ለሕወሃት ቅርቡ ማን ነው አብን ወይንስ የኦሮሞ ብልጽግና #ግርማካሳ

“አንዱ የጁንታዉ የመንፈስ ልጅ እና የአብን አመራር አባል በድፍረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቃት ስለሌላቸዉ ስልጣን ይልቀቁ ብሏል። ፅንፈኛዉ እና የድል አጥቢያ አርበኛዉ አብን ጌታዉ ሲሞት ጥያቄዉን በአስቸኳይ ወርሶ ብቅ ብሏል! በነገራችን ላይ ውርሱን ለባህሪ ወንድሞቹ በምን ስሌት ሊያካፍል አስቦ ይሆን?” ሲሉ አቶ ታዬ ደንድ ዓ በአብን አመራር ዶር ደሳለኝ ጫኔ ላይ የመረረ ተቃውሞ አቀርበዋል።
አቶ ታዬ አብንን የሕወሃት ልጅ አድርገው ነው ያቀረቡት። አብኖችን ከሕወሃቶች ጋር የባህሪ ወንድማማቾች አድርገው ነው ያቀረቧቸው።
በነገራችን ላይ ዶር ደሳለኝ ጠቅላይ ሚኒስተሩ ብቃት የላቸውምና ይልቀቁ ሲሉ አንደኛ የግል አስተያየታቸው ነው። ይሁ አቋማቸው የአብን አቋም አይደለም። ሆኖም ግን ነገ የአብን አቋም ሆኖ እንደ ድርጅት “ጠቅላይ ሚኒስተሩ ይልቀቁ” ቢባል ብዙም የሚያስደንቀኝ ነገር አይሆንም። “በማስተዳድረው ክልል ውስጥ ዜጎች በማንነታቸው ተለይተው የሚገደሉ ከሆነ እኔ ምን እሰራለሁ?” እንዳሉት የሶማሌ ክል ር እስ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ፣ በተከታታይ በአገራችን እያየነው ያለው ሰቆቃና የዘር ጭፍጨፋ እየተፈጸመ ባለበት ወቅት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛኝ ስራቸውን ካልሰሩ መልቀቅ ነው ያለባቸው መባሉ የሚጠበቅ ነው። የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ መሆን ማለት ቀይ ቆብ አድርጎ ፣ situation room ሆነን እየሰራን ነው የሚል ፎቶ መልቀቅ አይደደለም።
ዶር ደሳለኝም ሆነ ማንም ኢትዮጵያዊ ጠ/ሩ ከሃላፊነታቸው ይልቀቁ ብሎ መናገር ይችላል። በኃይል በአመጽ መሪዎች ለመቀየር እስካልተሞከረ ድረስ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የብልጽግና ጠቅላላ ጉባዬ ወይንም ፓርላማው የመተማመኛ ድምጽ በመንፈግ (vote of no confidence) አዲስ ጠቅላይ ሚኒስተር እንዲተካ ግፊት ማድረግ መብት ነው። አቶ ታዬ ለምን ዶር አብይ ይነሱ ተባለ ብሎ ከመቆጣት፣ ለምን ዶር አብይ መቀጠል እንዳለባችው በሐሳብ ቢከራከሩ ጥሩ ነበር የሚሆነው። የሰለጠነ ፖለቲካም ነው።
የዶር አብይ አብይን ጉዳይ ለጊዜው እንተወዉ አብንን የሕወሃት ልጅ አድርገው በማቅረብ አቶ ታዬ በሰጡት አስተያየት ዙሪያ አንዳንድ ሐሳቦች እንዳነሳ ይፈቀድልኝ።
ከሁለት አመት በፊት “የአማራ ብሄራዊ ንቃንቄ- አብን፣ ሕወሃትን የሽብር ቡድን ብሎ፣ በሕግ እንዲታገድ ጠየቀ” በሚል ርእስ መረጃ ሜዲያ የአብንን አንድ መግለጫ አውጥቶ ነበር። በመግለጫው የሚከተለውን እናነባለን፡
“ሕወሃት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በተለይም በአማራ ሕዝብ ላይ በፈፀማቸውና እየፈፀማቸዉ ባሉ የዘር ማጥፋት፣ ዘር ማፅዳት፣ መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ ከፍተኛ ዘረፋና ውንብድና እንዲሁም በአገርና በሕዝቦች አንድነት ላይ እየፈፀመ ባለው የሽብርና የጥፋት ድርጊቶች መነሻነት በአሸባሪነት ተፈርጆ ከማናቸውም የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች መታገድ እንዳለበት