በማስፈራራት አቋሜን ለማስቀየር ባለመቻላቸው በእስር ለመሞከር ያቀረቡት ክስ ነው ! – አስካለ ደምሌ- ከቃሊቲ እስር ቤት/ የፖለቲካ እስረኛ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ

በማስፈራራት አቋሜን ለማስቀየር ባለመቻላቸው በእስር ለመሞከር ያቀረቡት ክስ ነው ! የግል ጥቅሜን ባለማስቀደም – ለሀገር ህልውና በመታገሌ የመጣ ክስ ነው። — አስካለ ደምሌ- የባልደራስ አመራር ከቃሊቲ እስር ቤት/ የፖለቲካ እስረኛ

በእነ እስክንድር ነጋ መዝገብ በሽብር ወንጀል ተከስሸ ያለ አንዳች ጥፋት ቃሊቲ ወህኒ ቤት እገኛለሁ። ችሎት በምንቀርብበት ጊዜ ጉዳያችንን ዘርዝረን እንድናስረዳ በቂ ጊዜ አልተሰጠንም። ንግግሮቻችን በሽራፊ ደቂቃዎች የተገደቡ ናቸው። በመሆኑም ለፍርድ ቤቱም ሆነ ለሰፊው ሕዝብ ይደርስ ዘንድ ይህንን መጣጥፍ አዘጋጀሁ።

“መንግስት ላይ ጫና መፍጠር እና የእርስ በእርስ ግጭት ማስነሳት” በሚል ክስ ተመስርቶብኝ እስር ቤት ሆኜ ጉዳየን እየተከታተልኩን መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ለመታሰሬ ምክንት የሆነው ጉዳይ ከመከሰቱ በፊት፡-

1. በመንግስት ተቋም ውስጥ በምሰራበት ወቅት በእያንዳንዱ እንቅስቃሴየ ልክ መንግሥታዊ የስለላ አባላትን መመደብ፣ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች “መንግሥት ደሞዝ እየከፈለሽ በባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ መሳተፍ የለብሽም” ብለው በአካል እና በስልክ ተፅዕኖ ሲፈጥሩብኝ ነበር።

2. የፖሊትካ ተሳትፎዬን ብቻ በማየት በርቀት መከታተያ (GPS) አማካኝነት ሲሰልሉኝ ቆይተዋል። ግንቦት 21ቀን 2012 ዓ.ም ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ስልክ ደውለው አስፈራርተውኛል። ይህንን ፍርድ ቤቱ ሊረዳው ይገባል። ለክሱ ሰበብ የሆነው ክስተት ከተፈጠረ ከ42 ቀናት በኋላም ያለ አንዳች ማስረጃ አስረውኛል። እነኝሁ ሰላዮች በአካል አግኝተው ፖለቲካዊ አቋሜን እንድቀይር ጠይቀውኛል። ይህንን ካደረግኩ የጋራ መኖሪያ ቤት እንደሚሰጠኝና የኦሕዴድ/ብልፅግና አመራር እንደምሆን ነገረውኛል። ይህን ካልፈለግኩ ከሀገር ወጥቸ መኖር የምችልበትን ዕድል እንደሚያመቻቹም ገልፀውልኛል። እነኝህን መደለያዎች ባለመቀበሌና አቋሜን ባለመቀየሬ ወደ እስር ቤት የተወረወርኩ መሆኑን ሕዝብም ሆነ ፍርድ ቤቱ ሊያውቁት ይገባል። ከዚህም በተጨማሪ የደህንነት መሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች በሄድኩበት እየተከታተሉ ፎቶ ግራፍ ሲያነሱኝ ነበር።

3. አዲስ አበባ ኮልፌ ቃራኒዮ ክፍለ ከተማ ዓለም ባንክ ፋኑኤል በሚባል ቦታ ለተፈናቀሉ ህዝቦች ከባልደራስ የተደረገውን ድጋፍ ልናደርስ ቦታው ላይ በተገኘበት ወቅት እኔን ጨምሮ ብዛት ያላቸው የመንግስት የፀጥታ አካላት ተረጂዎችን የባልደራስ አመራሮች ታግተን ቆይተናል። ካራ ፖሊስ ጣቢያ ታስረን ከሰዓታት በኋላ እርዳታውን ሳናከፋፍል ከእገታው ተለቀን መመለሳችን ወትሮም ለክስ ሰበብ እየተፈለገልን እንደነበር አመላካች ነው።

