ሕግ መንግስቱ እንዲቀየር ዘጠኝ ስብስቦች በጋራ ያወጡት ባለ ሰባት ነጥብ መግለጫ

ለኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት – አዲስ አበባ
➢ ለኢፌድሪ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር – አዲስ አበባ
➢ በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኢምባሲ-ዋሽንግተን ዲሲ
➢ ለህብር ሬዲዮን ጣቢያ-ሰሜን አሜሪካ
➢ ለአዲስ ድምጽ ሬዲዮ–ሰሜን አሜሪካ
➢ ለኢትዮ360 ሚዲያ-ሰሜን አሜሪካ
➢ ለርዕዮት ሚዲያ – ስሜን አሜሪካ
➢ ለሚዛን ቴሌቪዥን-ሰሜን አሜሪካ
➢ ለምኒልክ ቴሌቪዥን-ሰሜን አሜሪካ
➢ ለአማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ/-ሰሜን አሜሪካ
➢ ለመረጃ ቴሌቭዥን ጣቢያ-ሰሜን አሜሪካ
➢ ለዘመድኩን በቀለ-መረጃ ቲቪ-ጀርመን
➢ ለአባይ ሚዲያ-አዲስ አበባ
➢ ለኢቲቪ-አዲስ አበባ
➢ ለአማራ ቡዙሃን ሚዲያ ኤጀንሲ-ባህርዳር
➢ ለአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ጣቢያ-ሰሜን አሜሪካ
➢ ለጀርመን ድምጽ ሬዲዮ ጣቢያ -ጀርመን
➢ ለዘሃበሻ-ሰሜን አሜሪካ
➢ ለኢትዮጵያ አንድነት ሬዲዮ-ስዊድን
➢ ለርዕዮት ቲቪ-ሰሜን አሜሪካ
➢ ለአደባባይ ሚዲያ-ሰሜን አሜሪካ
➢ ለኢትዮ-ቤተሰብ ሚዲያ-ሰሜን አሜሪካ
➢ ለመረጃ ሚዲያ-ሰሜን አሜሪካ
➢ ለፍትሀ መጽሄት-አዲስ አበባ
➢ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል ለምትሉ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች በሙሉ-ባላችሁበት
➢ ለሀገር ወዳድ ማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች-ባላችሁበት
➢ ለመላዉ የኢትዮጵያ ህዝብ

ጉዳዩ:-የኢትዮጵያን መጻኢ እድል በአንድነት: በህግ የበላይነት :በፍትህ፣ በእኩልነት ብሎም በዲሞክራሲያዊ
መሰረት ላይ ለማቆም እንዲቻል የቀረበ ሀገራዊ ጥሪ

ሕወሓትና ኦነግ ኢትዮጵያን በዘር ከፋፍለዉ፣ የሕዝቡን የአብሮነት የወል ዕሴቶች በማጥፋት፣ ሕዝቡ ከኢትዮጵያዊነት ማንነቱ ወጥቶ አጥፊና ጠፊ ሆኖ
እንዲቆም በማድረግ፤ ከሁሉም በላይ ዐማራና ኢትዮጵያዊነት ጠል የሆነ ሕገ መንግሥት በሕዝቡ ላይ መጫናቸው ግልጽ ነው። ይህ ሕገ-መንግሥት ዛሬ
በአገራችን ላይ በሁሉም አካባቢዎች ለሚታየው መገዳደል፣ መፈናቀል፣ መሳደድና አገር አልባ መሆን ዋናው የችግሮቻችን ቋጠሮ ነው። በአገሪቱ ታሪክም ሆነ
በማዕከላዊ መንግሥት ምሥረታ ሒደት ከፍተኛ ሚና ከተጫወቱት ነገዶች አንዱ የሆነውን ዐማራ፣ በትሕነግ የሚመራው ኢሕአዴግ የተባለው ድርጅት ስብስብ፣
ዐማራን የሁሉም ነገዶች አውራ ጠላት አድርጎ በመፈረጅ ባሰራጨው የዘረኝነት ፕሮፓጋንዳ፣ “መጤ፣ የምኒልክ ሠፋሪ፣ ትምክሕተኛ፣ ነፍጠኛና ጨቋኝ”
የሚሉ ስሞችን በመስጠት፣ አገር አልባ ከማድረጉም በላይ ዓለም አቀፍ ወንጀል የሆነው የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀል እንዲፈጸምበት አድርጓል ። ይህ
ሕገ-መንግሥት የግለሰቦችን ነፃነት፣ የሰዎችን ዕኩልነት፣ የሕግን የበላይነት በሚያረጋግጥ፣ ዲሞክራሲዊ መብቶችን፣ የጋራ ጥቅሞችንና ነጻነቶችን በሚያስከብር
ሕገ መንግሥት ካልተተካ የአገሪቱ ችግሮች ይፈታሉ ማለት ዘበት ነው።

