤት የማይሄዱ አሉ:: ይሁን እንጂ ማታ ሁሉም ከተሰማራበት ክትት ሲል፥ ወቅታዊቷን ጤፍ በምሳሌ እየጠቀሱ በሰባዊ ተፈጥሮ የሚደርሰውን እያስተማሩ ሱባዔዋን በመንደራቸው ይፈጽማሉ:: ጠቢቡ ሰሎሞን “ለሁሉም ጊዜ አለው” እንዳለው፥ ደቂቀ አዳም እንደጤፏ ዘር ተዘርተን ተበትነን ወድቀን የምንጠፋበት፥ ከወደቅንበትና ከጠፋንበት ከተዘራንበትና ከተበተንበትም፥ በዝተን የምንታጨድበት፥ የምንወቃበትና የምንሰበሰብበት ጊዜ እንዳለን በጥሞና የምናስብባት ወቅት ናት:: ወቅትና ዘመን እየጠበቀ በሰው ላይ የሚፈራረቀውን ፈተና እንዲቋቋሙ የሕጻናቱን አዕምሮ ለመቅረጽ በፍልሰታዋ ሰሞን ይህች ያንጎራጉራሉ::

ከእህሉ ሁሉ ጤፍ ታንሳለች፥

ወድቃ በስብሳ ትነሳለች፥

የአዳም ልጅ ሁሉ ሰነፈና፥

ወድቆ ቀረ አሉ በጎዳና

ያዳም ልጅ ሁሉ አትስነፍ፥

ጽድቅ እየሠራህ እለፍ”

በኢትዮጵያዊ ዘይቤ በፍልሰታ ሰሞን ይሰጥ የነበረው ይህንና ሌላውም ሁሉ ተረሳ:: በምትኩ በየመንደሩ በየደብሩና በየገዳማቱ እንኳ ሳይቀር ባንድ ወቅት አቡነ ማትያስ “በሊቃውንት ሌሎች ሊቃውንት በመጻሕፍትም ሌሎች መጻሕፍት ተተክተዋል” ብለው በድፍረት እንደተናገሩት ኢትዮጵያዊ ጽናትን፥ የተዋሕዶ መሠረታዊ እምነትን አናውጾ ግልብነትን፥ ገለፈትነትን፥ ራስ ወዳድነትን የሚተካ ትምህርት ለወጣቱ እየተሰጠ ነው:: የአሜሪካን ትውልድ ይህ መሳይ ፈተና ገጠመውና Schlosser የተባሉት አሜሪካዊ ሊቅ፥ ወጣቱ አቅጣጫውን ሳተ እሱነትንም ረሳ ከዚያም አልፎ “Fast Food Nation” ሆነ ብለው የጮኹት ትዝ አለኝ:: ለችግሩ መፍትሔ ይሆናል ብለው የተናገሩት በዚህ ወቅት ለኛም መነገር ያለበት መስሎ ታየኝ:: የመጽሐፍ መተርጉማን ሊቃውንት አበው፥ መጻሕፍትን አንድም እያሉ ሲያስተምሩን ትንቢትን ታሪክን ባሕልን እያነጻጸሩ እያተቱና እየተረጎሙ ይመጡና፥ ሰሚና አስተዋይ ልቡና ያለው ሊይዘውና ሊጨብጠው የሚገባውን ፍሬ ነገር ለማስጨበጥ፥ “ታሪኩን ባወቀ አናግሮታል፥ ትንቢቱንም ባወቀ ፈጽሞታል ምሥጢሩ እንደምነው ቢሉ” ብለው በባሕል፥ በታሪክና በትንቢት የተጠቀለለውን ምሥጢር ፈልቅቀው ያቀርቡታል:: በያመቱ የምናደርገው ሱባዔ ሳይቋረጥ፥ በጤፏ አማካይነት ለሕጻናቱ የሚቀርበውም ትምህርት ሳይሰረዝ፥ ለተርዮና ለልማድ ብለን ሱባዔ ገባን ከሚለው ባዶ ስሜታዊ ልማድ ተላቀን፥ “እኛም ማየት አለብን” ብለው የተናገሩትን ሐዋርያዊ ቆራጥ ውሳኔ አብነት እናድርግ:: ቤተ ክርስቲያናችንም ከገባችበት ዝብርቅርቅ ተላቃ፥ ይልቁንም ከመንግስት ጀምሮ በመላ አገራችን ለሚፈጠሩ ድርጅቶች መልካም ምሳሌ ሆና ለማየት የምንመኘወን ተግባራዊ ለማድረግ እንጥር ዘንድ ለማሳሰብ ይህችን ጦማር ማዘጋጀት ወደድኩ::

በብሔራዊና በመንፈሳዊ ስሜታቸው የተመኙትን አይተው ያለፉ ኢትዮጵያዉያን

ኮፌዳየን ይዤ ከተወለድኩበት ቤት ወጥቼ ካሳደጉኝ ወላጆችና ከጎረቤት ሰዎች ርቄ ወደ ቅኔ ቤት ስሔድ፥ ቅኔው ከሚፈትላቸው ፍጥረቶች በስተጀርባ ያለውን ሁሉ መዳሰስ እንድችል ነው:: ቤተ ክርስቲያኔ ወደ ውጭ ስትልከኝም፥ በየደረስኩበት ዓይኔ ከሚያው ጆሮየ ከሚሰማው ባሻገር ያለውን ሁሉ እያየሁ ለመረዳት መጣሩን የበለጠ እንድጠቀምበት አደራ ብላ ነው:: ይህ ልማድ ሆነብኛና ከአገሬ ስወጣም ከማየው ከምሰማው፥ ከማነበው በስተጀርባ ወደ ኢትዮጵያ በመሻገር በሕዝቧና በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ተደረገ ተፈጸመ እየተባለ ራሷ ቤተ ክርስቲያናችን በምትልካቸው ሰዎች የሚነገረውንና የሚታየውን ከማየትና ከመስማት ዓይነ ሕሊናዬ አላርፍ አለ::

የሚደረገውን ስሕተት ሁሉም የታዘበው ቢሆንም ለንጽጽር ያህል ትንሽ ተናግሬ እንደ ሐዋርያት እኛም ማየት አለብን በሚል ፍላጎት ተነሳስተው ማየት የፈለገቱን አይተው ካለፉ ኢትዮጵያውያን ለምሳሌ ያህል ጥቂቶችን እጠቅሳለሁ:: ከዮቶር ተማሪ ከሙሴ ልጀምር። ሙሴ የፈጣሪውን ገጽ ለማየት ፈለገ:: በቁሳዊ አይኑ ከቁሳዊ ባሕርይ የራቀውንና የረቀቀውን አምላክ ማየት እንደማይችል አምላክ ቢነግረውም፥ “ጀርባየን ታያለህ ፊቴን አታይም”( ዘጸ ፴፬፡፳፫) ብሎት ነበርና፥ ከቁሳዊ አካሉ ከተላቀቀ በኋላ የተመኙትን የማይነሳ የነገሩትን የማይረሰው አምላክ፥ በተወሐደው ሥጋ መለኮትን በደብረ ታቦር ተራራ ላይ አሳየው::

በሉቃስ ወንጌል ላይ እንደመዘገበው ስምዖን የተባለ ሰው ለማየት ሲመኘው የነበረውን በማየቱ “ለሰዎች ሁሉ ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይኖቼ አይተዋልና ውሰደኝ” (ሉቃ ፪፡፴) ብሎ የተናገረውን ሳንጠቅሰው መለፍ ተገቢ አይመስለኝም:: በአገራችንም ማየት አለብን ብለው ለማየት የፈለጉትን ያዩ  ለጠቅላላዋ ኢትዮጵያና ለቤተ ክርስቲያናችን እየታገሉ ያለፉ የምንጠቅሳቸው ብዙ አባቶች አሉን::

፩ኛ. በላይ ዘለቀ (ብሔራዊ ምሳሌ)

በበላይ ዘለቀ ዙሪያ ሲነገር የሰማሁት በጣሊያን ወረራ ጊዜ የተፈጸመ ታሪክ አለ:: በክፉ ቀን “ይህ ክፉ ቀን አልፎ መልካም ነገር ሳታሳየኝ አትግደለኝ” እያሉ የሚመኙ ቅዱሳን ዜጎች እንዳሉ ሁሉ፥ በተቃራኒውም በክፉ ቀን ውስጥ ከሚፈጸመው ክፉ ነገር ጥቅም የሚያገኙ ክፉ ሰዎች ክፉው ቀን እንዲቀጥል አጥብቀው የሚመኙ መኖራቸው ግድ ነውና፥ ጣሊያን በወረረን ዘመን፥ ከጠላት ጋራ ተናንቀው የሚጋደሉት ኢትዮጵያውያን ተሸንፈው፥ ጣሊያን አገሪቷን መቆጣጠር ይችል ዘንድ፥ በኢትዮጵያውያን ላይ አዚም ለማድረግ የተሰለፉ የሕብረተ ሰብ  ጠልሳሚ ገለፈቶች ነበሩ::

ከጠልሳሚ ገለፈቶች አንዱ በላይን ለመጥለፍ የበላይን ብሔራዊ ፍቅር ተረድቶ በላይ በሚወደው መንፈስ መስሎና አስመስሎ በመጠልሰም ቀረበ:: ተኩሶ እንዲስት የሚያደርግ የመተት ጠልሰም ሰጠው:: በላይ ደፍተራ ገለፈት ጠልስሞ የሰጠውን ባንገቱ አጠለቀና ለመፈተሽ በወፈጥ ድንጋይ ላይ አልሞ ለመተኮስ ሲሞክር፥ ያለመውን የድንጋይ ክምር ሊመታ ይቅርና፥ በቆቅ ላይ አነጣጥሮ የማይስተው እጁ እየተንቀጠቀጠ፥ ጣቱ የጠብ መንጃውን ምላጭ መሳብ አቃተው:: ጠልሰሙን ካንገቱ አውልቆ እንደገና ሲሞክር አላማውን መታ:: የገለፈቱ ከሐዲነት የበላይን ብሔራዊ ስሜት የበለጠ አነደደውና፥ ከግራኝ መሐምድ ጋራ የታገሉ ኢትዮጵያውያን እንደገና በአድዋ ላይም በአጼ ምንይልክ መሪነት ኢትዮጵያውያን ያዩትን ድል እኔም ማየት አለብኝ ብሎ በጋል ብሔራዊ ስሜት የተመኘውን ነጻነትና ድል አየ፥ አገኘ:: በመንፈሳዊ ታሪካችንም የተመኙትን አይተውና አድርገው ካለፉ ጥቂት ሰዎች አቡነ ቴዎፍሎስንና አባ አበራ በቀለን እጠቅሳለሁ::

፪ኛ አቡነ ቴዎፍሎስ (መንፈሳዊ ምሳሌ)

የአቡነ ቴዎፍሎስ አባታዊ ብቃታቸው የሚያጠያይቅ ባይሆንም በመንደርተኝነት በሽታ የተጠቁ ሰዎች ይፈጥሩባቸው የነበሩትን ችግሮች እየታገሉ በቆዩባቸው ዘመናት ከሰሯቸው ሥራዎች አንዱ እንደ ነቢይ ያስቆጠራቸው ከአብዮቱ ቀደም ብለው ያወጁት ቃለ አዋዲ ነው:

ለዘመናት ሥር ሰዶ፥ የኖረውን የመሬት ሥርአት የሚነካ ሥር ነቀል አዋጂ ማወጅ ይቅርና የደብር አለቃ መሰየም በማይችሉበት ሥርአት ውስጥ ይህን መሳይ አዋጅ በኢትዮጵያ ምድር ማወጃቸው በወቅቱ ብዙውን አስደንቋል:: የመሬት ተጠቃሚውንም አስቆጥቷል:: በሳቸው ግላዊ ጥላቻ የነበራቸውንም ሰዎች ጥላቻቸውን የበለጠ እንዲያጋግሉት ረድቷቸዋል::

ብጹዕ ቴዎፍሎስ ፀሐቅ ለቃለ ትምህርት ወለ እመ ኮንከ ትክል ተርጉሞ እምነ ኩሉ መጻሕፍት ቃላተ አጽግቦሙ ለሕብከ ወአብርህ ሎሙ እምነ ብርሃነ ሕግጋቲከ ከመ ይኩኑ በዝንቱ አብዕልት በብዝሐ ትምህርትከ”(. . አንቀጽ ፭፡ ገጽ ፵፱ ቁጥር ፻፲፮) ማለትም፦ “የተጻፈውን መጽሐፍ ሁሉ ትርጉመህ የተረዳህ ከሆንክ፥ የሚሰሙህን አብራርተህ በመንገር ለማርካት ተዘጋጅ፥ ካንተ የሚሰሙት ምክርና መመሪያ ከጨለማ ያላቅቃቸው ዘንድ ከተረከብከው ከረካህበት እውቀትም በጨለማ ላሉት ሰዎች አብራላቸው” በሚለው መጽሐፍ እየተመሩ ለሚመሯት ቤተ ክርስቲያናቸው፥ ለጠቅላላ ኢትዮጵያውዊ ዜጋቸው የተሻለ ነገር አይተው ለማሳየት የሚናፍቁ አባት ነበሩ::