በለገሀር የይሁዳ አንበሳ ሃውልት እና ዙርያውን ለማፅዳት፣ ችግኝ ለመትከል እና የዘርዓይ ድረስን 82ኛ ዓመት ዝክረ በዓል በማክበር ላይ እያለን ፕሮግራሙን ሳንጨርስ እኔን ጨምሮ የባልደራስ ከፍተኛ አመራሮች እና ደጋፊዎችን ብዛት ያላቸው የመንግስት ፖሊሶች አስቆሙን። ቀጥሎም ወደ ለገሀር ፖሊስ ጣቢያ ወስደውን ካገቱን በኋላ ለቀውናል።
በባልደራስ 6 ኪሎ ከተፈሪ መኮንን ከፍ ብሎ የሚገኘው ዋና ጽ/ቤት ውስጥ ሥራ ላይ እያለን የፌዴራል ፖሊሶች መጥው ጠመንጃ ደቀኑብን። በማስፈራራት አቋሜን ለማስቀየር፣ የፖለቲካ ተሳትፎዬን ለመግታት ጥረት ሲደረግ እንደ ነበረና ይህ እስርም የዛው አካል መሆኑ ይታወቅ።

ፍርድ ቤቱ ሆይ በቁጥጥር ስር ከዋልኩኝ በኋላም የፌዴራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ (ማዕከላዊ) እያለሁኝ ሁሉም ተጠርጣሪ ተቆጥሮ ወደ ቤት ከገባ በኋላ ሰዓት እላፊ መስኮት ከተው ለምስክሮች ሲያስጠኑኝ፣ የተለያዩ ማስፈራራቶች ሲደርስብን እንደ ነበረ እና በወቅቱ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት ያደረግኩኝ መሆኑ ይታወቅልኝ።

4. በምርመራ ላይ በነሐሴ 5 ቀን 2012 ዓ.ም በመርማሪው ስጠየቅ ከነበሩት ውስጥ፤ “የአፄ ምኒልክ ሃውልት እንዳይፈርስ የአዲስ አበባን ህዝብ አደረጅተሸ ታግለሻል፣ መንግሥት ደሞዝ እየከፈለሽ ለምን የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር መሆን አስፈለገ፣ አዲስ አበባ የነዋሪዎቿ ነች በማለት በአስሩ (10) ክፍለ ከተማ ወጣቶችን ወይም ህዝቦችን ለባልደራስ ለእውነትኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ስታደራጅ ነበረ” በማለት መርምሮኛል። ከዚህ መረዳት የሚቻለው ጉዳዩ የፖለቲካ እንጂ የህግ እንዳልሆነ ነው።

5. በአዲስ አበባ የሥራ ዕድል ፈጠራን አስመልክቶ እና ለአዲስ አበባ የመጣ የተዘዋዋሪ ፈንድ ብድር ብሔርን ያማከለ ስለ ነበር ለሁሉም ብሔር እድሉ መድረስ አለበት በማለት የበኩሌን ድርሻ ተወጥቻለሁኝ። ይህም ለመታሰሬ አንድ ምክንያት ነው፡፡

6. በአዲስ አበባ ውስጥ በብዙ ወረዳዎች ላይ የቀበሌ መታወቂያ ሕጋዊ ሂደቶችን ሳይከተል ማለትም መሸኛ ሳይመጣ፣ በሀሰተኛ የድንች ማህተም በወረዳዎች ግቢ ውስጥ መዘጋጀቱ እየታወቀ፣ ያለ ባለቤት ፍቃድ በሰው ቤት ቁጥር መታወቂያ ለኦሮሚኛ ተናጋሪዎች ብቻ እየታደለ፣ ህጋዊ መስፈርቶችን አሟልው ከሌላ የኢትዮጵያ ጫፍ ለሚመጡ እየተከለከለ ብሎም መሸኛቸው ላይ ከጀርባ ከ6 ወር በኋላ ነው የምትሰስተናገዱት መባለቸውን፣ በጋሃድ ስለ ስለተቃወምኩኝ ብቻ ሳይሆን ስለ ታገልኩኝ ሚዛናዊ አገልግሎት መኖር አለበት ስላላኩኝ መታሰሬ ይታወቅ።

