በሊብራል ገበያ የንግድ ሥነ-ምግባር ( ጌታቸው አስፋው )

በሊብራል ገበያ የንግድ ሥነ-ምግባር
***
ጌታቸው አስፋው
***
በዓለም ዐቀፍ ኢኮኖሚ ጥናት ከምርትም በላይ ትኩረት ስቦ ብዙ የተባለለት ንግድ ነው፡፡ በተግባር ቅደም ተከተል ማምረት ከመነገድ ይቀድማል፡፡ ሆኖም ግን ሰዎች ከራሳቸው የግል ፍጆታ አልፈው በግብይይት መልክ ያመረቱትን ሽጠው ከገበያ የሚፈልጉትን ለመግዛት ያደረጉት እንቅስቃሴ በኢኮኖሚ ጥናት ውስጥ ትልቅ ቦታ አለው፡፡ የዚህ ምክንያቱም ማምረት ግላዊ ብቻ ሊሆንም ሲችል፣ ንግድ ግን ማኅበራዊ ስለሆነ ነው፣ የሰፊ ሕዝብ እንቅስቃሴ ስለሆነ ነው፡፡ ተጨማሪ እሴት የሚፈጠረው በምርት ሂደት ቢሆንም ዋጋ ግን የሚወሰነው በንግድ ሂደት ውስጥ ስለሆነ ነው፡፡

ኢኮኖሚክስ እንደ የማኅበራዊ ኑሮ ዘዴ የጥናት መስክ ሆኖ ሲጀምር የሞራልና የሥነ-ምግባር ጥበብ ነበር፡፡ ጥንት ከከፕሌቶና አሪስቶትል ጀምሮ ስለ ሀብት ይዞታና አጠቃቀም በሥነ-ምግባር ደንብ ተጠንቷል፡፡ ከኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ በተለይ ንግድ ለብዙ ዘመናት ማጭበርበርና ማታለል ያለበት የማኅበረሰብ ጠንቅና የተወገዘ ነገር ተደርጎ ይቆጠር ነበር፡፡ ሮማውያንም የግሪኮችን ወርሰው ለንግድ በጎ አመለካከት አልነበራቸውም፡፡ በመካከለኛው ክፍለ ዘመን የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከጥሬ ገንዘብ ንግድ (ብድር) ወለድ መውሰድን እንደነውር ቆጥራ አውግዛለች፡፡ ዛሬም በእስልምና ሃይማኖት ባንክ ከሚቀመጥ ጥሬ ገንዘብ ወለድ መቀበል ሀጢዓት ተደርጎ ወለድ አይቀበሉበትም፡፡

አቅመቢሱን በንግድ ግንኙነት በዝብዞ፣ ሌላውን አደህይቶ ራስ መክበር ዛሬም ቢሆን የግለሰቦችና የአገራት የብልጽግና መንገድ ነው፡፡ ሆኖም ንግድ በሁለት ሕጋዊ ሰውነት ባላቸው አካላት ስምምነት የሚፈጸም ስለሆነ ሕጋዊ ነው፡፡ በሕግ ከተደነገጉት የሰው አካልን ወይም እጾችን ከመነገድ ሸቀጦችን ደብቆ አላግባብ እጥረት ፈጥሮ ከማትረፍ በቀር በስምምነት መነገድ ማትረፍ ሕገ ወጥ ሥራ ተደርጎ መክሰስ መውቀስ አይቻልም፡፡ ነገር ግን ጥሬ ገንዘብ ፈጥሮ ከሚያሰራጨው መንግሥትና በጥሬ ገንዘብ እንዲነግዱ ከተፈቀደላቸው፣ የገንዘብ ድርጅቶች በቀር አለማወቅን ወይም አቅመቢስነትን ተጠቅሞ አራጣ በማበደር በጥሬ ገንዘብ ግብይይት መክበር ለግለሰቦች ክልክልና በሕግ የሚያስቀጣ መሆኑን አገራት በአዋጅ ይደነግጋሉ፤ ኢትዮጵያም ይህን ድንጋጌ አውጃለች፡፡