አልምቶም አጥፍቶም ያለፈው አብዮት በሩቅ እየነደደ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱንና የመሬት አዋጅ በማወጅ ቤተ ክርስቲያኒቱንም እንደሚንጣት በተሰጣቸው ጸጋና ችሎታቸው አስቀድመው ተመለከቱ:: እንደሳቸው ያለ ቅዱስ አባት ጠቃሚም ሆነ ጎጂ በአገር ላይ የሚመጣውን አስቀድሞ አይቶና ተረድቶ፥ ሕዝቡ በተጠንቀቅ እንዲጠብቅ ቃጭልና ደዎል ማሰማት ተግባሩ ነውና፥ ይህን እይታ ለማግኘት ፍለጋ ገብተው፥ እኛም ማየት አለብን ብለው የተመኙትን እንዳዩት ሐዋርያት፥ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ቴዎፍሎስም እኛም ማየት አለብን ብለው በድሬዳዋ ቅዱስ ሚካኤል በገቡበት ሱባዔ፤  መጥምቁ ዮሐንስ ያወጃት “ቃለ አዋዲ” ለሚመሯት ቤተ ክርስቲያን  መሬት ላራሹ ከመታወጁ በፊት ታየቻቸው።

ሐዋርያት የተሰወራቸውን “እኛም ማየት አለብን” ብለው የተመኙትን ቢያዩ ም ይህን እይታቸውን የሚቃወሙ ብዙዎቹ የወቅቱ ገለፈቶች ተነሱባቸው:: እንዲአውም አልፈው ተርፈው “የቤተ ክርስቲያን የበላይ ጠባቂነተዎን የሚፈታተን ነው” ብለው ለጃንሆይ ከሰው ያቀረቡም ነበሩ:: አቡነ ቴዎፍሎስ በገለፈቶች የደረሰባቸውን ሁሉ ተጽእኖ አሸንፈው፥ ጃንሆይን አግባብተውና አሳምነው በነጋሪት ጋዜጣ እንዲታወጅ አስደረጉ:: ከጥቂት አመታት በኋላ በቃለ አዋዲ አዋጃቸው የቀደሙት አብዮት፥ የጃንሆይን መንግሥት ገልብጦ በገጠርና በከተማ ቦታ ላይ አብዮታዊ አዋጅ አዋጀ:: በነማርክስ ፍልስፍና እየተገፋ መጥቶ መሬት ላራሹን ያወጀውን አብዮታዊ ብጹዕ ወቅዱስ ቴዎፍሎስ “ቃለ አዋዲ” ብለው በነጋሪት ጋዜጣ በማሳወጅ የአብዮቱን አዋጅ ቀደሙት።

የመሬቱ ተጠቃሚወች ቢያጉረመርሙባቸውም፤ አርቀው የተመለከቱ ሊቃውንቶች ግን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ንሕነሰ ኢኮነ ዘነሳእነ መንፈሰ ዝ ዓለም:: ወባሕቱ ነሳእነ መንፈሰ ዘእምእግዚአብሔር ከመ ናእምር ዘወሀበነ እግዚአብሔር ጸጋ”(፩ኛ ቆሮ ፪፡፲፪) ያለውን በመጥቀስ አቡነ ቴዎፍሎስን ሐዋርያዊት እይታ እጅግ አደነቁ። አቡነ ቴዎፍሎስ ኢትዮጵያ ባፈራቻቸው ሊቃውንት ተቀርጸው ያደጉ፥ በትርጉም አልባ ልማድ ከሚመራ ሕሊና የተላቀቁ፥ ያሰቡትንና የታያቸውን ለማድረግ ከንጉሡ ይህ ይመጣብኛል ብለው የማይጨነቁ መንፈሰ ጠንካር ባሕርይ ነበራቸው:: ለውጡ አቅጣጫውን ስቶ በኋላ በደም ይነከር እንጅ፥ በመጀመሪያ “ኢትዮጵያ ትቅደም ያለምንም ደም” ብሎ ከዳር ዳር ሕዝቡ የፈነደቀለት ነበር:: ሕዝቡ በሰለቸው ንጉሣዊው አገዛዛና “ማየት አለብን” ብሎ በተደሰተበት ለውጥ መካከል ምርጫ የቀረበበት ለቤተ ክርስቲያን ፈታኝ ወቅት ነበር::

ሆኖም “ኢትቅንይዎሙ በኩርህ አላ በጽድቅ”(፩ኛ ጴጥ ፭፡፪) ማለትም፥ ‘ሕዝቡን በፍቅርና በእውነት እንጅ በግድ አትግዙ’ የሚለውን አንድም ብለው የሚተረጉሙ መንፈሳዊ አባት ከመሆናቸው ጋራ፥ ሕዝቡ “ማየት አለብን” ብሎ በጋለ መንፈስ የተመኘውን በንጉሣዊው አስተዳደርም ላይ የነበረውን ህዝባዊ ጥላቻ አንብቦ የመገንዘብ ብሩህ አዕምሮ ያለው አባት ከተጎዳው አካል ጋራ የመሰለፍ ኃላፊነት አለበትና አቡነ ቴዎፍሎስ ራሳቸው ንጉሡ ቀ.ኃ. ሥላሴ ያልተቃወሙትን ይልቁንም የደገፉት ለውጥ ደገፉ:: አብዮቱ “ጊዜአዊ ተሐድሶ ጉባዔ” ብሎ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሊቆጣጠራት ሲሞክር ደግሞ በጠበንጃ ታጅበው እስከ ተወገዱባት ቅጽበት ድረስ እኔ በሕይወት እስካለሁ ድረስ ቤተ ክርስቲያንን መሳሪያ አታደርጓትም በማለት የታገሉ አባት ናቸው:: ዛሬ በሳቸው ቦታ ያሉት እንኳን አስቀድመው ለቤተ ክርስቲያን ጠቃሚ ራዕይ አይተው አቅጣጫ ሊአሳዩና ሕዝቡ የደገፈውን ሊደግፉ፥ የነበረው ፈረሰ ነገረ መለኮቱ ተቃወሰ እየተባለ ሲነገራቸው ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው፥ ቤተ ክርስቲያኒቱን ላለው መንግሥት ሽፋን አደረጉ እየተባሉ ነው::

መንፈሳዊ መሪ በሕዝብ ላይ የሚመጣውን አስቀድሞ አይቶ ለማሳየት መቻል ብቃት ሊኖረው እንደሚገባ ቤተ ክርስቲያናችን “አብርህ ሎሙ እምነ ብርሃነ ሕግጋቲከ ከመ ይኩኑ በዝንቱ አብዕልት በብዝሐ ትምህርትከ”(ፍ.ነ.አንቀጽ ፭፡ገጽ ፵፱ ቁጥር ፻፲፮) ብላ ያዘዘቸውን መመሪያ ብፁዕ ወቅዱስ ቴዎፍሎስ ቃለ አዋዲ ብለው በማወጅ ተግባራዊ ያደረጉትን፥ ከስማቸው ጋራ ተቀብሮ እንዲረሳ ብዙ ሰዎች በሚታገሉበት ወቅት፥  መንነው በበረሐ ከወደቁት ኩምራን ሕብረተ ሰብ መካከል መጥምቁ ዮሐንስን እየጮኸ እንዲወጣ የቀሰቀሰ አምላክ፥ ቃለ አዋዲውን ከተቀበረበት ፈልቅቆ አውጥቶ ተግባራዊ ያደርግ ዘንድ፥ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩንቨርስቲ አበራ በቀለን እግዚአብሔር ቀሰቀሰ::

፫ኛ: ጋሼ አበራ በቀለ (መንፈሳዊ ምሳሌ)

ሰው ሲመነኩስ፥ ምንኩስና እንደ ጀመሩት እንጦንስና መቃርስ፥ ከናት አባት የወረሰውን፥ እራሱም ጥሮ ግሮ ያፈራውን ንብረት ለድሐ ሰጥቶ መንኖ፥ ድሕነትን መጎሳቆልን፥ መራብን መጠማትንና መራቆትን መርጦ፥ ወደ ገዳም ለመግባት እንጅ፥ አሁን በዘመናችን እንደምናየው በዓለም ውስጥ ለመኖር የሚገጥመውን ድሕነትና ጥሮ ግሮ መኖሩን ሸሽቶ፥ ምእመናን የሚሰጡን ገንዘብ በመዝረፍ የግል ቤት ለማነጽ ገንዘብ ለመሰብሰብ በሚያስችለው ቦታ ሁሉ፥ ከጠቅላይ ሥራ አስኪያጅነት እስከወረዳ ከደብር ልቅና እስከ ገጠሪቷ ቤተ ክርስቲያን ያሉትን ቤተ ክርስቲያኖች ለመውረር ፈጽሞ አልነበረም::

ጋሼ አበራ በቀለ፥ እውነተኛውን ምንኩስና በሕይወቱ የተረጎመ ነው:: በዓለም ተወዳድረው መኖር አቅቷቸው ውድድሩን ሸሽተው፥ ለምናኔ የሚሰጠውን የሕዝቡን ስነ ልቡና አጥንተው ከዓለም ያጡትን ገንዘብ ባቋራጭ በማግኘት፥ የከተማ ቤት ለማነጽ ገንዘብ ለመሰብሰብ ቆብ እየጫኑ ከዚያም ወደ ጵጵስናው ከገቡት ሁሉ የዘመናችን አስመሳይ መነኮሳትና ጳጳሳት ጋሼ አበራ በቀለ ፈጽሞ የተለየ ነው:: ጋሼ አበራ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጣ ዓለምንና ፍላጎቷን በተሰማራበት ትምህርቱ ተረድቶ፥ ንቆና መንንኖ ነው:: ይህም ይታወቅ ዘንድ ኑሮን በውድድር አሸንፎ ለመኖር የደከመበትን ሙያና ዓለማዊውን ኑሮ በመመነን እርግፍ አርጎ ወደ ቤተ ክርስቲያን የመጣ እውነተኛ መናኝ ነው:: አካባቢውን በከንቱ ውዳሴ ላለመጠለፍና ባባነቱ ክብር እያስፈራራ ሕዝቡን ለመጋለብ ብዙውን ሰው እየጠለፈ በመጣል ላይ ያለውን ቀሚስ አላንዘረፈፈም:: የእንጦንስን ምንኩስና ከአእምሮ አውጥቶ፥ የሲሞንን መንፈስ በጭንቅላት ላይ የሚቀርጸውን የዘመኑን ቆብ ሳያጠልቅ፥ የሰማእታቱን የነ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያገልግሎትና የጽድቅ ዝናር ታጥቆ የጽድቅ ጥሩር አጥልቆ ወደ ቤተ ክህነት ገባ:: ትዳር ይዘው ወልደው አሳድገው የተፈጥሮ ግዴታቸውን የተወጡ ክርስቲያኖች፥ ቀሪ ዘመናቸውን በልጆቻቸው መካከል እየኖሩ ክርስቲያናዊ ምሳሌነታቸውን በእጦንስና በመቃርስ ሕይወት ለማሳለፍ እንደሚመነኩሱ፥ ጋሸ አበራም “እኛም ማየት አለብን” በሚል እውነተኛው ብፁዕና ቅዱስ ፓትርያክ ቴዎፍሎስ የጀመሩትን ከቆመበት ጀምሮ በብሕትውና ሕይወቱ በብዙ ፈተና እና እንባ ከፈጸመ በኋላ፡ አቡነ ቴዎፍሎስ የገቡበትን አማናዊ ምንኩስና በሕይወቱ ፈጽሞ ይህችን ዓለም ያቋረጠ የዘመናችን ቅዱስ ነው ማለት ይቻላል::

በቀሪ ዘመኑ ባደረገው እንቅስቃሴ ሁሉ አብራችሁ ተሰልፋችሁ ‘አባ’ ‘አባታችን’ እያላችሁ የሸኛችሁ ወገኖቼ፥ በዚህ አጋጣሚ ጋሼ አበራ በቀለን አንስቼ ከሱ ጋራ ያሰልፍኩትን ስገልጽ በአዕምሮየ የሚመጣ፥ ጋሼ እያልኩ ስከተለው የነበረው ትዝታ ነው:: መንኩሰው ሳላያቸው ድምጻቸውን ሳልሰማው ስላመለጡኝ ባለመታደሌ እያዘንኩ፥ ዕድሉ ገጥሟችሁ አባ እያላችሁ በመከተል እስከ መጨረሻ የሸኛችኋቸው ወገኖች፥ ለኔ የሚታየኝ ጋሼ አበራ እያልኩ እከተለው የነበረው ጋሼ አበራ ነው:: ስለዚህ አሻግሮ በሚያየው ትዝታየ ጋሼ እያልኩ በመግለጼ የሚሻክራችሁ ወገኖቼን ይቅርታ እጠይቃለሁ:: ጋሼ አበራ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ተማሪ ነበር:: ከዚያም አሜሪካ መጥቶ ዘመናዊ ትምህርት ቢማርም፥ ከቤተ ክርስቲያናችን ያብነት ትምህርቶች የተሳተፈበት ከካህናቱ ጋራ የመግባቢያ ቋንቋ ስላልነበረው በቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት እይታ ያስኳላ ተማሪ ነበር:: ጋሼ አባራ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አሜሪካ ከመምጣቱ በፊትና ከተመለሰም በኋላ ከባሕታዊ ገብረ ሥላሴ ተድላ ጋራ የቅርብ ግንኙነት ስለነበረው፥ የብሕትውና መንፈስ ይታይበት ነበር:: ይህም በወላይታ በነበሩት በባሕታዊ ደስታ ባሕርይና አርያ እንደተቀረጹት እንደ አባ መላኩ (ፓትርያርክ ተክለ ሃይማኖት) እና አባ መስቀሌ ማለት ነው::