• የመከላከያ ሰራዊቱ፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላት፣ ከአማራ ክልል የተንቀሳቀሱ ሚሊሺያዎች፣ እንዲሁም የአፋር ክልል ልዩ ኃይል አባላት፣ በጋራ
ባደረጉት ጥረትና በከፈሉት ከፍተኛ መስዋእትነት፣ ሕወሃት ከመቀሌ ምሽጉ በመደምሰሱ እንደ ማንም ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያዊያን በእጅጉ አስደስቶናል።
ቢሆንም በትግራይ ድሎች ቢመዘገቡም፣ አሁንም በመተከልና በኦሮሞ ክልል የኦነግ አሸባሪዎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ እየፈጸሙት ያለው ጥቃት እንደቀጠሉ
ነው። አሁንም ንጹህ ዜጎች በጽንፈኞች እጅ እየተገደሉ ነው። መንግስት ለትግራይ የሰጠውን አይነት ትኩረት ለመተከልና ለኦሮሞ ክልል በበቂ ሁኔታ
እየሰጠ ነው ብለን አናምንም። በተለይ ደግሞ የኦሮሞ ክልልና የቤኒሻንጉል ክልል መንግስታት ህግን በማስከበር አንጻር ያላቸው ቁርጠኝነት ላይ ትልቅ
ጥያቄዎች አሉን። በመሆኑም የፌዴራሉ መንግስት በአስቸኳይ በመተከልና በኦሮሞ ክልል ሰላምንና መረጋጋትን ማስፈን እንደ መንግስት ግዳጁ
ስለሆነ የመንግስት አውታሮችን ከሰርጎ ገብ እና ተባባሪዎች በማጽዳትም ጭምር ሃላፊነቱን እንዲወጣ በአጽንኦት እንጠይቃለን፡

• የኢትዮዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ይፋ እንዳደረገው በማይካድራ ከ700 በላይ ዜጎች መታወቂያቸው እየታየ ዐማራ ስለሆኑ ብቻ ትሕነግ
ባደራጃቸው ዘረኛና አሸባሪ ታጣቂዎች የጅምላ ጭፍጨፋ ተፈጾሞባቸዋል። በኢሰመኮ ሪፖርት ከተጠቀሰው በተጨማሪም በርካታ ዜጎች በጅምላ ተገድለው
መቀበራቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች በይፋ እየወጡ ነው። በተመሳሳይ ሁኔታ ከማይካድራው ዕልቂት ቀደም ብሎ በወለጋ ጉሊሶ ተተኪ ኀይል ሳይሰማራ
የመከላከያ ሠራዊት ከስፍራው መልቀቁን ተከትሎ ወደ አካባቢው የመጡ የኦነግ ታጣቂዎች ከ200 በላይ ዐማራዎችን በትምህርት ቤት ግቢ ዉስጥ በአንድ
አዳራሽ ሰብስበው የጅምላ ጭፍጨፋ ፈጽመዉባቸዋል። ላለፉት ሁለት ወራት በማይካድራ፣ በወለጋ፣ በመተከል እና በጉሩፈርዳ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
ሃይማኖት ተከታዮች ላይ እንዲሁም በአማራ እና በአገው ነገዶች ላይ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀሎች ተፈጽሟል። የሐጫሉን ግድያ ተከትሎ
አያሌ ንፁሐን ዜጎች በግፍ ተገድለዋል። ንብረት ወድሟል። ቤቶች በእሳት ጋይተዋል። ከላይ የተጠቀሱት የዘር ፍጅቶች እንዲሁም ከአንድ ዓመት በፊት
አቶ ጃዋር መሐመድ ተከብብኩ በማለት በፌስቡክ ባሰራጨው ወሬ በኦሮሞ ክልል በባሌ፣ ሐረርጌና አርሲ ዞኖች የተፈጸሙትን ጭፍጨፋዎች በገለልተኛ
አካላት ተጠንቶ ሁሉም የወንጀሉ ተሳታፊ የሆኑ ቡድኖችና ግለሰቦች ለፍርድ እንዲቀርቡ በአንክሮ እንጠይቃለን።