7. በአዲስ አበባ የወረዳ ሥራ አስፈፃሚዎች ላይ መታወቂያ በዜሮ ዜሮ (00) ኮድ እንድያወጡ በሥም ዝርዝር ከበላይ አካል መርተውላቸው እሱንም ወደ መታወቂያ ክፍል እንዲያስተላልፉ ጫና ሲደረግባቸው ስለነበረ ይህ አግባብ አለመሆኑን ተቃውሜያለሁ። ታግያለሁ። የእስሬ ምክንያትም የኸው ነው።

8. ያለአንዳች ህጋዊ እና አስተዳድራዊ ምክንያት ከኦዴፓ (የብልጽግና ፓርቲ ኦሮሚያ ቅንጫፍ አባላት) ውጪ የሆኑትን ዜጎች (ብሔረሰቦች) ከሥራ ገበታቸው ሲባረሩ፣ ከአመራርነት ዝቅ ሲደረጉ በማየቴ እና በመታገሌ የደረሰብኝ እንግልት እና እስር ነው።

9. በመንግሥት መሥሪያ ቤት ብሄርን የማጣራት ሥራ ስለ ተጀመረ ለምን አስፈለገ?፣ የሚል ተቃውሞ በማስነሳቴ ምክንያት የመጣ እስር እንጂ እንደ ተባለው ወንጀል ሰርቼ እንዳልሆነ ፍ/ቤቱ እንድገነዘብልኝ እጠይቃለሁ፡፡

10. የብልጽግና ፓርቲ ኦሮሚያ ቅርንጫፍ የአዲስ አበባ ክፍለ ከተማ አመራሮች በሥራ ልምድ፣ በትምህርት ዝግጅት እና በመፈፀም ብቃት የተሻለ እያለ በብሔር ተረኛ ነኝ ባዮች ሲመዳደቡ እና እነዚሁ አመራሮች ደግሞ በዚሁ ተረኝነት ስሜት ሌሎችን በትምህርት ዝግጅት እና ልምድ ያነሱበትን ለመመደብ ሲንቀሳቀሱ አይቼ ታግያለሁኝ። ወደ ፊትም እታገላለሁ። እስሩም ከዚሁ የመነጨ መሆኑ ይታወቅ።

11. ከ1997 ዓ.ም. እና 2005 ዓ.ም. የጋራ መኖሪያ ቤት የተመዘገቡትን ባለ እድሎችን አስመልክቶ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ በእጣ አወጣጡ፣ ቅድመ ቁጠባ ቆጥቦ ጨርሶ እጣ ውስጥ ያለ መካተታቸውን አስመልክቶ፣ መሉ ክፍያ ከፍሎ ዕጣ ውስጥ ያለው መግባታቸው፣ ቤቱ የደረሳቸው ደግሞ ቤቱን አለመረከባቸውን፣ ሳይቆጥቡ የተሰጣቸውን እና ፍትሀዊ ባልሆነ መንገድ ለአንድ ብሔር ብቻ መታደላቸውን አስመልክቶ ፓርቲው የማህበረሰቡን ቅሬታ ለመቀበል በማህበራዊ ሚዲያው የግል ስልኬን ለጥፎ ስለ ነበር የመንግስት አካላት ደውለው “የተለጠፈውን ስልክ አንሺ” እያሉ ሲዝቱብኝ ነበር፣ ይህን አስመልክቶ ብዙ ቅሬታዎችን አስተናግደናል። እኔም ይህንን ድርጊት በመቃወሜ የመጣ እስር እንጂ እንደ ተባለው ወንጀል ሰርቼ እንዳልሆነ ፍርድ ቤቱ ሆይ እንድትረዳልኝ እጠይቃለሁ።

12. እኔን ጨምሮ የመንግስት ሰራተኞችን ብልግጽና ፓርቲን ትቀበላላችሁ አትቀበሉም በማለት የተለያዩ ማስገደዶች ሲደርሱ አይቼ ለምን በማለት ስለ ተቃወምኩኝ የመጣ እስር እንጂ ወንጀል አልሠራሁም።