ጋሼ አበራ ከአሜሪካ ተመልሶ በየኒቨርስቲው በማስተማር ላይ ሳለ፥ እድገት በኅብረት ታወጀና ያንድ ቡድን መሪ ሆኖ ወደ ገጠር ዘመተ:: ዘመቻውን ፈጽሞ እስኪመለስ የዘመቻው መሪ ሆኖ እንዲቆይበት በተዘጋጀው የዘመቻ ጣቢያ ከመቆየት ይልቅ ባካባቢው ወዳለው መቃብር ቤት ተጠልሎ የዚያን አመት የፍልሰታ ሱባዔ ፈጽሞ ወደ አዲስ አበባ እንደተመለሰ ይነገር ነበር:: አብረውት የዘመቱት ሁሉ ከቀድሞው ባሕል የሚጋጭ ነገር እየፈጽሙ ከባላገሩ ጋራ ሲጋጩ፥ ጋሼ አበራ ገላጋይ በመሆ ከፈጸመው ተልኮ ባሻገር፥ በዘመቻው ጣቢያ ሆኖ ይታየው የነበረው፥ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያር ቴዎፍሎስ እኛም ማየት አለብን ብለው ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ያወጁት ቃለ አዋዲ ነበር:: ጋሼ አበራ በቀለ በዘመቻ ውስጥ በነበረበት ወቅት አሻግሮ ይመለከተው የነበረ ብፁዕ ፓትርያርክ ያወጁት ቃለ አዋዲ ስለነበረ፥ ከዘመቻ በኋላ ወደ ወደ የኒቨርስቲው አልተመለሰም::

“አቡነ ቴዎፍሎስ ከአብዮቱ በፊት ቀደም ብለው አይተው፥ እድርጌ ማየት አለብኝ ብለው ጀመረውት የቆመውን ቃለ አዋዲ ፈጽሜ ቀሪውን ዘመኔን እግዚአብሔርን በማገልገል እንዳሳልፍ ፍቀዱልኝ” ብሎ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ማመልከቻ አስገባ:: ቤተ ክህነት “የምትሰማራበት መስክ ቢኖርም እንኳ አሁን የኒቨርሲቲው የሚከፍልህን ያህል የምንቀጥርበት የገንዘብ የለንም ትንሽ ጠብቅ የሚል መልስ ሰጠው”::

አቡነ ቴዎፍሎስን ቃለ አዋዲው እንዲያውጁ ያስገደዳቸው መንፈሳዊ ኃይል፤  “የኒቨርሲቲው የሚከፍልህን ያህል የምንቀጥርበት ገንዘብ የለንም” የሚለው የቤተ ክህነቱ ቁስአካላዊ መልስ ጋሼ አበራን እንዳይቀበል አስገደደውና የሚከተለውን ጥያቄ ለቤተ ክህነቱ አቀረበ፡፡

የማደራጀትና የኮምኒኬሽን ሙያ ተምሬአለሁ:: በዚህ ሙያየ ለአቡነ ቴዎፍሎስ ታይቷቸው ያወጁትን ቃለ አዋዲ ለመላ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ተከታይ ክርስቲያን ለማሳየት እመኛለሁ:: ስለምትከፍሉኝ ገንዘብም አታስቡ፥ ሥራውን የማካህድበት መኪናም ቤተ ክህነቱን አልጠይቅም:: አሜሪካ በተማሪነት ሳለሁ ከትምህርት ጊዜየ በተረፈው ሰአት የወጥቤት እቃ እያጠብኩ በሰበስብኳት ገንዘብ የገዛኋት መኪና አለችኝ:: ለነዳጅ፥ ለሥራ ማስኬጃና ቢሮ ብቻ ፍቀዱልኝ አለ:: አቡነ ተክለ ሃይማኖት በመንበረ ፓትርኩ ላይ ከተሰየሙ በኋላ ለፓትርያርኩ የተመደበውን የወር ገቢ “የሰንበት አስተማሪዎች ይቀጠሩበት አሉ” ተብሎ እንደብርቅ ይነገር ስለነበረ የጋሼ አበራና የአቡነ ተክለሃይማኖት ፍላጎት ተገጣጠሙና የወቅቱ አድናቆት የተትረፈረፈው ወሬ ሆነ::

ጋሸ አባራ ሥራውን ለማካሄድ ቤተ ክህነቱ ሊተባበረው ስላልቻለ፥ በተማረው ስልቱ እቅዱን ነድፎ ለዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጽ. ቤት በማቅረብ እርዳታ ጠየቀ:: በልማት ኮሚሽን በኩል ከዓለም አብያተ ክርስቲያናት የጠየቀውን ገንዘብ አገኘ:: የቢሮውን ሥራ ለመጀመር፥ ከነ አለቃ አምደ ጽዮን ጋራ ሆነው የትምህርት ክፍሉን ሲመሩ የነበሩት ነፍሳቸውን ይማርና የቅኔ ባለሙያ አቶ ቄርሎስ ከጡረታ ተመልሰው የመምሪያውን ጽ/ ቤት እንዲመሩ ተመደቡ:: ከአቡነ ባስልዮስ ዘመን ጀምረው  የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን  ገቢና ወጭ ይቆጣጠሩ የነበሩት መምሕሬ ተፈራን ከጡረታቸው መልሶ ለሰበካ ጉባዔው መምሪያ  መደባቸው::

ጋሼ አበራ ቀጠለና “እኔ ከውስጥም ከውጭም የተማርኩት ያስኳላ ትምህርት እንጅ  ከቤተ ክርስቲያኒቱ አብነት ከሚባሉቱ ባንዱም ተሰለፌ ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት የቀሰምኩት የለኝም:: እኔ የማቀብላቸውን እቅድ በቤተ ክርስቲያኒቱ የንግግር ለዛና ቋንቋ በማዛመድ በከተማ በገጠር ለሚኖሩት አበው ሊቃውንትና ለጠቅላላ አገልጋይ ካህናት የሚገልጹልኝ ያስፈልጉኛልና ቤተ ክህነቱ ብቁ ናቸው የሚላቸውን ይመድብልኝ” ብሎ ቤተ ክህነቱን ጠየቀ::

ዛሬ በግሪክ አገር ያለችውን ቤተ ክርስቲያን በማገልገል ላይ ያሉትን ቀሲስ ኃይለ ልዑል ገሪማንና እኔን በጀታችንን እንደያዝን ተንቀሳቃሽ ‘የሰበካ ጉባዔ አስተዳደር’ አደራጅ ቡድን የሚል ስም ተሰጥቶን ለመጀመሪያ ጊዜ ከጋሼ አበራ ጋራ እንድንሠራ ወደ መመሪያው ቤተ ክህነት መደበን:: ጋሼ አበራ፥ አቶ ቄርሎስን፥ መምሕሬ ተፈራን፥ ቀሲስ ኃይለ ልዑል ገሪማንና እኔን ጠርቶ፥ አቡነ ቴዎፍሎስ የነደፉት ሐሳብ የታተመበትን ነጋሪት ጋዜጣ አባዝቶ ለያንዳንዳችን ሰጠንና፥ ይህን የተቀደሰ ዘላቂና አላማ ከፍጻሜ ለማድረስ እንደሚጠብቀን ከባድ ኃላፊነት ገለጸልን::

የሚቀጥለው ሳምንት የሐምሌ የመጨረሻ ሳምንት ነበር። በትክክል በማላስታውሰው ቀን  የጋዜጣውን ኮፒ አባዝቶ ከጠረጴዛው ላይ ዘረጋው:: እጁን በላው ላይ ጫነና፥ እንባውን በጋዜጣው ላይ እያፈሰሰ “ለበአቡነ ቴዎፍሎስ ይህን እቅድ የገለጸክ አምላክ ሆይ፥ ሥራውን ለማከናወን እንበቃ ዘንድ ለኛም መንገዱንና ጥበቡን አሳየን” ብሎ ጸለየ:: በፈሰሰው እንባ የራሰውን ጋዜጣ አጣጥፎ ያዘና “እኔ ለሁለት ሳምንት የለሁም፥ እናንተ ብትፈልጉ ከቢሮ እየመጣችሁ ከአቶ ቆርሎስና ከመምሬ ተፈራ፥ ብትፈልጉም ለዚህ ሥራ ቅን አመለካከትና የሐሳብ አስተዋጽኦ ለማድረግ ችሎታ አላቸው ብላችሁ ከምትግምቷቸው ሰዎች ጋራ ተነጋገሩ” ብሎ ያባዘውን ኮፒ ጥሎልን ሄደ::

በነጋሪት ጋዜጣዋ ላይ የነበረችውን የአቡነ ቴዎፍሎስን ሐሳብ አስፍቶና አምልቶ፥ ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ጀምሮ እስከ መንበረ ፓትርያርክ ድረስ እንዲያገናኝ አድርጎ መዋቅሩን በመዘርጋት በደብተር ጽፎ ከፍልስታ በኋላ መጣ:: “እናንተስ ምን ይዛችሁ መጣችሁ?” ብሎ ጠየቀን:: ቀሲስ ኃይለ ልዑል ገሪማ፥ እንደ ጋሼ አበራ ወደውጭ ወጥተው የመማር እድል ገጥሟቸው የጋሼ አበራን ያህል ስልት ባይኖራቸውም፥ ሊቀ ዲያቆን ሆነው የአቡነ ቴዎፍሎስ የቀርብ ረዳት በመሆን ባሳለፉት ጊዜ ከራሳቸው ከአቡነ ቴዎፍሎስ የቀሰሙት ልምድ ስለነበራቸው ይመስለኛል፥ የመሰላቸውን የራሳቸውን ሐሳብ ጨምረው መምጣታቸው ትዝ ይለኛል::

እኔ ግን ከራሴ የጨመርኩት ሀሳብ ሊኖረኝ ቀርቶ፥ ነጋሪት ጋዜጣውን ከኪሴ አውጥቼ አላየሁትም:: እንዲያውም በኪሴ ይዤ ስለሰነበትኩ ጋዜጣው ወደ ጥጥነት ተለውጦ ጽሁፉም ጠፍቶ ነበር:: ጋሼ አበራ በቀለ በዓይኑ የገረፈኝ የትዝብት ግርፋት ምን ጊዜም አልረሳውም:: ሰንፌ ደክሜ የሚፈለግብኝን ሳላደርግ በመቅረቴ ከአብነት መምሕሮቼ ከተሰነዘረብኝን ተግሳጽ ቀላቅዬ በመያዝ ለሕይወቴ መመሪያ አድርጌዋለሁ::ነገር ግን ከጋሼ አባራ፥ ከቀሲስ ኃይለ ልዑል ገሪማና ከነ አቶ ቄርሎስ ጋራ ባደረኩት ተሳትፎ፥ የመዋቅሩን ሥልት (ቃለ አዋዲውን) እንደ ውዳሴ ማርያም በቃሌ ስለያዝኩት መምሪያውን እየወከልኩ በየጊዜው ለሚመጡት ካህናት አስተማሪ ሆኘ ተመደብኩ።

ጋሼ አበራ ከባሕታውያን ጋራ ያለው ቀረቤታ ያይልበት ነበር:: ብሕትውና ሞተሩ እንዳረጀበት መኪና ተንገጫግጮ በባሕታዊ ገብረ መስቀል እጅ እስከ ቆሞበት ዘመን ድረስ፥ በተለይ አብዮቱ በፈነዳበት ዘመን አገሩን ወሮት ነበር:: ባሕታውያን የማይደርሱበት ስርቻ ስለሌለ የቃለ አዋዲው እንቅስቃሴ በባሕታውያኑ ቢጀመር ባጭር ጊዜ ውስጥ በመላ አገሪቱ ይዳረሳል በሚል ወቅታዊ ግምት፥ እንቅስቃሴው በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ቅጽር ውስጥ በባሕታውያን ተጀመረ:: ከራስ መኮንን ድልድይ አጠገብ በነበረው ፋሲካ ሆቴል ምግብ አቅራቢነት ጉባዔው ለሁለት ሳምንታት ሌትና ቀን ተካሄደ:: ባሕታውያኑ የሚናገሩትን ሁሉ ለማስፈር ካቅም በላይ ስለነበረ:: በቴፕ እንድንቀዳ ቴፕ ሪክርድም እንደተሰጠን ትዝ ይለኛል::