• መንግሥት ችግሮችን ከማድበስበስ ወጥቶ፣ ችግሮችን አሳንሶ ግጭት ከማለት በትክክለኛው የወንጀሉ ስም የዐማራን ዘር እና ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት
ተከታዮችን ማጥፋትን ዘር ማጥፋት በሚል ሊጠራው ይገባል። ኢትዮጵያዊነት ተዋርዶ፣ ጎሠኝነት እና ክልላዊነት በመንገሡ የተነሳ ኢትዮጵያውያን
በሀገራቸዉ ተዋራጅ፣ ተገፊ፣ ተገዳይ፣ እና ተፈናቃይ ሆነዋል። ዜጎች በመላ ሀገሪቱ ሠርተዉ ከመኖር ይልቅ በሀገራቸዉ ተሳዳጅ እንዲሆኑ ያደረገዉ
የጎሳ ፖለቲካ ፍልስፍና ሀገሪቷን አሁንም እየመራ በመሆኑ በመላዉ አለም ያለን ኢትዮጵያዉያንን ላለፉት ሠላሳ ዓመታት ሲያሳፍረን ኖሯል። አሁንም
በዚህ ሥርዓት እና አስተሳሰብ መቀጠል እያፈርንበት እንገኛለን። ስለሆነም የችግሮቻችን ሁሉ ምንጭ የሆነው የጎሳ ፖለቲካ ፍልስፍና ተወግዶ ኢትዮጵያዊ
በሆነ የፖለቲካ ፍልስፍና ሊተካ ይገባዋል እንላለን:: ለዚህም እዉን መሆን ከህዝባችን ጋር ሆነን እንታገላለን::

• ያልታጠቁ ሰላማዊ ዜጎችን በተደራጀ መልኩ መጨፍጨፍ አሸባሪነት ብቻ ሳይሆን አለም አቀፍ ወንጀል ጭምር ነዉ:: የኢትዮጵያ መንግስት ኦነግንና
ህወሃትን አሸባሪ ብሎ ላለመፈረጅ እያደረገ ያለውን ማቅማማት በጭራሽ ልንረዳው አልቻልንም። የፌዴራል መንግስቱ አቃቤ ሕግ ሰላማዊ በሆነ መንገድ
ለአዲስ አበባ ህዝብ መብትና ለእኩል ተጠቃሚነት የሚታገሉ፣ አገራቸውንና ወገናቸውን ከመውደድ ውጭ ምንም አይነት ጥፋት የሌለባቸውን የባልደራስ
አመራሮች ምስክርነታቸውን ከመጋረጃ ጀርባ በሰጡ ምስክሮች አማካይነት “አሸባሪ” ብሎ የሃሰት ክስ መስርቶባቸዋል:: ይሄም ታላቅ ጸረ ዲሞክራሲያዊነት
እና የወደፊትን የኢትዮጵያን ሰላም የሚጎዳ አምባ ገነናዊ እርምጃ መሆኑን መንግስት ማወቅ ይሳነዋል ብለን እናምንም:: ሆኖም መታወቂያቸው እየታየ
በጅምላ ሰላማዊ ዜጎች በመግደል የዘር ማጥፋት ወንጀል የፈጸሙትን የህወሃትና የኦነግ ቡድኖችን በአሸባሪነት አለመፈረጅ ኢፍትሃዊ ስለሆነ አጥብቀን
እንቃወመዋለን። በአገራችን ከዘር ፖለቲካ የተነሳ በኦነግ፣ በህወሃት እና በልዩ ልዩ የወንጀል ሀይሎች በጌዲዮ በወላይታ በጉራጌ በጋሞ በሸካ በጉሙዝ
እንዲሁም በሌሎች ማህበረሰቦች ላይ በርካታ ግድያ ማፈናቀል እና የዘር ጭፍጨፋ ተከናዉኗል:: እነዚህን ዘር ተኮር እልቂቶች እንዲሁም ከላይ በዝርዝር
የቀረቡትን በአማራ ህዝብ እና በተዋህዶ ኦርቶዶክስ አማኞች ላይ የተፈፀሙትን የዘር ማጽዳት እና የዘር ማጥፋት ወንጀሎችን የሚያጣራ ገለልተኛ አካል
በአስቸኳይ እንዲመሰረትና ተጎጂ ወገኖች በቂ ካሳ እንዲከፈላቸው እንዲሁም ወደ ቀያቸው ተመልሰው ይቋቋሙ ዘንድ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ
እንዲያደርግላቸዉ እንጠይቃለን።

