አፋጣኝ መፍትሔና መሠረታዊ ለውጥ የሚሻው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሰራተኞች እና የመንገደኞች አቤቱታ

አፋጣኝ መፍትሔና መሠረታዊ ለውጥ የሚሻው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሰራተኞች እና የመንገደኞች አቤቱታ (ምንልክ ሳልሳዊ )

በብልሹ አሰራር የበሰበሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላለፉት ሀያ አመታት በሰራተኞቹ እና በመንገደኞች ላይ መንግስታዊ ወንጀል ሲፈፅም የኖረ ተቋም ነው ። በአቶ ተወልደ የሚመራው የተቋሙ ማኔጅመንት ከሕወሓት ኢሕአዴግ የደህንነት ተቋም ጋር ተቀናጅቶ በዜጎች ላይ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት አድርሷል ። የሰራተኞችን መብት ማኔጅመንቱ እንዲያከብር መንግስት እርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል ።

ዘረፋንና ዘረኝነትን አጣምሮ የያዘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ስር ነቀል የመዋቅር ለውጥ ሊደረግ ይገባል።ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች ጀምሮ እስከ መንገደኞች ድረስ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ከፍተኛ የሆነ ስሞታ ያቀርባሉ፤ በተለያየ መንገድ በድርጅቱ ላይ የገጽታ ግንባታ ፕሮፓጋንዳ ቢሰራም አየር መንገዱን ከዘረፋና ከዘረኝነት ሊታደግ ባለመቻሉ ዘረፋውና ዘረኝነቱ አይኑን አፍጥጦ እያየነው ነው።

በተለያዩ የመስሪያ ቤቱ ቁልፍ መዋቅሮች ላይ የተመደቢ ዘራፊዎችና ዘረኞች አየር መንገዱን ለእዳና የዜጎችን መብት እንዲጣስ ከማድረጉም በላይ በከፍተኛ ደረጃ ሕገወጥ ስራዎች ይፈጸማሉ። የተለያዩ የሃገርን ኢኮኖሚ የሚጎዱ ኮንትሮባንዶች በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ትእዛዝ ይሰራል ; ወደ ሃገር ውስጥ የሚገቡና ከሃገር የሚወጡ በርካታ ማቴሪያሎች የውጪ ምንዛሬዎች የተፈጥሮ ሃብቶች በኢትዮጵያ አየር መንገድ በሕገወጥ መንገድ የሚዘዋወሩ የሃገሪቷን ኢኮኖሚ ባዶ አስቀርተውታል።

ዘረፋ ብቻ ሳይሆን አየር መንገዱ ዜጎችን ለማፈንና ሕጋዊ ተጓዦችን ለማስተጓጎል በሚደረገው ደሕንነታዊ ስራ ላይ ተባባሪ ነው፤ ዜጎች በነጻ እንዳይዘዋወሩ በሃገር ውስጥና በውጪ በረራዎች ላይ ሰላዮችን በመመደብ ወንጀል ላይ የ አየር መንገዱ ማኔጅመት ተሳታፊ ነው። በርካታ የደሕንነቱን መስሪያ ቤት ወንጀሎችን በማስፈጸም ረገድ ሚናው የላቀ ነው።ከአየር መንገዱ በርካታ ኢትዮጵያውያን በፖለቲካ እምነታቸውና በዘራቸው እየተመረጡ ተባረዋል። እንዲሁም ያገኙትን እድል በመጠቀም ከሃገር የሸሹም በርካቶች ናቸው። ይህ አየር መንገድ ከደሕንነት ተቋሙ የተቀበለውን ትእዛዝ ወደ ተግባር በመለወጥ ዘረኝነት በድርጅቱ ውስጥ እንዲነግስና የተወሰኑ የገዢው ሰዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሲሰራ ቆይቷል። ሰሞኑን ወደ ሳኡዲ አረብያ ለሐጅ ፀሎት በሚጓዙ ሙስሊም ምእመናን ላይ ያደረሠው በደል የአየር መንገዱ የብልሹ አሰራር ውጤት ነው።

ሳይቀረጥባቸው በርካታ እቃዎች በመንግስት ባለስልጣናትና ዘመዶቻቸው በሕገወጥ መንገድ በገፍ ገብተው የግብር ከፋዩን ነጋዴ እንቅስቃሴ ከጨዋታ ውጪ እያደረጉ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን በአሁን ወቅት ባለፉት ሃያ ሰባት አመታት ሲዘርፉ የኖሩ ባለስልጣናትና ባለሃብቶች ከነዘመዶቻችው የአየር መንገዱን ሰራተኞች በመጠቀም የውጪ ምንዛሬ እያሸሹ ይገኛሉ። ይህ ከፍተኛ ቁጥጥር ካልተደረገበት አደጋው የከፋ ነው። ወደ ዱባይ የሚሸሹ የውጪ ምንዛሬዎች ማረፊያቸው ማሌዢያና ፓናማ ባንኮች ነው። አየር መንገዱ ሊፈተሽ ፣ ሊጠራና ሊበረበር እንዲሁም ስር ነቀል ለውጥ ሊደረግበት ይገባል። የኢትዮጵያ መንግስት አስቸኳይ የቦርድና የማኔጅመንት ማስተካከያ በማድረግ የሰራተኞችንና የመንገደኞችን እምባ ማበስ አለበት ።#MinilikSalsawi