አቡነ ቴዎፍሎስን አውርዶ ለወታደራዊው መንግሥት አሳልፎ በመስጠት ለማስገደል “ጊዚያዊ ተሐድሶ ጉባዔ” በማለት ደርግ ከሰየመው ቢሮ ቄስ ዳኛቸው ካሣሁን ወደኛ እየመጡ፥ ሌትና ቀን ከኛ ጋራ እያደሩ ከባሕታውያን የሚወጣውን ቃል ለማስፈር ትልቅ ሚና ተጫውተዋል:: የዜና ቤተ ክርስቲያን አዘጋጅ መጋቤ ሚስጥር ወልደሩፋዔል ፈታሂም ቀን ቀን አልተለዩንም ነበር::

በባሕታውያን ከተካሄደው ጉባዔ በኋላ፥ የሚቀጥለው የጋሼ አበራ እቅድ ቤተ ክሕነቱ በበጀት ቀጥሮ ያሰማራቸውን ሰባክያን መሰብስ ነበርና የጥሪው ወረቀት ተበተነ:: ሰባክያኑ ጥሪው ደርሷቸው ወደ አዲስ አበባ ከመምጣታቸው በፊት “አቶ አበራ በቀለ አድኃሪው አቡነ ቴዎፍሎስ ያቀዱትን አድኃሪ መርሆ በመከተል፥ ከምዕራቡ ዓለም ገንዘብ እየተቀበለ አብዮቱን ለመገልበጥ ይሞክራልና አብዮቱ እንቅስቃሴውን የማገድ ኃላፊነት አለበት” በሚል ተከሰሰና የሥራ ማስኬጃውን ቤተ ክህነቱ ለባንክ የማገጃ ትዛዝ ስለላከ እንቅስቃሴው ቆመ:: ጋሼ አበራ ተበሳጨ::

ስንጀምር በጸሎት ካለቀሰው ልቅሶ እጅግ የባሰና የመረረ ልቅሶ አለቀሰ:: የመምሪያው ባልደረቦች ቀሲስ ኃይለ ልዑል፥ አቶ ቄርሎስ መምሬ ተፈራና እኔ ያጽናናነው ትዝ ይለኛል:: አትርሱኝ ብሎ ወዴት እንደሄደ ሳይነግረን ለሁለት ሳምንታት ከመካከላችን ጠፋብን:: ተመልሶ በመጣ ጊዜ “ሰይጣን የዘጋውን በር አምላክ ከፍቶታል:: አቡነ ቴዎፍሎስ ያወጁትን ቃለ አዋዲ እኛም በተግባር ሳናየው አንቀርም፥ በዚህ ሳምንት ጥሩ ነገር እንሰማለን” የሚል ቃል ነገረን:: እንዳለውም ቤተ ክህነት እገዳውን እንዲያነሳ ከመንግሥት ትእዛዝ መጣና፥ የታገደው ገንዘብ ተለቆ ሥራው ተጀመረ:: ከራሱ አንደበት እንደሰማሁትና የጽ/ቤቱ አቶ ቄርሎስ ያረቀቁትን እንዳየሁት፦

የጽሁፉ ይዘት እንደሚከተለው ነበር፦

የሰበካ ጉባዔው እቅየተወጠነው በአቡነ ቴዎፍሎስ መሆኑ እርግጥ ነው:: አቡነ ቴዎፍሎስ ቢታሰሩም ያቀዱት እቅድ ሊወድቅ የማይገባ ጠቃሚ ነገር ነው:: አቡነ ቴዎፍሎስ ቃለ አዋዲውን ያወጁት ከአብዮቱ በፊት ነው:: ሲካሄድ የኖረውን የመሳፍንቱን ሥርአት የሚቃወም ሲሆን፥ የሥርአቱ መሪ ንጉሡ አምነው የተቀበሉት ነው:: ይህ መንግሥት ቤተ ክርስቲያናችን የመሬቱን ሥርአት የሚቃወም አስቀድማ በማወጇ አድንቆ መቀበል ሲገባው ይህን እቅድ መቃወሙ ተገቢ አይመስለኝም:: በዚህ ላይ ደግሞ አብዮቱ የቤተ ክርስቲያኒቱን ንብረት ወርሷል:: ሕዝቧን አደራጅታ በሕዝቧ እንድትደገፍ የምታደረገውን ጥረት ማሰናከል መንግሥትን በብዙ መንገድ ተወቃሽ ያደርገዋል የሚል ደብዳቤ በሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግ ደረስ አቅራቢነት ለኮረኔል መንግሥቱ ቀርበ::

በኮረኔል መንግስቱ ትእዛዝ የሥራ ማስኪያጃው ገንዘብ እንዲለቀቅ ተደረገ:: በባሕታውያን ተጅምሮ በደብር አለቆችና በመምሪያ ኃላፊዎች በየደረጃው ጉባዔ ከተካሄደበት በኋላ፥ ቃለ አዋዲው ጸድቆ ሥራው እንዲጀመር ወደ ሲኖዶስ ሲቀርብ በሁለት ደካማ ምክንያቶች አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጣሉት::

  • ፩ኛው ምክንያት እርሰዎ ባርከውት መክፈት ሲገባ፥ ተንቀው ቤተ ክህነቱ በማያውቃቸው ጆቢራ ባሕታውያንና በተራ ሰባክያን ተከፈተ የሚል ነበር::
  • ፪ኛውና አሳፋሪ የነበረው አሳብ ደግሞ፥ “አብዮቱ ባሰራቸው ባብዮቱ ጠላት በአቡነ ቴዎፍሎስና በአድሀሪው መንግሥት ጊዜ የተጀመረ አድሐሪ እቅድ ነው” የሚል ነበር::

በታገደበት ቀን ጋሼ አበራ በሥራው መደናቀፍ ከየአገሩ ለተለያየ ጉዳይ መጥቶ በሚተራመስበት በዋናው ጽፈት ፊት ለፈት ባለው አስፋልት ላይ ቆሞ “የአቡነ ቴዎፍሎስ አምላክ ይህን ግፍ ተመልከት” ብሎ የመረረ ልቅሶ አለቀሰ:: አቶ ቄርሎስ ቀሲስ ኃይለ ልዑልና እኔ የሱ ማልቀስ አሳዝኖን አንገታችንን ደፍተን ከበነው ካጠገቡ ቆመን ነበር።

ብዙ ሰዎች የዘመድ ሞት መርዶ ነግረነው የሚያለቅስ መስሏቸው እየመጡ ጠየቁን:: ጋሼ አበራ አሁንም ወደ ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ቢሮ ሄዶ አመለከተ፥ እገዳውን ባስቸኳይ እንዲያነሱ ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት ተደውሎ ተነገራቸውና እንቅስቃሴው እንደገና ቀጠለ:: በእቅዱ ላይ የደረሰው ይህ ሁሉ ተደጋጋሚ ፈተና፥ ለጋሼ አበራ የበለጠ ሞራል ሰጠው::

ጋሼ አበራ “አቡነ ቴዎፍሎስ፥ ያወጁት ቃለ ዓዋዲ በትክክል ከእግዚአብሔር የተቀበሉት በመሆኑ ‘ወአናቅጸ ሲኦል ኢይኄይልዋ’ ብሎ ጌታችን ለቤተ ክርስቲያን እንደገባላት ቃልኪዳን፦ ቃለ ዓዋዲውም ዘመን የማይሽረው ሆኖ  ከቤተ ክህነቱም ከጳጳሳቱም የሚገጥመውን ፈታና እያሸነፈ ከዚህ ደርሷል” አለ::

ቀጠለና “ከእንግዲህ የሚገታው ኃይል የለም:: ይሁን እንጅ ሥራውን ለማፋጠን ተጨማሪ ኃይል ስለሚያስፈልገን የወጣቶች ጉዳይ መመሪያን ከኛ ጋራ እንዲሰለፍ ጠይቄ ፈቃደኛ ሆነውልኛልና ነገ ከነሱ ጋራ ስለ እቅዱ ስለምንነጋገር ቀደም ብላችሁ ተገኙ” ብሎ ለቀሲስ ኃይለ ልዑልና ለኔ ነገረን:: ከሃይማኖት አበው ድርጅት ጋራ ጎን ለጎን እንዲሰራ በወቅቱ የተቋቋመዉ የወጣቶች ጉዳይ መመሪያም በዋናነትና በምክትል ሥራ አስኪያጅነት እንዲያገለግሉ የተመደቡት ነፍሳቸውን ይማርና አቶ ሐዲስ ተረፈና አቶ የማነ ብርሃን ተሾመ ነበሩ::

በሥራቸው የነበረውን የአጠቃላይ ጉባዔ አባላት በማስተባበር ተቀላቀሉን:: አቶ ሐዲስ ተረፈ፥ አቶ የማነ ብርሃን ተሾመና ቀሲስ ኃይለ ልዑል ገሪማ ለአቡነ ቴዎፍሎስ የነበራቸው ክብርና ፍቅር ጥልቅ ስለነበረ፥ አቡነ ቴዎፍሎስ ቢነድፉትም ፍጻሜውን ሳያዩ በመሞታቸው እያዘኑ፥ ለተዘዋዋሪው ቡድናችን “ባዩ” የሚል የውስጥ ስም ሰጡት:: “እኛም ማየት አለብን” የምትለዋን ሐዋርያዊት ትውፊት ተከትለው ብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ ያወጁትን ቃለ አዋዲ፥ በኋላ የነ እንጦንስን እውነተኛ ረድኤት ተቀብሎ ሩጫውን ጨርሶ ከንቱ የሆነውን ዓለማዊ ምኞት ርግፍ አርጎ ትቶ የተረሳውንና የተዳፈነውን ቃለ አዋዲ ቀስቅሶ ተግባራዊ ያደረጉላት ለቤተ ክርስቲያናችን ዳግማዊ ከሳቴ ብርሃን በመባል ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት በኋላ ፓትርያርክ ይሆናሉ ብለን ተስፋ አድርገን ነበር። ሳይሆን ከመቅረቱ ባሻገር አባራ በቀለ የደኩሙላት ቤተ ክርስቲያናችን  ዛሬ የደረሰችበትን  Schlosser የተባሉት አሜሪካዊ የአሜሪካን ሕብረተ ሰብ “Fast Food Nation” የሚል ምሳሌ ሰጥተው በገለጹበት አማናዊ ምስሌ የቤተ ክርስቲያናችንን መሪወች ሁኔታ ለማሳየት እሞክራለሁ::

የዛሬዋ ቤተ ክርስቲያናችን መሪወች ገጽታ

አቡነ ቴዎፍሎስ “እኛም ማየት አለብን” በሚል ውሳኔያቸው ሐዋርያት የተመኙትን ያገኙበትን ሐዋርያዊ ትውፊት ተከትለው፥ ቤተ ክርስቲያናችን ከፊውዳሉ ሥርአት ተላቃ “ማየት አለብኝ” ብለው ያወጁትን ቃለ ዓዋዲ በተግባር ለማዋል፥ ጋሼ አበራ በቀለ እየወደቀ እየተነሳ እያነባ እያለቀሰ የከፈለው መስዋዕት፥ ቤተ ክርስቲያናችንን ከመሳፍንቱ ሥርአት አላቆ፥ ጦም አዳሪ የነበሩትን ካህናት በኑሯቸው አሻሽሎ፥ በነዋየ ቅድሳት በኩል ከሚገጥማት ችግር ነጻ አውጥቶ እውነተኛውን ecclesiastical order ቢያሲዛትም፥ የዚህ ዘመን ጳጳሳት መነኮሳትና ካህናት “Fast Food Nation” አደርግናታል::

በዚህ መጽሐፍ በገጽ 123 ላይ “Aroma and memory are somehow inextricably linked. A smell can suddenly evoke a long -forgotten moment. The flavors of childhood foods seem to leave an indelible mark, and adults often return to them, without always knowing why.” የሚል ሐሳብ አገኘሁ:: ማለትም፦ ሽታና የማስታወስ ኃይል በማይለያይ ሁኔታ የተያያዙ ናቸው:: ሽታ ለረዥም ጊዜ የተረሳውን ትዝታ ይቀሰቅሳል:: የልጅነት ምግብ ከጭንቅላት የማይሰረዝ ምልክት ነው:: ለምን እንደሚያደርጉት መግለጽ በማይችሉት ምስጢር ተገደው፥ በትዝታው ተስበው ይመለሳሉ” ይላሉ:: እንዳሉትም በዚህ በፍልሰታ ሰሞን የሚደረገው ትዝታ በክርስቲያን ቤተ ሰብ ተወልዶ ያደገ ይቅርና በሌላ እምነት ቤተ ስብ ተወልዶ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ያደገ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ዛሬ በዘመኑ ጳጳሳት “Fast Food Nation የተደረገችው ቤተ ክርስቲያናችን ከልጅነቱ ጀምሮ ያስቀመጠችበት የማይለቀው ትዝታ አለበት:: ከዚህ ትዝታ በመንደርደር፥ የፍልሰታን ጾም ከመጀመራችን በፊት “ለምንድነው የምንጾመው” ብየ ጥቂት ሰዎችን ጠየኩ::