• የአገሪቷ “ሕገ መንግስት” የሚባለው ከመቋቋሙ በፊት የበጌምድር ክፍለ ሃገር አካል የነበሩት የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ካፍታ ሁመራና ጠለምት፣እንዲሁም
የወሎ ክፍለሃገር አካል የነበረው ራያ በጉልበት ወደትግራይ ክልል እንዲካተቱ ተደርገዋል። ኋላም የጎጃም ክፍለ ሃገር አካል የነበረው መተከል ወደ
ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እንዲካተት ተደርጓል። ሰሞኑንን ከሕወሃት ጋር በተደረገው ውጊያ በከፍተኛ መስዋዕትነት የተመዘገበውን ድል ተከትሎ
ከቤጌምድርና ከወሎ የተወሰዱት አካባቢዎች ከሕወሃት እጅ ወጥተዋል። ሕወሃት ዴሞግራፊን ለመቀየር በነዚህ አካባቢዎች የፈጸማቸው የዘር ማጥፋት
ወንጀሎች በስፋት እየተዘገቡ ነው። ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል፤ ተሰደዋል። በብዙ ቦታዎችም የጅምላ መቃብሮች እየተገኙ ነው። ይሄም
ልባችንን እጅግ አድምቶታል። ከነዚህ አካባቢዎች የተፈናቀሉትን ወገኖቻችን መልሰው እንዲቋቋሙ በመርዳት ፋንታ፣ የሕወሃት ሕገ ወጥ ተግባር ትክክል
እንደነበረ በሚያሳስብ መልክ ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ካፍታ ሁመራ፣ ጠለምትና ራያን አዲስ በተመሰረተው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ መንግስት ስር
እንዲተዳደሩ ለማድረግ የሚወሰደውን ማናቸውንም አይነት እንቅስቃሴ አጥብቀን እንቃወማለን። አገር ተረጋግታ ሕዝባዊ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ሕዝቡ
እራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱ እንዲከበርለት እንጠይቃለን። ሆኖም የህግ የበላይነትን በማስከበር ስም መንግስት የወያኔን እና የኦነግን ህገመንግስት
እየጠቀሰ እነዚህን አካባቢዎች አለ ፈቃዳቸዉ ወያኔ በ1983 ዓም በጉልበት ወደ አካለላቸዉ ክልል ተካተዉ እንዲቀጥሉ ማስገደድ ካሰበ እጅግ ትልቅ
መዘዝ እና ጣጣ ለመንግስት ለራሱ ይዞበት እንደሚመጣ ካሁኑ ማሳሰብ እንወዳለን:: የኛ ፍላጎትና አቋም ህዝባችን የሚመርጠዉን እና ፍላጎቱን መደገፍ
ስለሆነ በወልቃይት፣ በጠገዴ፣ በካፍታ ሁመራ፣ በጠለምትና በራያ ያለዉ የወገናችን ፋላጎት እንዲሰማና እንዲከበር አጥብቀን መንግስትን እናሳስባለን::
የአማራ ወገናችንም በአጠቃላይ እና በጋራ በመንቀሳቀስ አሁን በእጁ የገባዉን ድል ማስጠበቅና እንዲሁም በመላዉ ሀገሪቱ ህልውናውን የማረጋገጥ ትግሉን
ዳር ሳያደርስ እንዳይዘናጋ አጥብቀን እንመክራለን:

• የኢትዮጵያ ህዝብ የሕወሃትን መወገድ እንደ ትልቅ ድል የቆጠረው በዋናነት ሕወሃት ካራመደውና ከሚያራምደው የፖለቲካ አስተሳሰብ በመነሳት ነው።
ሕወሃት ማለት ዘረኝነት፣ መከፋፈል፣ ኢፍትሃዊነት፣ ኢሰባአዊነትና ሙሰኝነት ማለት ነው። ሕወሃት በአካል ከትግራይ ቢወገድም የሕወሃት አስተሳሰቦች
እስካልተወገዱ፣ የሕወሃት ህገመንግስትና የሕወሃት የፌዴራል አወቃቀር እስካልተቀየሩ ድረስ መተካካት እንጂ ለውጥ አለ ማለት አይቻልም። የህወሃትን
አስተሳሰብ የተሸከመዉ የሙሰኛ ንቅዘታዊ የመንግስት አሰራር ስርዓት እና በጎሰኝነት በመጓተት ህዝብን በማንነት መፈረጅ እስካልቆመ ድረስ ህወሃት
ተወግዷል ማለት ፈጽሞ አይቻልም:: ስለሆነም መንግስት በአስቸኳይ ዘረኛ እና ሙሰኛ ባለስልጣናትን አበጥሮ በመለዬት ከመንግስት መዋቅር የማስወገድ
እርምጃ እንዲወስድ በጥብቅ ጥሪ እናቀርባለንል::

• በሕወሃት ላይ የተደረገውን ወታደራዊ ዘመቻና ድል ተከትሎ አንደኛ ዜጋ፣ ሁለተኛ ዜጋ እንዲሁም ጨቋኝና ተጭቋኝ የሚለው ከፋፋይ የጎሳ ፖለቲካ
አስተሳሰብ አክትሞ የእኩልነትና የአንድነት ምሰሶዎች በተቋም ደረጃ እንዲተከሉና እንዲጠናከሩ፣ የጎሳ ክልል እንዲፈርስና ከሁሉም በላይ ወያኔና ኦነግ
ያረቀቁት የጎሳ ህገመንግስት እንዲቀዬር አጥብቀን እናሳስባለን:: በአጭሩ መንግስት ለህዝባችን ዉለታ እንዲዉልለት ሳይሆን መንግስታዊ ግዴታዉን በአግባቡ
እንዲወጣ በታላቅ አክብሮት እናሳስባለን:: በአጠቃላይ የኢትዮጵያ አንድነት በጽኑ መሰረት ላይ እንዲቆም፣ የህግ የበላይነት እንዲሰፍን፣ የእያንዳንዱ
ኢትዮጵያዊ ነገድ ህልዉናው እንዲረጋገጥ ብሎም የግለሰብ መብት የሚከበርበት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍን ብሎም ኢትዮጵያ የሁሉም
ኢትዮጵያዉያን ሀገር እንድትሆን ትግላችንን በጋራ በመቆም እንድናስቀጥል ለመላው አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን::
ኢትዮጵያን እግዚአብሄር ይባርክ !

ይሄ መግለጫ ከዚህ በታች ስማችን የተዘረዘረዉ ድርጅቶች ተወያይተን እና ተስማምተን ለሚመለከታቸዉ ሁሉ ይደርስ ዘንድ በጋራ ወስነናል:-

1. ኢትዮጵያዊነት–(ሰሜን አሜሪካ)
2. ሀገር አድን–(ሰሜን አሜሪካ)
3. የኢትዮጵያ ህልዉና አድን ህብረት–(ሰሜን አሜሪካ)
4. የዓለም አቀፍ የአማራ ህብረት–(ሰሜን አሜሪካ)
5. ሞረሽ ወገኔ የአማራ ድርጅት–(ሰሜን አሜሪካ)
6. ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ሴቶች ድርጅት-(ሰሜን አሜሪካ)
7. የባልደራስ ለእዉነተኛ ዲሞክራሲ የድጋፍ ማህበር በሰ/ሜን አሜሪካ–(ሰሜን አሜሪካ)
8. የታህሳስ ሶስት መታሰብያ ለአንድነትና ዴሞክራሲ–(ሰሜን አሜሪካ)
9. ሀገራዊ የምክክር አደባባይ–(ሰሜን አሜሪካ)