13. አዲስ አበባ የምትተዳደረው በቻርተር ሆኖ ሳለ በቻርተሩ ላይ የሥራ ቋንቋ አማርኛ መሆኑን በግልፅ ደንግጎ እያለ በ2011 ዓ.ም “እኔ የምሰራበት መስሪያ ቤት አዲስ ብድር እና ቁጠባ ተቋም” (አማ) ለክፍት የሥራ መደብ ማስታወቂያ አውጥቶ ማስታወቂያ ላይ ኦሮምኛ መናገር መፃፍ የሚችል የሚል መስፈርት አመጣ። ይህንን በመቃወሜም ታስሬያለሁ።

14. ሚያዚያ 27 ቀን 2012 ዓ.ም የአርበኞች የድል ቀን ሲከበር የባልደራስ ለእውነተና ዴሞክራሲ ፓርቲ የሰማዕታት ሃውልት ላይ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች እኔን ጨምሮ የአበባ ጉንጉን አስቀመጠን ስለ ነበር ይህ ሁኔታ በማህበራዊ ሚዲያ ፎቶ ተሰራጭቶ ነበር። የመንግሥት አመራሮች ይህን ፎቶ በማየት ይህንን ድርጊት አቁሚ ብለው ከፓርቲው ጋር ያለኝን ግንኙነት ለማስቆም ብዙ ጥረት ሲደርጉ ቆይተዋል፡፡ የሀሰት ክሱም የመነጨው ከዚህ ነው።

15. በኢትዮጵያ ቤተ መንግስት መግቢያ በር ላይ የተገነቡት የፒኮክ ምልክቶች የሀገራችንን ምልክት የማይገልፁ በመሆናቸው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አግባብ አይደለም በማለት የተቃውሞ ፊርማ ማሰባሰቡ ይታወቃል፡፡ እኔም ከፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን “እኔ ብሄራዊ ምልክቴ አንበሳ እንጂ ፒኮክ አይወክለኝም” የሚል ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያ አሰራጭቻለሁ፡፡ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ይህንን ቪዲዮ በማየት ከፍተኛ ተፅዕኖ ከመፍጠራቸውም በዘለለ ለእስር ዳርጎኛል፡፡

16, አዲስ አበባ ሲቪል ሰርቪስ 2012 ዓ.ም በወጣው ክፍት የሥራ መደብ ላይ ምዝገባውም ቅጥሩም ብሄር ብሔረሶችን የሚወክል አይደለም፣ አንድ ብሔር ማለትም ኦሮምኛ ተናጋሪዎችን ብቻ የሚወክል ነው በማለት መቃወሜ ለእስር እና ለተለያዩ የመብት ጥሰቶች ያጋለጠኝ መሆኑን ፍ/ቤቱን ማስገንዘብ እፈልጋለሁ፡፡

17, አዲስ አበባ ነዋሪዎቿ ነች፣ ማንኛውም ዜጋ መጤም ሰፋሪም ሊባል አይገባም በማለቴ የመጣ እስር ነው። ክሱ በራሱ ማንነትን መሰረት ያደረገ፣ የመናገር፣ የመቃወም፣ የመደራጀት፣ ህገ መንግስታዊ መብትን የሚጥስ ብቻ ሳሆን አማራ እና የደቡብ ተወላጆችን (የጋሞ ተወላጅ) በጋራ ማደረጀት የሚለው ክስ በእራሱ ልዩነትን የሚያስፋ ነው። ሁለቱህዝቦች በአንድ ላይ ቢደራጁም የሚያለሙ እንጂ የሚያጠፉ አይደሉም። ስለዚህ ክሱ መሰረተ ቢስ ነውና ሊዘጋ ይገባል፡፡

18. አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀይ ቀለም ያላቸውን አልባሳት፤ የአጼ ምኒልክ ምስል ያላቸው ትሸርቶችን በመስሪያ ቤት አካባቢ ስለብስ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩ አልፀደቀም በማለት እና ቲሸርቱ ላይ ያላቸው እይታ መጥፎ በመሆኑ ለመታሰሬ ምክንያት ሆኗል።

19. የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት ማህበረሰቡ ውስጥ ገብተው 1 ለ 5 ሲያደራጀ ለማህበረሰቡም ሆነ ለመንግስት መስሪያ ቤት ሰራተኞች ከፍተኛ አደጋ ያጋልጠናል በማለት ስለ ተቃወምኩኝ የታሰርኩ መሆኔን ፍ/ቤት እንዲገነዘብልኝ እፈልጋለሁ።