ብዙዎቹ እናት አባቶቻችን ሲያደርጉት ስላየንና ሐዋርያት ስለ ጾሙት ከሚል በቀር ሐዋርያትን እንዲጾም የገፋቸው “እኛም ማየት አለብን” የሚለውን የጾሙን መሠረት የነገረኝ የለም:: “ሕጻናት ለምን እንደሚያደርጉት መግለጽ በማይችሉት ምስጢር ተገደው፥ በትዝታው ብቻ በመሳብ ያደርጉታል” ብለው Schlosser ከገለጹት ጋራ ገጠመ:: በቦታ የሚርቁኝ በሐሳብ የሚቀርቡኝን ከቤተ ሰብ ተለይተው ሁለቱን ሳምንታት ለማሳለፍ በዝግጅት ላይ ያሉትን አንዳንድ ካህናት ጠየኩ፥ ሱባዔ በትዳር ለሚኖሩ ካህናት ተገቢ ነው:: ግን ቤተ ክርስቲያን የተነጠቀችውን ያጣችውን ሐዋርያት እንዳደረጉት “እኛም ማየት አለብን” በሚል ቆራጥ ምኞት የተንተራሰ መሆን አለበት::

ከሱባዔው ስንወጣ እንደ ሐዋርያት፥ እንደ አቡነ ቴዎፍሎስና እንደ ጋሸ አበራ ይዘነው የምንወጣው ሊኖረን ይገባል:: ሱባዔያችን ከዚህ ውጭ ከሆነ የዋጠውን መሸከም አቅቶት፥ የሚቀጣለው ተቃጥሎ፥ የሚወሐደው ተዋሕዶ አሮጌ ቆዳውን አራግፎ፥ ባዲስ ኃይል የሚውጠውን በመፈለግ ከሚምዘገዘግ ዘንዶ የተለየን አያደርገንም:: እንደ እውነቱ ከሆነ ብዙዎቻችን ባለንበት በዚህ ዘመን ልናደርገው የሚገባንን ነገር ሳናውቅ ቀርተን፥ ለማወቅ ሱባዔ የሚያስፈልግ አይመስለኝም::

በበኩሌ እንደ ጋሼ አበራ ወደ አገሬ ተመልሼ ያደረኩት ባይኖኝም፥ ባለሁበት በአሜሪካ ዞሬ ለሕዝብ የማካፈሉ እድሉ ባይገጥመኝም፥ በዘመኑ እውቀት የበሰሉ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ባዘጋጇቸው ድሕረ ገጾች በጽሑፍ ከማቀርበው የተለየ ተልእኮ የሚኖረን አይመስለኝም:: ካድርባይነት ከጥርጥርና ከፍርሐት መንፈስ ተላቆ፥ እምነትንና ድፍረትን ለማግኘት ከሆነ ሱባዔ መግባት ተገቢ ነው:: በፍርሐትና በጥርጥር በተወጠረ ጭንቅላት ሱባዔ ከብቶ፥ ባዶ ጭንቅላት ይዞ ከሱባዔ መመለስ ግን መንፈሳዊ በመምሰል ሕዝቡን ለማታለል ከሚደረገው ሸፍጥ የተለየ አይደለም::

በዚሁ ጉዳይ ላይ መነኮሳት በሱባዔው ውስጥ ያላቸውን ሚና ካንድ መነኩሴ ጋራ ተነጋገርን:: “ወአንተኒ መነኮስ እመ ኮንከ ሱቱፈ ምስለ አኀው በፍቅረ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ በ፩ዱ ልብ ወትፈቱ ትኩን ረድኦ ለእግዚእነ ወከመ ትትሁዌለቅ ምስለ ማሕበረ ሐዋርያት ንጹሐን ኩን መናኒ ዘበአማን ወኢትሄሊ ምንተኒ ዘሀሎ ውስተ ዝንቱ ዓለም ግሙራ ከመ ዚአከ ውእቱ ሕየንተ ኩሎሙ አኀው ዘአንተ ተሐድር ምስሌሆሙ በፍቅር” (ሃ.አ. ሰለስቱ ምዕት ፳፩፡፳፭) የሚለውን መመሪያ ላልሳቱ መነኮሳት፥ መጀመሪያ ሲመነኩሱ መላ ሕይወታቸው ለሱባዔ ለመስጠት እንጅ ለፍልሰታ ብቻ አይደለም:: ምን ጊዜም ሕይወታቸው ለሰቡዔ የተሰጠ በመሆኑ ከገጠር ከከተማ ወደ ገዳማቸው መጥተው ሱባዔ የገቡትን ማገልገል እንጅ ለፍልሰታው ሰሞን ሱባዔ አያስፈልጋቸውም:: በቆየሁባቸው ገዳማት ውስጥ የማውቃቸው እውነተኞች መነኮሳት፥ አሁንም በሌሎች ኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናት ያሉት መነኮሳት የሚያደርጉት ይህንኑ ነው::

በዘመናችን እንደ አሸን ፈልተው ዓለሙን የወረሩት መነኮሳት ግን “ይርሐቁ እምአንስት ወኢይቅረቡ ኀቤሆን ወኢይትነገሩ ምስሌሆን ወኢያውስእዎን ምንተኒ ግሙራ”(ፈ.ነ.፳፡፮) ከሴቶች ይራቁ ፈጽመው ወደሴቶች አይቅረቡ:: ቢአነጋግሯቸውም እንኳ ምንም ነገር አይመልሱላቸው:: የሚለውን ጥሰው በብዙ ሴቶች ተከበው የከተማ ሕወት የሚኖሩ ናቸው:: የከበቧቸው ሴቶች የሕግ ሚስቶች ስላይደሉ፥ ለባለትዳሮች የተጻፈው የሱባዔ ሥርአት እንደ ባለ ሕጎች ሱባዔ ግቡ አይባሉም:: በገዳም አይኖሩምና ለሱባዔ ወደ ገዳማቸው የሚመጡትን ክርስቲያኖች እንደ ገዳማውያን መነኮሳትም አገልግሉ አይባሉም::

የሚያደርጉት ሁሉ ስለተለወጠ የዘመኑ መነኮስትም ሕግ ካልተለወጠ በቀር ይህን ወይም ያን እንዲያደርጉ የሚጠቀስባቸው አንቀጽ የለም:: ወእመ ወጽአ እኁ እምኔቱ መኒኖ ሕገ ምንኩስናሁ ወሖረ ኀበ ሀገር ወብሔር ከመ ይንበር ህየ፥ ይኩን በመአርገ ሕዝባውን እለ ሀለው ውስቴታ ወኢደልዎ ሎቱ ከመ ይትመሰል በመነኮሳት ዘእንበለ አምሳለ ሕዝባውያን ለእመ ውእቱ ኢይክል ላዕለ ተጸውኖተ አርአያ ምንኩስናሁ ይከውን ሀሜት ኀበ ኩሎሙ መነኮሳት ወይሬሲ ሎሙ ስመ እኩየ”( ፍት.. አን ፲፡ ቁጥ ፬፻፭) ከመነኮሳቱ ውስጥ አንዱ ከገዳም ወጥቶ ከሕዝቡ ጋራ ተቀላቅሎ በገጠር በከተማ የሚኖር ከሆነ፥ ክህነቱን በመልቀቅ እንደማነኛውም ሰው የመኖር ነጻነቱ ሊነፈገውና ሊዘለፍበትም ሆነ ሊከሰስበት አይገባም:: ከመነኮሰ በኋላ ከገዳም ወጥቶ ከሕዝብ ጋር ተቀላቅሎ የሚኖር ከሆነ ግን የምንኩስናውን መሥመር በመሳቱ መነኩሴ መስሎ መኖር የለበትም:: መጽሐፈ መነኮሳቱ በተጻፈበት ዘመን በነበሩት የገጠር ከተማዎች ዉስጥ መኖራቸውን ሕገ ቤተ ክርስቲያን የሚቃወም ከሆነ፥ በዘመናችን በኢሮፕና ባሜሪካ ከተሞች ለሚኖሩት መነኮሳት የሚጠቀስላቸውና የሚጠቀስባቸው አንቀጽ የለም::

“ወኢትጸአል ወኢትትናገር ነገረ ሥላቅ ወኢትርግም ወኢትምሐል ግሙራ አላ ይኩን ቃልከ እመኒ እዎ እዎ፥ ወእመኔ አልቦ አልቦ”(ፈ.ነ.አ ፲) ማለትም፦ “ከሰው ጋራ አትጋጭ ተራ ነገርም ካንደበትህ አይውጣ፥ ፈጽሞ አትማል:: ቃልህ እውነት ለሆነ ነገር እውነት፥ ስሕተት በሆነ ነገር ሁሉ ስሕተት ከማለት አልፈህ ከሁለቱ የራቀ ዲፕሎማቲክ አትሁን”:: የሚለውን አልፈው “‘እኛም ማየት አለብን” የሚለውን ሐዋሪያዊ ቁም ነገር ረስተው የሕብረተሰብ ቀልብ በመሳብ ገንዘብ፥ ጥቅም፥ዝናና ክብር ለማግኘት በሚረዳቸው ነገር ላይ አተኮሩ:: (አንባቢ ከዚህ በፊት የጻፍኳቸውን ሁለት ጦማሮች: የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሃዶ ቤተክርስቲያን ከዉስጥም ከዉጪም የገጠማትን ፈተና ወይም http://www.medhanialemeotcks.org/pdf/fetena.pdf የሚለውንና ኢትዮጵያ በ‘ሶስት’ ፍካሬዎች ወይም http://www.medhanialemeotcks.org/pdf/FIKARE.pdf የሚለውን ይመልከት)::

የቤተ ክርስቲያናችን ልጆች በ 2002 ዓመተ ምህረት Memphis, Tennessee on November 16, 2002 Annunciation ግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተገኝተን የጋብቻቸውን ሥርአት እንድንፈጽምላቸው ከመአስባን ሊቀ ማእምራን አማረንና እኔን፥ ከመነኮሳት ደግሞ ነፍሳቸውን ይማርና አባ ደስታ ና አሁን ኢዮጵያ የገቡ መነኩሴ ተጋብዘን በዝግጅቱ ላይ አራታችንም ተገኘን:: የሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ባለቤቶች (ግሪኮች) በዝግጅቱ ላይ እንዲገኙ ተጋብዘው ስለነበር፥ ከሙሽሮች በፊት በሰአቱ ተገኙ:: ሙሽሮቹ ዘግይተው መጥተው ሥርአቱ ከመጀመሩ በፊት ወደኛ እየቀረቡ ሰላም ካሉን በኋላ፥ በደረታችን ያጠለቅነውን የጠፍር መስቀሎቻችን የት እንደተሰሩ ጠየቁን:: ቀጠሉና እነዚያ ሰዎች ለምን እንደናንተ ያለውን አላደረጉም? ብለው ስለነ አባ ደስታ ጠየቁን:: እነሱ የመነኩሴ ቄሶች ናቸው:: ስንላቸው የድንጋጤና የመደነቀ ፊት እያሳዩ “ከየት ገዳም የመጡ ናቸው? ብለው ጠየቁን:: ገዳም ስለሌለን “በከተማ የሚኖሩ ናቸው” አልናቸው:: ገዳም ከሌላችሁ እናንተስ ምንድናችሁ? ከየት ገዳም መጣችሁ? ብለው ጠየቁ:: “እኛ በትዳር ውስጥ ያለን እንጅ መነኮሳት አይደለንም” ስንላቸው የመገረም ገጽ አሳዩን:: እጅግ እየተገረሙ እናንተ ቄሶች ስትሆኑ ያደረጋችሁት መስቀል የገዳም መነኮሳት የሚያደርጉት ነው:: እነዚያ ደግሞ መነኮሳት ሲሆኑ ያደረጉት መስቀል በግሪክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መነኩሴም ቄስም ያልሆነ ማንም ሰው የሚያደርገው ነው፥ ለምንስ ይህ ሆነ” ብለው ጠየቁ::

ነፍሳቸውን ይማርና አባ ደስታ በውጩ ትምህርት የበሰሉ ስለነበሩ የሰዎችን ጥያቄ በሰሙባት ቅጽበት በደረታቸው የነበረውን መስቀል በቀሚሳቸው ውስጥ ደበቁት፥ አባ …. ግን የተካሄደውን ሁሉ ሊሰሙ ይቅርና በወርቅ ቀለም ቅብ በሩቁ የሚፈልቀውን የግሪክ መስቀል ለማሳየት በደረታቸው ላይ ያለውን የበለጡ አጉልተው ለማሳየት ሞከሩ:: ኧራ አባ በደረተዎ ያለውን መስቀል ጉድ እያፈላ ነውና እንደ አባ ደስታ እባከዎ ይደብቁት” ብንላቸው እንዲያውም የተናቁ መሰላቸውና የሌላቸውን ሁሉ ወኔ ሰብስበው ደረታቸውን ነፍተው አውደ ምሕረቱን ተቆጣጠሩት::