አብን በጽኑ ያምናል። ስለሆነም ሕወኃት ከአገሪቱ ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝርዝር ውስጥ እንዲፋቅ አብን እየጠየቀ ከዚህ አሸባሪ ቡድን ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መልኩ የሚሰሩ የንግድ ድርጅቶች፣ ግለሰቦች/የጥፋት ቡድኖች ግንኙነታቸውን እንዲያቋርጡ አብን በአንክሮ ያሳስባል። ከሕወኃት ጋር ግንባር የፈጠሩ ፓርቲዎችም ውሳኔያቸውን እንዲያጤኑ አብን ይጠይቃል”
ያኔ አቶ ታዬ ደንድዓ አባል የነበሩበት ኦህዴድ/ኦዴፓ በኢሕአዴግ ውስጥ ከሕወሃት(እርሳቸው ጂንታው የሚሉት) ጋር እህት ፓርቲ እየተባባሉ ይሰሩ ነበር። በቅርብ የኦሮሞ ብልጽግና ሊቀመንበር ዶር አብይ አህመድም የሕወሃቱን መሪ ዶር ደብረጽዪንን ደግፉት እንዳሉ ሁላችንም የምናስታውሰው ነው።
ሕወሃቶች ይሄ ሕገ መንግስት የሚቀየረው በመቃብራችን ላይ ነው ባዮች ነበሩ። ሆኖም የሕወሃትን መወገድ ተከትሎ የሕወሃት ሌጋሲ ለማስቀጠል አቶ ታዬ ራሳቸው በቅርቡ ሕወሃት በህዝቡ ላይ የጫነው ሕገ መንግስት ችግር የለበት፥ ችግር ያለው አፈጻጸሙ ላይ ነው ማለታቸው መቼም ይዘነጉታል ብዬ አላስብም። በሌላ አባባል የሕወሃት ፖለቲካ እንዲቀጥል ፍላጎት ያላቸው እርሳቸውና ደርጅታቸው የኦሮሞ ብልጽግና መሆኑን ነው የገለጹልን። አቶ አዲሱ አረጋም ተመሳሳይ አስተያየት ነው የሰጡት።
አብን በበኩሉ አሁን ያለው ሕገ መንግስት የአንድን ቡድን ጥቅም ለማስጠበቅ የተሰራ መቀየር ያለበት ሕግ መንግስት እንደሆነ ነው በተደጋጋሚ እየገለጸና እየተናገረ ያለው።
እንግዲህ ትልቁ ጥያቄ ለሕወሃት ቅርቡ ማን ነው ? የሚለው ነው። የሕወሃት አስተሳሰብን የሚያራምደው፣ ህወሃት አሸባሪ ድርጅት ተብሎ ይፈረጅ ሲባል እምቢ ብሎ ለረጅም ጊዜ ከህወሃት ጋር ሲሰራ የነበረው፣ ህወሃት በትግራይ ከተባረረችም በኋላ አሁንም ህወሃትን አሸባሪ ለማለት የሚያቅማማው እነ አቶ ታዬ ደንድዓ ያሉበት የኦሮሞ ብልጽግና ነው ? ወይንስ ከጅምሩ ሕወሃት አሸባሪ ድርጅት ተብሎ ይፈረጅ ሲል የነበረው፣ የሕወሃት ከፋፋይ የዘር ፖለቲካ የዘር ሕገ መንግስት ይቀየር፣ የሕወሃት በአካል እንደተሸነፈችው የሕወሃትን መፈንስ መወገድ አለበት ብሎ የሚታገለው አብን ????? መልሱን ለአንባቢያንና ለአቶ ታዬ ደንድዓ ለራሳቸው እተዋለሁ።
አቶ ታዬ አብንን ከኦነግም ጋር ለማገናኘት ሞከረዋል። አብን ደግሞ ከኦነግ ሸኔ ጋር በመቀናጀት “ተረኛ” እና “ነፍጠኛ” በሚል የጁንታዉን ትርክት ለማስቀጠል ለፍቷል” ሲሉ። በዚያ ዙሪያ ተከታይ ጽሁፍ ይዤ እመለሳለሁ።
“የጁንታዉ ህልውና በክፍፍል ላይ እንደተመሠረተ ይታወቃል። በተለይ ደግሞ አማራንና ኦሮሞን ለማባላት “የእሳት” እና “የጭድ” ትርክት ፈጥሮ ለ27 ዓመታት ተጠቅሞበታል” ያሉት አባባልም አለ። ትኩረቴን የሳበው። በዚህም ጉዳይ በስፋት እመለስለሁ። ለጊዜው ግን ይህ አባባል በግርድፉ ትክክለኛ አባባል መሆኑ እየገለጽኩ ከጣና ኬኛ በኋላ በአማራውና በኦሮሞም ፖለቲከኞች መካከል የነበረውን መቀራረብ ሙሉ ለሙሉ በሚ መልኩ ያደፈረሰው አራት ኪሎና አዲስ አበባ መስተዳደር ውስጥ ኦህዴዶች ከገቡ በኋላ የወሰዷቸው አፍራሽና ዘረኛ ስግብግብነት የተሞላበት እርምጃዎች መሆኑን ለአቶ ታዬ ደን ድዓ ላስታወሳቸው እፈለጋለሁ። ሌላው ቢቀር የርሳቸው ጓድ አቶ ሺመለስ አብዲሳ የተናገሩትን፣ አቶ ታከለ ኡማ በአዲስ አበባ ሲሰሩ የነበሩትን መጥቀስ ይበቃል። በዚህ ጉዳይ ላይ በስፋት እመለሳለሁ::