20 . በሀገሪቷ በአጥቃላይ እንደ ባልደራስ ለእውነተና ዲሞክራሲ ፓርቲ ካለን ብዙ ሃሳቦች በጥቂቱ የንፁሃን ዜጎች ሞት፣ መፈናቀል፣ የዘር ማጥፋት፣ የንብረት መውደም፣ የኃይማኖት ተቋማት ማለትም የመስጊድ፣ቤተክርስቲያን እና ሌሎችም መቃጠል፣ መፍረስ፣ መዋረድ የለባቸውም በማለት ስለ ተቃወምን እና ስላወገዝን ለእስር የተዳረግን መሆናችን ግልፅ ነው። መንግስት አቻ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በተለያዩ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ጠርቶ ሲያወያይ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲን ግን አንድም ውይይት ላይ አላሳተፈውም። ይህ ደግሞ የሚያመላክተው ካለን ህዝባዊ ቅቡልነት የተነሳ መንግስት በጥላቻ የሚመለከተን መሆኑን ነው። ፍ/ቤቱም ሆነ መንግሥት እንዲረዳ የምፈልገው ሌላኛው ጉዳይ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ማንኛውም ሰው በአመለካከቱ ልዩነት ምክንያት፣ በብሄሩ ምክንያት፣ በኃይማኖቱ ምክንያት፣ በፖለቲካ አቋሙ ምክንያት ለእስር እና ለተለያዩ መገለሎች መዳረግ የለበትም የሚል ነው፡፡

21. የመንግስት አካላት የፖለቲካ ተሳትፎየን በማወቅ የእጅ ስልኬን ቀድመው በመጥለፍ ሲከታተሉኝ ነበር። አሁንም በእጃቸው ላይ የሚገኘውን ስልኬን የኢንተርኔትና የስልክ ጥሪ እየተጠቀሙበት ነው። የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የመሰረተብኝ ክስ አንድም ለመጠርጠር እንኳን የሚያበቃኝ በሌለበት፣ አንድም አካል ለህገ ወጥ ዓላማ ማደራጀቴን ማስረጃ ባልቀረበበት ነው።

22. የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የመመስረቻ ጉባኤ ላይ መስራች አባል ስለሆንኩኝ፣ በጉባኤው ላይ መገኘቴን ከማህበራዊ ሚዲያ መረጃ በማየት፣ የመንግስት ደህንነት አካላት ከፍተኛ ክትትል ከማድረግም ያለፈ የፓርቲው አባልነቴን እንዳቆም ጥረት አድርገዋል። የምሰራበት ተቋም ማለትም አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም (አማ) የሰራተኞችን መብት የሚጥስ፣ጉልበት (በብዙ ሃይል የሚሰራን ስራ አንድ ሰው ላይ በመጫን) ሰራተኞች ሲቀጠሩ የስራ ድርሻ የማይሰጥበት፣ የሰራተኛ ጥቅማ ጥቅም የማይከበርበት፣ ሰራተኛ ከስራ ሲለቅ የሰራውን ስራ በስራ ልምዱ ላይ በዝርዝር አለማስቀመጥ፣ እውቀት፣ ልምድ እና ትምህርት ዝግጅት የተሻለ እያለ ከዚህ ያነሱትን ማስቀደም ስለሌለ፤ ይህ መሆን የለበትም መስሪያ ቤቱ የሰራተኛ ደም መጣጭ ነው በማለት ስለ ተቃወምኩኝ የታሰርኩ መሆኔን ፍ/ቤቱን ማሳወቅ እፈልጋለሁ፡፡

በአጠቃላይ ከላይ የተዘረዘሩት ተግባራት ለእስር ካጋለጡኝ ጉዳዮች መካከል ከብዙ በጥቂቱ ናቸው። በመሆኑም የግል ጥቅሜን ባለማስቀደም፤ ለሀገር ህልውና በመታገሌ የመጣ ክስ መሆኑን አውቆ ፍርድ ቤቱ ውድቅ እንዲያደርግልኝ እጠይቃለሁ። ስለ እውነት ብላችሁ ከእስር እንድንፈታ በልዩ ልዩ መንገዶች በአሳሪዎች ላይ ጫና እየፈጠራችሁ ላላችሁ ሰዎች ሁሉ ምስጋናየ ይድረሳችሁ።

አስካለ ደምሌ- የባልደራስ አመራር ከቃሊቲ እስር ቤት/ የፖለቲካ እስረኛ