የቴፒው ግጭት አልቆመም።

የጅምላ ፍርድ መስፋፋት አደገኛነት!

ሙሉቀን ተስፋው

የቴፒው ግጭት አሁንም አልቆመም፤ መከላከያም የገባ አልመሰለኝም፡፡ ዛሬ በስልክ ከቴፒ ባረጋገጥኩት መሠረት ሰዎች እየተጎዱ ወደ ሆስፒታል የሚገቡ አሉ፡፡ ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ አደገኛነቱ ከሁሉም ሊከፋ ይችላል፡፡ ይህ አደገኛ አካሔድ ትናንት በጅጅጋ አብያተ ክርስቲያናትንና ሰዎችን ማቃጠል፣ በናዝሬት መድረሻ ያጡ የተፈናቃይ ወገኖችን መጠለያ ማቃጠል፣ በሻሸመኔ የስቅላት ቅጣት፣ በወለጋ የሁለት ሰዎች ሕይወት በግፍ መገደል ወዘተ ብቻ ተወስኖ አለመቆሙን ነው የሚያሳየን፡፡

እንዲህ ዓይነት የጅምላ ፍርድን ማስቆም የሁሉም ኃላፊነት ይመስለኛል፡፡ በዚህ ሒደት ማንም በምንም የሚተርፍ አይኖርም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ባሕር ዳር ላይ በሕገ ወጥ ንግድ የሚንቀሳቀስን እህል መያዝ የሰው ገላን በእሳት ከማቃጠል ጋር አነጻጽረው ሲያቀርቡ አይቻለሁ፤ ይህ ዓይነት ራስን ማታለል ለችግሩ መፍትሔ አያመጣም፡፡