ምንም እንኳ ንግድ የሁለት ተገበያዮች የገዢና የሻጭ የግል ጉዳይ ቢሆንም፣ ሕገ ወጥ ንግድ እንዳይፈጠርና የአገርን ጥቅም ከማስከበር አንጻር ንግድ የግለሰቦች ቤተሰቦችና ማኅበረሰቦች ግላዊ ጉዳይ ብቻ ከመሆንም አልፎ የአገርና የመንግሥታት ጉዳይም ሆኗል፡፡ በአገር ውስጥ መንግሥታት በሥነ-ምግባር ምክንያት ባህል የሚያጎድፉ፣ ባሕርይን የሚያበላሹ፣ ሱስ የሚሆኑ፣ ጎበዙ ደካማውን እንዳይበዘብዘው፣ አንዳንድ ዓይነት ንግዶችን የቆጣጠራሉ የምግብና የመድሃኒት የመሳሰሉ ምርቶች ንግዶች እጥረት እንዳይገጥማቸውም ድጋፍ ያደርጋሉ፤ ሸቀጥ ደብቀው የዋጋ ንረት ከፈጠሩ በኋላ አውጥተው የሚሸጡትን ይቀጣሉ፡፡

በውጭ ንግድም መንግሥታት ራሳቸው ባይነግዱም፣ የግለሰቦች አጋር በመሆን ዜጎቻቸው ከውጭ ዜጎች ጋር የሚያደርጉትን የንግድ ግንኙነት በመደገፍና በማደናቀፍ ይተባበራሉ፡፡ የኮንትሮባንድ ንግድን ያደናቅፋሉ፤ ሕጋዊ ንግድን ይደግፋሉ፡፡ መንግሥታት ዜጎቻቸው ከውጭ ሕዝቦች ጋር ተነጋግደው ለአገሮቻቸው የውጭ ምንዛሪና ቋሚ ሀብት እንዲያመጡ ይደግፏቸዋል፤ በሕግ ፊትም ጥብቅና ይቆሙላቸዋል፡፡ ስለሆነም በሊብራል የገበያ ኢኮኖሚም ቢሆን ገበያው መረን የለቀቀ እንዳይሆን መንግሥት ልዩ ልዩ የንግድ ሕጎችን አውጥቶ ገበያውን ይቆጣጠራል፡፡ በኢትዮጵያ ንግድን በመቆጣጠርና ሻጩ በሸማቹ ላይ ሸቀጥ በመደበቅ አላግባብ ዋጋ መጨመር የመሳሰሉትን ህገወጥ ንግዶች እንዳይፈጽም በምታደርገው የላላ ቁጥጥር ከኒዮ-ሊብራሎቹም የባሰ ልቅ የገበያ ሥርዓት የምታራምድ አገር አስመስሏታል፡፡

ኒዮ-ሊብራሎች የሠራተኛ አቀጣጠርና አያያዝን አስመልክቶ፣ የአካባቢ ጥበቃን አስመልክቶ፣ የትርፍ ህዳግን እና የንግድ ሥነ-ምግባርን አስመልክቶ፣ በአምራቹና በነጋዴው ላይ ብርቱ ቁጥጥር ሲያደርጉ ሕግ ደንግገው የሞኖፖል ገበያ ሥርዓትን ተቆጣጥረው ወደ ውድድራዊ ገበያ ኢኮኖሚ ሲመልሱ፣ ኢትዮጵያ ግን አምራቹ በፈለገው ዋጋ የሠራተኛውን ደሞዝ የሚወስንበት፣ አካባቢውን እንደፈለገው የሚበክልበት፣ ነጋዴው በሸማቹ ላይ እንደ ልቡ ዋጋ የሚጭንበት ልቅ የሆነ ነጻ ንግድ የሚካሄድባት አገር ነች፡፡

ኢሕአዴግ ንግድን ኢትዮጵያ ውስጥ የቂም በቀል መውጫና የፖለቲካ ዓላማ አድርጎ ነው የተጠቀመው፤ እንዲከብሩለት የፈለጋቸው ሰዎች ከብረውለታል፤ እንዲደኸዩለት የፈለጋቸው ደህይተውለታል፡፡ “ወይ ከሀብታም ተወለድ ወይ ከሀብታም ተጠጋ፤” በሚለው ብሂል የኢሕአዴግ ዓላማ ውስጥ ሳይኖሩ በመጠጋት የከበሩ ቢኖሩም ኢሕአዴግ ንግዱን የፖለቲካ ዓላማ መሣሪያ እንዳደረገው የሚያመለክቱ በጽሑደፍ ተዘርዝረው የማያልቁ በርካታ መገለጫዎች አሉ፡፡