በኋላ እንደተረዳነው፥ የጠየቁን ሰዎች እነሱ እያዩ ባደጉበት አካባቢ ባለው ገዳም ውስጥ የሚኖሩ መነኮሳት ትህትናን ለማሳየት የሚያደርጉት መስቀል ከእንጨት ወይም ከጠፍር የተሰራ ነው:: የእኛን መስቀል ከመነኮሳት ጋራ ያገናኙት እያዩ ካደጉት ጋራ በማገናዘብ ነው:: ይህ አይነት መስቀል የኦሬንታል ቀሳውስት የሚያደርጉት ከገብጾች ያገኘነው ነው ስንላቸው ተረዱልን:: እኔ ከኢትዮጵያ እስከወጣሁባት ሰዓት ድረስ፥ ማንም የሚመነኩሰው ለግሉ መንኖ ሊጸድቅበት የሚደረግ የግል ነው፥ ክህነት ግን የሕዝብ ነው:: ማነኛውም ሰው እችላለሁ ካለ ሊመነኩስ ይችላል:: ስለዚህ ነው ሰዎች ወልደው አሳድገው ወደፋጣሪ ፊታቸውን ሲመልሱ የሚመነኩሱት:: ክህነት የሚሰጠው ግን ለሕዝባዊ የአልግሎቱ በቅቶ ሲገኝ ብቻ ነው:: በዚህም ምክንያት በክህነት እድሜ የቀደመ ሰው እያለ እሱ ካልፈቀደ በቀል፥ ለቡራኬም ሆነ ለማስተማር የሚቀርብ ቆሞስ ነኝ መነኩሴ ነኝ በሚል ስሜት ወደ ሕዝብ ራሱን ጋብዞ ማቅረብ ነውርና ክልክል ነበር:: እንዲህ የሚያደርግ መነኩሴም ፈጽሞ አይቼ አላውቅም ነበር::

Schlosser የተባሉት ሊቅ ስለ Fast Food Nation ሲገልጹ “Few of the people who built fast food empiresded college, let alone business school. They worked hard, took risks, and followed their own paths.”(Schlosser, page 6) ፈጣን ምግብ ቤት የመሰረቱት ጥቂት ሰዎች ርቀውና መጥቀው ስለንግድ ሊማሩ ይቅርና ወደ ኮሌጅ ሄደው የተሳተፉት እውቀት የላቸውም:: ነገር ግን የሚገጥማቸውን ነገር ሁሉ በድፍረት በመጣስ የሚፈልጉትን ለማግኘት የራሳቸውን ምንገድ ፈጥረዋል” እንዳሉት እኒህም ሰው ቆብ ባጠለቀ ላይ ሕዝቡ የሚሰጠውን ክብር በመጠቀም ለግል ኑሯቸው በመጓዝ ላይ ስለነበሩ በድፍረት መድረኩን ተቆጣጠሩት:: ምን እሳቸው ብቻ! Schlosser “Over the last three decades, fast food has inflitrated every nook and canny of Americn society.”(Page 3) ማለትም፥ ካለፈው ሰላሳ አመታት ወዲህ የፈጣን ምግብ ቤት በየስርቻው እየገባ ያሜሪካን ሕዝብ ተቆጣጠረው እንዳሉት፥ በአገራችንም በዚህ ዓለም ተሰማርቶ የኑሮ ውድድርኑ አሸንፎ ለመኖር ያቃተው ሁሉ ጎረምሳ፥ እውነተኛ የገዳም መነኩሴ እየመሰለ መጽሐፈ መነኮሳቱን ሳያውቅ ስለምንኩስና ሳይረዳ ሕሊናው ሳይመነኩስና ሳይመንን ቆቡን እያጠለቀ ቀሚሱን እያንዘረፈፈ ጢሙን እየከፈከፈ ታላቋን ቤተ ክርስቲያን በመውረር፥ የተሰደደውን ሕዝብ ፋስት ፉድ ወደ መሰለ ዜግነት እየለወጡት ነው::

የሚአስገርመው ደግሞ፥ ይህን የከፋ እቅድ ለፖለቲካ መጋረጃ አድርጎ የሚጠቀመው የዘመኑ አመራር መሆኑ እየታወቀ፥ በቅርቡ አቶ ስብሐት ነጋ (አቦይ ስብሐት) የተባሉ የአቶ መለሰ ጓድ በቤተ ክርስቲያኒቱ ዙሪያ የተሰለፉ ጳጳሳትና መነኮሳት የሚፈጽሙትን በደል ምንም የማያቁ መስለው በመደነቅ፥ “በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሚፈጠረው ሁሉ ዝብርቅርቅ ለምን በሌሎች አይታይም?” ብለው በጥያቄ መልክ መናገራቸው፥ በዚህ ዘመን አለን የምንባለውን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባል ሁሉ “Fast Food Nation” ነሕ ማለታቸው አይመስልምን?

ምሁራን በethics ክርስቲያኖች በእምነታቸው ይገደዳሉና Schlosser ከሁለቱ መንገዶች ባንዱ መገደድ “You should better off eating a carrot stick that fell in your toilet than one that fell in your sink” ( 221). ብለው ተናገሩ:: ማለትም፦ “ከወጥ ቤት እቃ ማጠቢያ ላይ የወደቀውን ከመብላት፥ ከሽንት ቤት የወደቀውን የካሮት ቅንጣት መብላት ይሻላል” በማነኛውም መንግድ ተፈትኖ ወድቆ ከታየው ሲኖዶስና (አንባብቢ ከዚህ በፊት የጻፍኳትን ጦማር ከገጽ 12-14 የሚቀጥለውን በመጫን ያንብቡ http://www.medhanialemeotcks.org/pdf/telsem-be-dc-debtera.pdf ) ጵጵስና የሚወጣውን መርሆ ከመቀበል ራሱን እስኪያጸዳ ድረስ ከማነኛውም ጳጳስ ነኝ መነኩሴ ነኝ እያለ ከሚመጣ ግለ ሰብ ገለል ማለቱ አማራጭ የሌለው ይመስለኛል::

ይህን ስል አንባቢ እንዲረዳልኝ የምፈልገው ክርስቶስ ከአስመሳዮች ጋራ አለመተባበሩን ለመግለጽ እንጅ፥ ከተዋህዶ ነገረ መለኮትና ከቀኖናችን ገለልተኞች ነን በማለት የሚደረገውን ግፍና ስሕተት አንይ አንስማ፥ ዝም እንበል አንናገር ማለቴ አይደለም:: (ከአሁን ቀደም ‘ገለልተኛ’ በሚል ርዕስ የጻፍኩትን ጦማር እዚህ ላይ ወይም ttp://www.medhanialemeotcks.org/pdf/geleltegna.pdf በመጫን ያንብቡ):: “It smelled like someone in the room was flipping burgers on a hot grill.” ማለትም፥- እየተጠበሰ በመገላበጥ ላይ ካለው   burger የሚነሳ ሽታ የሸተተኝ መስሎኝ ነበር” እንዳሉት፥ የዘመኑ ጳጳሳትና መነኮሳትም እንደሚሸት Hamburger እየተገለባበጡ የምንኩስና ሽታና መነኩሴ መስሎ በመቅረብ የሚያፈልቁት ባዶ የከተማ ጮሌነት ንግግር ክርስትናንና ዜግነት ወደ ፋስት ፉድ መሳይ እየለወጡት ነው::

ምንም እንኳ በየአካባቢው የተፈጸመ ቢሆንም በከንሳስ ከተማ የተፈጸመውን ለማስረጃ እጠቅሳለሁ:: ካሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ሄደው ጳጳስ የሆኑ አንድ መነኩሴ፥ በመጀመሪያ የአቡነ ጳውሎስ ወኪል ነኝ ብለው ወደ አሜሪካ መጡ:: ከጥቂት ጊዜ በኋላ አቡነ ጳውሎስን ካዱና፥ ከአቡነ ይስሐቅ ጋር ተሰልፈው አቡነ ጳውሎስንና በሳቸው የሚመራውን ሲኖዶስ እየዘለፉ እውነተኛው አባት አቡነ ይስሐቅ ናቸው በማለት አጥብቀው ሰበኩ:: ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ነገረ መለኮት እምነት ውጭ የሆነውን የሮማ ካቶሊክንች ትምህትና እምነት (http://www.youtube.com/user/medhanialemeotcks#p/u/12/U2fplUxOgXc ) በመካከላችን ረጭተው ከመለያየታችን በፊት፥ እኒህ መነኩሴ ከአቡነ ይስሐቅ ጋራ ወደ ከሳንሳስ ኪዳነ ምሕረት መጥተው ከላይ የገለጽኩትን ተናገሩ::

ስለአቡነ ጳውሎስ ስሕተትና ስለ ሲኖዶሱ ብቃት የሌሽነት በመጀመሪያ የሰማሁት ከሳቸው ነው:: ከጥቂት አመታት በኋላ፥ ለፓትርያርክነት ብቃት የላቸውም እያሉ ሲከሷቸው ወደነበሩት አቡነ ጳውሎስና አይታመንም እያሉ ወደ መሰከሩበት ሲኖዶስ እንደገና ተገልብጠው፥ አሁን በአቡነ ጳውሎስ ጳጳስና ተሾሜያለሁ፥ በሳቸው ለሚመራውም ሲኖዶስ አባል ነኝ፥ ስለዚህ በአቡ ጳውሎስ ሥር በማይተዳደርና በሲኖዶስ ሥር ያልሆነ ሁሉ ቤተ ክርስቲያን የተሳሳተ ነው:: ስለዚህ ‘ቤተ ክርስቲያን ማለት የከንሳስ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርቲያን ብቻ ናት’ እያሉ በዚያው መድረክ ላይ ቆመውም ተናገሩ::

ከዚህ ቀደም ከአቡነ ይስሐቅ ጋራ ከንሳስ ላይ መጥተው ስለ ውስጡ ሲኖዶስና ስለአቡነ ጳውሎስ የተናገሩትን ሁሉ ገልብጠው በዚሁ መድረክ ላይ ሲናገሩ ሕዝቡ ይታዘበኛል ብለው አያስቡም? አያፍሩም? እጅግ ታዘብኩዎ ብየ በስልክ ለጠየኳቸው የሰጡኝ መልስ “እርሰዎ እውነትን አለቅም ብለው ደርቀው ይቀራሉ እንጅ፥ ሕዝቡና እኛ እንደሆን ተስማምተናል:: ሕዝቡ ጵጵስናውንና ቆቡን ነው የሚከተለው እንጅ እውነቱን ፈልጎ እውነቱን ሰምቶ ንስሐ ገብቶ ለመጽደቅ ብሎ ወደ ቤተ ክርስቲያን አለመምጣቱን መረዳት እንዴት ተሳነዎ? ይህ ባይሆን ኖሮ የከንሳስ ሕዝብ አቡነ ማትያስን የት ያውቃቸዋል? አንድ ቀን እንኳ መጥተው ጎብኝተዋቸው አያውቁም:: እርሰዎ እውነቱን እየተናገሩ፥ እኔ እየሠረኩና እየዋሸሁ እያየ ጳጳስ በመባሌ ብቻ፥ ከፊቱ ላይ ነፍስ ብገድም ዝም ብሎ ከመከተል በቀር እጠይቀኝም” አሉና፥ ይልቁንስ ወደ አዲስ አባበ አብረን እንሂድ። ወደ ሲኖዶሱ ለመግባት አያስቡ እኛ እጀዎን ይዘን እንገባለን፥ በውጭ ሆነው የሚጽፉትን ያቁሙና ከዚያ ሄደው ከሊቃውንቱ ጋራ ተነጋግረው ከተመለስን በኋላ አብረን መሥራት እንጀምራለን” አሉኝ:: “መጀመሪያ እናንተ ወደ ከንሳስ መጥታችሁ ከሕዝቡ ጋራ ተነጋገሩና ስምምነት ከተደረሰ በኋላ የምትሉት ይደረጋል” ስላቸው፥ “የምትተኩሰውን ጥይት ለሕዝቡ አቅመህ በኛ ላይ ልታስተኩስብን ነው” በሚለው ቃላቸው ውይይታችን ቆመ::

ታዲያ እነዚህ ምንኩስናውንና ጵጵስናውን የFast Food መጥበሻ grill, ሕዝቡን Fast Food Nation አላደረጉትም? ይህ የነ አባ ንግግር Schlosser ስለ Fast Food Nation በጻፉት ገጽ 129 ላይ “But when I opened my eyes, there was just a narrow strip of white paper and small flavorst” ካሉት ጋራ ገጠመብኝ:: “አይኔን በደንብ ከፍቼ ስመለከት፥ ሲጠበስ እሱን የመሰለ ሽታ የሚአመነጭ ነጭ ወረቀት ሲአቃጥል አየሁ” እንዳሉት የዘመኑ ጵጵስናና ምንኩስና፥ በሩቁ ሲታዩ እውነተኛ ይመስላሉ ቀርበው የሚያደርጉትንና የሚናገሩትን ስንሰማቸው ግን የፋስት ፉድ ምግብ ቤት ለማስመሰል ከሚጤሰው ወረቀት የባሱ የነ እንጦንስን ምንኩስናን፥ የነ ቅዱስ አትናቴዎስን ጵጵስና በማስመሰል ስሜት እያጤሱ ዓለማዊውን ኑሯቸውን በመቅጨት ላይ ናቸው:: ተመልካችና እውነተኞችን ክርስቲያኖች ሊአሳስባቸው የሚገባ ነገር አለ::

Schlosser እንዳሉት “The fast food chains, understandably, would like the public to belive that the flavors of their food somehow orginate in theirrestuarant kichens, not in distant factories run by other firms.”(120) ማለትም “የፈጣን ምግብ አዘጋጆች፥ የፈጣን ምግብ መአዛ በሌላ ድርጅት ሆን ተብሎ በማስመሰል የተሰራ ነው:: ይሁን እንጅ ከማብሰያ ቤት ውስጥ ከሚዘጋጅበት ምድጃ የሚነሳ የእውነተኛው ምግብ ሽታ እንደሆነ ሕዝቡ ያለ ጥርጥር አምኖ እንዲቀበለው ይጥራሉ” እንዳሉት፥ ከዚህ በኋላ የሚነሳው ትውልድ ከውስጡ የሚመዝንበት ኢትዮጵያዊና ቀጥተኛው ኦርቶዶክሳዊው ሚዛን ስለሌለው ዛሬ እኒህን ከመሰሉ ሰዎች የሚሰማውንና የሚያየውን ሁሉ ከቤተ ክርስቲያቱ መመሪያ እንደፈለቀ አርጎ እንዳይቀበለው ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋና ለሃይማኖቱ የሚቆረቆር ክርስቲያን ሁሉ መታገል አለበት::

Schlosser ስለ አሜሪካ ሕዝብ Fast Food Nation ሆነ እያሉ በጮሁበት ዘመን፥ “The Reverend Robert Schuller founded the nation’s first Drive-in Church, preaching on sunday morning at a drive- in movie theater, spreading the Gospel through the little speakers at each parking space, attracting large crowds withe slogan “worship as you are. . .in the family car”.(19) ማለትም፡- ቄስ Robert H. Schuller የዘመኑን ባሕል በመከተል በየእሁዱ ጧት የሚሰብክበት nation’s first Drive-in Church, አቋቋመ:: በትያትር፥ በፊልም፥ በመኪና መቆሚያወች ሁሉ ትንሽ ቃል ማጉያ በመጠቀም፥ በየቤትህና በየመኪናህ አምልክ በሚል መፈክር የሰፊውን ሕዝብ ሕሊና የሚስብ ንግግር ማሰራጨት ቀጠለ”. በዚህ መርሆ የተመሰረቱት ሁሉ ከ50 ዓመት በኃላ የበለጠ ትርፍ ለማግኘት በመጣደፍ ላይ ናቸው::

[በሰፊው ለመረዳት ይህንን ይጫኑ ሰchuller’s Crystal Cathedral may be reborn as Catholic http://www.usatoday.com/news/religion/2011-07-23-Crystal-Cathedral-Catholic_n.htm ] ከላይ በተጠቀሰው በRobert Schuller በሚመሳሰል ሁኔታ የዘመኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ.ክ. መነኮሳትና አንዳንድ ሰባኪዎች የሲኖዶስ አባላት ነን የሚሉ ጳጳሳት ሳይቀሩ፥ ከቤተ ክህነት ከሚከፈላቸው ሌላ ገቢ ለማግኙት በሚያደርጉት ስግብግብ ባሕርያቸው፥ አካል ነን ከሚሉት ሲኖዱስ የተለየ፥ የሰየሟቸውን ፓትርያርክ ታማኝነት በማሳጣት የሚሰብኩበት ቤተ ክርስቲያን በየቦታው መሠረቱ::

እኒህ ሰው “The impact of McDonald’s on the way we live today is hard to overstate.The Golden Arches are now more widly recognized than the cheristians cross.”(5) ሁኔታው እጅግ ርቆ ከመሄዱ የተነሳ ነገሩን አጋነን የምንናገርበትን ቃል ሁሉ በመያዙ አጋነን የምንገልጽበት ቃላት የሉንም:: እንዲያው በጠቅላላው የማክዶናል ወርቃማው የቀስተ ደመና ምልክት ከክርስትና ምልክት መስቀል ይልቅ በስፋት እያየለ መጥቷል” እንዳሉት፦ የክህነት የመንኩስና ልብሱ ሁሉ ቀለሙ የስፌቱ አሰራር የመስቀሉ አደራረግና አያያዝ ራቁትን የተሰቀለውን ክርስቶስን እየሸሸ ወደ አክተሮች ፋሽንነት እየተለወጠ ነው:: እንዲያውም አልፎ ተርፎ ባንድ ወቅት አውደ ምሕረት ላይ ቆሞ፥ “ይህ በእጄ የምታዩት መስቀል በሽልማት የተሰጠኝ የሰማዕቱ ያቡነ ጴጥሮስ መስቀል ነው” ብሎ ተናገረ ተብሎ “ኧረ እንደምን ያለ ድፍረት ገጠመን? ኧረ ለመሆኑ እሱ ማነውና የታላቁን ያቡነ ጴጥሮስን መስቀል ተሸላሚ ሆነ? ሸላሚውስ እንደምን ያለ ሰው ነው? ብሎ የዲሲ ዙሪያ ሕዝብ ቅሬታውን ያሰማበት ወቅት ነበረ:: ታዲያ በኛ ዘመን የሰማዕቱን የአቡነ ጴጥሮስን መስቀል ሸላሚና ተሸላሚዎች ካሉ የኢትዮጵያን ህዝብ Fast Food Nation ያደረጉ በመሆናቸው የታሪክ ተወቃሾች አልሆኑምን?

እንዲያውም አልፎ ተርፎ ባንድ ወቅት አንድ የሰንበት ተማሪ አውደ ምሕረት ላይ ቆሞ፥ “ይህ በእጄ የምታዩት መስቀል በሽልማት የተሰጠኝ የሰማዕቱ ያቡነ ጴጥሮስ መስቀል ነው” ብሎ ተናገረ ተብሎ “ኧረ እንደምን ያለ ድፍረት ገጠመን? ኧረ ለመሆኑ እሱ ማነውና የታላቁን ያቡነ ጴጥሮስን መስቀል ተሸላሚ ሆነ? ሸላሚውስ እንደምን ያለ ሰው ነው? ብሎ የዲሲ ዙሪያ ሕዝብ ቅሬታውን ያሰማበት ወቅት ነበረ:: ታዲያ በኛ ዘመን የሰማዕቱን የአቡነ ጴጥሮስን መስቀል ሸላሚና ተሸላሚዎች ካሉ የኢትዮጵያን ህዝብ Fast Food Nation ያደረጉ በመሆናቸው የታሪክ ተወቃሾች ናቸው “Most Americans have forgoten what real beef tastes like.”(257) ማለት Fast Food ብዙዎችን አሜሪካውያን የእውነተኛው የሥጋ ጣዕም እንዲረሱት አድርጓቸዋል እንዳሉት፥ ዛሬ በዘመናችን አገራችንን በሚመራት ድርጅት የተዘጋጀው ተልእኮ የኦርቶዶክስ አማኞችን ከጠራው ኦርቶዶክሳዊ እምነትና ትምህርት አስለቅቆ ከፕሮቴስታንታንና ከሮማ ካቶሊክ የሰሙትን እያጠራቀሙ፥ አሉባልታውንና ሐሰቱን እየለቃቀሙ ስለለቀቁበት፥ የኦርቶዶክሱን ከሌላው፥ እውነቱን ከሐሰት ለመለየት አቅቶታል::

“Fast food has played a more central role. By tracing the diverse influences of fast food I hope to shed light not only on the workings on an important industry, but also on a distinctively American way of viewing the world.”(pp. 9) ፈጣን ምግብ ብዙ ማእከላዊ ሚና ተጫወተ:: ፈጣን ምግብ የተጫወተውን የተለያየ ሚና በመመርመር ስንከተል በዋና ድርጅቶች ተቀጣሪዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በመላ አሜሪካ ላይ የዘረጋውን የርእዮተ ዓለም ጠለሸት አሻግረን እንመለከታለን”:: በአራችን ይህ ዘመን የፈጠራቸው የፖለቲካ ሰዎች በቀጠሯቸው አስመሳይ ሰባኪዎች፥ ጳጳሳትና የመነኮሳት ቄሶች ላይ ያስቀመጡት ተጽእኖ በነሱ ላይ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያውያንና ወደፊት በሚመጣው ትውልድ አዕምሮ ላይ ጥሎት የሚያልፈው መጥፎ ልምድ ለማስወገድ እስኪያቅት ድረስ ወጣቱን እየተወሐደው ነው::

በዚህ መንገድ ሰርጾ የገባውን ለማስለቀቅ፥ “the longer carcass remains on the out rail, the harder it is to clean. With every passing minute, bacteria grows more firmly and difficult to kill.” (216) የሞተው አካል ሳይጸዳ ከቆየ፥ ለማጽዳት ያስቸግራል፡ በምታልፈው ምንት ውስጥ ነፍሳት የበለጠ በመጠንከር ያድጉና ለመግደል ካቅም በላይ ይሆናሉ:: ይህንንም ካካባቢየ ሳልርቅ የተረዳሁት ነገር ነው:: በከንሳስ ከተማ የኪዳነ ምሕረትን ቤተ ክርስቲያን መሥርተን ለሰባት አመት ከቆየሁ በኋላ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነገረ መኮት ምንም ግንዛቤ የሌላቸው ቁጥር ስፍር የሌላቸው ሰዎች ከመንጠቃቸው በላይ፥ እነሱን ማጽዳት ይቅርና መላ ኦርቶዶክሶች የሰጡንን ሕንጻ ጥለንላቸው ከከተማ እንድንጠፋ ከፍተኛ ዘመቻ እያካሄዱብን ነው::

“Widely employed at fast food restaurants are the young and the poor are also responsible for much of the nation’s violent crime.”(84) በፈጣን ምግብ ቤት የሚቀጠሩት ወጣቶች ድሆች ናቸው:: በኅዝቡ መካከል ለሚፈጠረው ወንጀል ሁሉ ተጠያቂ የሚሆኑት እነሱ ናቸው:: እንዳሉት ከላይ ያሉት መሪዎች የወጣቱን ጫጫታ ለፖለቲካቸው ሽፋን  ከመጠቀማቸው አልፎ፥ እራሳቸው ለሚፈጽሙት ጥፋት ወጣቱን ተጠያቂ ለማድረግ የሚያደርጉትን ሙከራ የተረዳ ዜጋ ሁሉ ሊአወግዛቸው ይገባል::

“The aim of most children’s advertising is straight forwad: get kids to nag thier parents to buy the fast food” በልጆች ላይ የተነጣጠረ ማስታወቂያ፥ ልጆች ወላጆቻቸውን በመወትወት እየጎተቱ ያዘጋጁትን ፈጣን ምግብ እንዲገዟቸው እንደሆነ ግልጽ ነው” እንዳሉት፥ ስለጵጵስና የተጻፉትን ማር ይስሐቅ፥ መንፈሳዊ አረጋዊና ፊልክስዩሰ ተባሉትን መጻሕፍት አንብበው ምንኩስናው የሚጠይቀውን ብቃትና ኃላፊነት ሊረዱ ቀርቶ፥ ክርስቲያናዊ መጠነኛ እውቀትና ተመክሮ የሌላቸውን ጎረምሶች በሰፊው በማሰማራት ህዝቡን እየወተወቱ የፍላጎታቸው ተከታይ ለማድረግ ትልቁ አላማቸው ነሆነ:: ለዚህ አላማ የተሰለፉት ሁሉ “Today the nation’s fast food chains are marketing their products in pablic schools through conventional campaigns , classroom teaching materials, and lunch-room franchises, as well as a number of unorthodox means.”( page 52) ዛሬ የተቆላለፉት የፈጣን ምግብ ድርጅዮች፥ የምግብ ሸቀጣቸውን በጠነከረው ማስታወቂያቸው በትምህርት ቤቶች እያራገፉት ነው:: የትምህርት መስጫ ክፍሎች፥ ለምግብ ብቻ የተዘጋጁት ቤቶችና የቀሩት ሁሉ ከቀጥተኛው መስመር የወጡ የትምህርት መሣሪያዎች ሁሉ ከቀጥተኛ አላማቸው ወጥተው ለዚህ ንግድ ወደ መሳሪያነት ለውጠውታሉ” እንዳሉት በመላ ኢትይጵያ ካሰራጩት የባሰ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩበት አገር ሁሉ በመላክ ከኦርቶዶክስ ትምህርትና ከክትርስትና መመሪያ ውጭ የሆነውን ሸቀጣ ሸቀጥ ወሬያቸው ማረገፊያ አድርገውታል:: Schlosser የተሰማቸውን የታያቸውን ሁሉ ከገለጹ በኋላ መፍትሔውንና የተሻለውን ነገር ለአሜሪካ ሕዝብ ከዚህ በታች እንደማቀርበው ሳይጠቁሙ አላለፉም::

መፍትሔው

መፍትሔውን ማን ያምጣው? ማን ይጀምረው? እንዴትስ ይጀመር የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል:: Schlosser የተባሉት አሜሪካዊ በአሜሪካ ዙሪያ ተፈጸመ ብለው የገለጹትን ችግር ለመፍታት ከሰማይ መላክ አልመጣም:: ወይም ከውጭ የባእድ ጠበብቶችንም አልጠየቀም::

“It is our responcibility to make it clear that schools here to serve children, not commercial interest,”(55) ማለትም፥ “ ትምህርት ቤቶች ልጆች የሚማሩበት እንዲሆኑ የመርዳት፥ የንግድ ፍላጎት መፈጸሚያ እንዳይሆኑ ደግሞ የማስቆም ሙሉ ኃላፊነት አለብን” ብሎ የተንቀሳቀሰው አስቀድሞ ተመስርቶ ስሕተቱ ሁሉ ሲካሄድ ሲታዘብ የነበረው የትምህርት ቦርድ ነው::

በቤተ ክርስቲያናችንና በሃይማኖታችን ላይ ለሚፈጸመው በደል ከዲኖሚኔሽንና ከግል ጥቅም እስረኝነት ከተላቀቁ ጥቂት ወገኖች በቀር ግን በተቀናቃኝነት የተፈጠሩ ድርጆቶች ሁሉ ቢተባበሩብን እንጅ፥ ቤተ ክርስቲያኗ ተበደለች፥ መሠረታዊ ዶግማዋ ተቃወሰ ብለው ከኛ ጋራ አይቆሙም:: በቤተ ክርስቲያኗ ላይ ብቻ ለሚመጣው ችግር፥ እኛ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አባላት በተለይም ነገረ መለኮቱን ጠብቀን እናስጠብቃለን ብለን የገባን ሰዎች፥ አላማዋን እንዳትስት ተልእኮዋን እንዳትዘነጋ ነቅተን የመጠበቅና የማስጠበቅ ኃላፊነቱ የኛ ነው::

በሥጋዊው አስተዳደር የሚድርሰው በደል በእምነት በማይመስሉን ዜጎች ሁሉ ላይ እኩል ስለሚፈጽም፥ ለጩኸታችን አድማቂና አጃቢ ይኖረዋል:: የቤተክርስቲያንና የሃይማኖታችን ጉዳይ የግላችን ይሁን እንጂ በጠቅላላው ፍጥረት ላይ ለሚደርሰው ሥቃይ፥ ሃይማኖት ዘርና ጎሳ ሳንለይ ለሁሉም እኩል እንድንጮኽ በእንግድነት በቀርቡ ወደ አገራችን ከገቡትም የሃይማኖት ድርጅቶች የበለጠ ኃላፊነትና አደራ በእኛ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያ ካህናት ላይ አለብን:: ቤተ ክርስቲያናችን በመሠረታዊ ዶግማዋ ከምትመስላቸው አብያተ ክርስቲያናት ሳትለይ፥ የሞራል የፍቅርና የኅብረት ምንጭነቷን ጠብቃ ለሕዝቧ ምስክርና አለኝታ እንድትሆን እንጅ፥ በጠበንጃ ኃይል እየገለበጠ ለሚመጣ ሁሉ የተሳሳተ ፖለቲካ መጋረጃና መሣሪያ እንዳትሆን የመጠበቅና የማጽዳት ኃላፊነት አለብን በሚል ቆራጥ ውሳኔ ይዞልን የሚመጣ አካል ከውጭ አንጠብቅም::

አቡነ ቴዎፍሎስ እኛም ማየት አለብን ብለው የጀመሩትን ሐዋርያዊ ትውፊት፥ በተግባር ያዋሉት ዲቁና፥ ምንኩስና፥ ቅስናና ጵጵስና ያልነበራቸው አባ አበራ በቀለ ናቸው:: ከእንግዲህ ወዲህ ከጳጳስ፥ ከመነኩሴ፥ ከቄሶችና ሲዋሹና ሲቀጥፉ በማየት ከታዘብናቸውም አዛውንቶች መፍትሔ የሚጠብቅ ካለ፥ እየተካሄደ ያለው ጥፋት እንዲቀጥል የሚፈልግና የቤተ ክርስቲያናችንን ታሪክ ያልተረዳ ነው:: ከውሸት ከማስመሰል፥ ከክፍለ አገር መከፋፈልና አድላዊነት ተላቆ፥ ቤተ ክርስቲያኒቱን የስሜቱ መግለጫ ሳያደርግ እንደ ጋሼ አበራ የጽድቅ ዝናር ታጥቆ፥የጽድቅ ጥሩር በራሱ ደፍቶ ከመጣ እግዚአብሔር ሊጠቀምበት ይችላል::

ሐዋርያት ቁጭ ብለው ክርስቶስን አየሁት ብሎ ለክርስቶስ ክብር ተቀጥቅጦ የሞተው ለአስተዳደር የተመረጠው እስጢፋኖስ ነበር:: ሰማእታት የምንላቸው እነ ቅዱሳን ጊዮርጊስ ጳጳስ መነኩሴና ቄስ ዲያቆን አልነበሩም::ጋሼ አበራም ከምዕራቡ በቀሰመው ትምህርት እኛን እየቃኘ፥ ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ጠቅላላ ሁኔታ ግን እኛን ተላላኪዎቹን ሳይንቀን በዚህ ጉዳይ ሊቃውንት አባቶች ምን ይላሉ? እያለ ይጠይቅ ነበር::

Lynne McTaggart የሚባሉት ሊቅ The Field: The Quest for the Secret Force of the Universe በሚለው መጻፋቸው የQuantum Physics እንደነ Albert Einstein ያሉት ሊቆች የሚሉትን ጠቅለል አድርገው ሲያብራሩ “This energy exchange is analogous to loaning someone a penny: you are a penny poorer, he is a penny richer, until he returns the penny and the roles reveres. This sort of emission and reabsorption of virtual particles occurs not only among photons and electrons, but with all the quantum particles in the universe.” (The Field page 23) ብለው እንደ ገለጹት “ኃይል ባንዲት ሳንቲም ብድር ምሳሌ ሊገለጽ ይችላል:: አንተ አንዲት ሳንቲም የሌለህ ደሐ ነህ:: ሌላው ደግሞ እስኪመልሳት ድረስ ያንዲት ሳንቲም ባለጸጋ ነው::ይህ አይነት የተፈጠሮ መስጠትና መቀበል በብርሃን ፍንጣቂና በelectrons ብቻ የተወሰነ አይደለም:: በዓለማችን ባለ በማነኛውም ፍጥረት የሚከናወን ነው::

የቤተ ክርስቲያናችንን ችግር ፈትቶ፥ ኃይሏ ሳይቀነስ ቁጥሯ ሳያንስ ለሚቀጥለው ትውልድ ለማሻጋር፥

ከእህሉ ሁሉ ጤፍ ታንሳለች፥

ወድቃ በስብሳ ትነሳለች፥

የአዳም ልጅ ሁሉ ሰነፈና፥

ወድቆ ቀረ አሉ በጎዳና

ያዳም ልጅ ሁሉ አትስነፍ፥

ጽድቅ እየሠራህ እለፍ”

እያሉ በዚህ ፍልሰታዋ ሰሞን እናቶቻችንና አባቶቻችን በየመንደሩ በየደብሩና በየገዳማቱ የሚያንጎራጉሩትን ማስተዋል ይጠበቅብናል። ባንድ ወቅት “በሊቃውንት ሌሎች ሊቃውንት በመጻሕፍትም ሌሎች መጻሕፍት ተተክተዋል” ተብሎ  በድፍረት  የተነገረው እንደሚያረጋግጠው የተዋሕዶ መሠረታዊ እምነትን ተናውጾ ግልብነትን፥ ገለፈትነትን፥ ራስ ወዳድነትን የሚተካ ትምህርት ለወጣቱ እየተሰጠ ነው::

ቤተ ክርስቲያናችንን እነዚህ ከመሰሉ ሰዎች ማላቀቅ የሚችሉት፤ የጤፏን ወድቆ መነሳት እንደጋሸ አበራ የተረዱ፥ ከውጭ በተማሩት ትምህርት እያገለገሉ የቤታችንን ነገረ መለኮት በማጥናት በትሕትናና በተሰበረ ልብ ወደፊት ለመምጣት ፈቃደኞች የሆኑ ብቻ ናቸው::

“Teenagers should be rewarded, not harmed, by the decision to work after school. And if the nation is genuinely intersted in their future, it will adequately fund their education, instead of inviting advertisers into the schools.”(Schlosser 262) እንዳሉትም፥ ማለትም፥ ያገሪቱ ዜጋ ወደፊት ለሚመጣው ትውልድና ለወደፊቷ አሜሪካ እውነተኛ ጠቃሚ ምኞት ካለው፥ ወጣቱ ትውልድ ከትምህርት ሰዓቱ ውጭ ባለው ጊዜ ዘለቄታ በሌለው ፋስት ፉድ ካምፓኔ ተቀጥሮ መሥራቱ እንደ ወንጄል ታስቦ ከመክሰስ፥ ከመውቅስና ከመቅጣት ይልቅ፥ በሥራ ፈቃደኝነቱ መመስገንና መሸለም አለበት:: http://www.slowfoodusa.org/ የሚባል ሕዝባዊ እንቅስቃሰሴ በEric Schlosser ምክርና ተግሳጽ መሰረት በ ፋስት ፉድ አቅጣጫውን የሳተውን ዜጋ ወደ ጤናማ ዜጋነት ለመለወጥ በመጣር ላይ ነው::

እኛም ይህን ቆራጥ ምኞት እንደምሳሌ በመጠቀም በዚህ መንግስት ወደ ፋስት ፉድ ዜጋነት የተለወጥውን ትውልድ ወደ ጤናማ ኢትዮጵያዊነት ተለውጦ ለማየት የሚያስቸለንን እቅድ መዘርጋት አለብን:: በተለይም ለታሪክና ለቅርስ ቆምኩ ብሎ ራሱን በውጭ ያዘጋጀው በቅርቡ በአሜሪካ ዙሪያ የተፈጠረው የወጣቶች ድርጅት የዚህን ኃላፊነት የሚሸከም አካል በሥሩ የመፍጠር ታሪካዊ ሞራላዊና ቅርሳዊ ኃላፊነት እንዳለበት ሊያስብበት የሚገባው ይመስለኛል:: ፊደላችን አስደናቂ ቅርሳችን እንደሆነ ሁሉ፥ መሠረታዊ ዶግማችንም ቅርሳችን ነውና በየዘመኑ በተፈጠሩ ጠልሰመኞች መናጋት የለበትም:: አምነን የምንከተለው የተዋሕዶው ዶግማ ይቅርና፥ ቀደም ብሎ ወደ አገራችን ገብቶ ሩቅ ዘመን የቆጥረው የወገኖቻችን እምነት ኢትዮጵያዊ ታሪክ ሆኗልና ዶግማውን ማንም ሰው ድንገት መጥቶ ሊለውጥ ቢሞክር፥ እኛ እንጸድቅበታለን ብለን ባናምንበትም በቅርስነቱ የመጀመሪያ ገጹን ሳይለውጥ እንዲቀጥል ምኞታች ሊሆን ይገባል:: የተዋሕዶ እምነት ተከታይ ነኝ የሚል ኢትዮጵያዊ ይቅርና፥ እጸድቅበታለሁ ብሎ ሌላ ዶግማ በመከተል ላይ ያለ ዜጋ ሁሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ ዶግማዋን መለወጥ የለባትም ተብሎ የሚሰማውን ድምጽ የመደገፍ ኃላፊነት ሊሰማው ይገባል::

የፍልሰታ ጾም ትንሿ የጤፍ ፍሬ በውስጧ የተሸከመችውን ሕይወት፥ ፈርሳ በስብሳ ለሚመጣው ዘሯ ለማቀበል በምታልፍበት ሁሉ ውጣ ውረድ አንጻር፥ የሰው ዘሮች እኛም ከናቶቻችን ማሕጸን ከወጣንባት ደቂቃ ጀምሮ እንደ ጤፏ ቅንጣት እየወደቅን እየተነሳን አድገን፥ እኛነታችንን ለሚቀጥለው ዘሮቻችን ለማቀበል በዚህ ምድር ላይ መዘራታችንን የምንመረምርበት የጥሞና ወቅታችን ናት:: መንፈሳችን ከሥጋዊ ስሜትና ፍላጎት ርቆ ያጣነውን ፈልጎ ለማግኘት የሚሰማራበት ወቅት ናት:: የጥንት ኢትዮጵያዊያን በጤፏ ቅንጣት ምሳሌነት በፍልሰታ ሱባዔ ለህጻናቱ የሚስተምሩትን የሕይወት ምሥጢር በዓለም ዙሪያ የተበተነው ሁሉ ወጣት ረስቶ Fast Food Nation ሆኖ እንዳይቀር፥ እንደ ጤፏ ቅንጣት የመበተኑ፥ የመዘራቱ፥ የመታጨዱና የመወቃቱ መከር አልፎ የመሰብሰቡ ወቅት አሁን እንደሆነ የማስተማርና የማስጨበጥ አቅሙና ችሎታው የሚፈቅደለት ኢትዮጵያዊ ሁሉ ኀላፊነት አለበት:: እግዚአብሔር ሁላችንንም በሰላም ጠብቆ ለከርሞዋ ፍልሰታ ያብቃን::

ለሌሎች ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ ጦማሮች የሚከተለዉን ድህረ-ገጽ ይመልከቱ:: http://www.medhanialemeotcks.org/