ሕወሃታዊ ሆነው ሕወሃትን መሳደብ ነውር ነው ፣ “ዶር አብይ የባልደራስ እስረኞችን ፍታ” #ግርማካሳ

አሁን ለውጥ መጣ ተብሏል፡፡ እነርሱ ከሕወሃት የተሻሉ የሆኑ ይመስል፣ ሕወሃት “ጁንታው” እያሉ እየከሰሱት ነው፡፡ መደመር፣ ፍቅር ይላሉ፡፡፡ ግን ሌሎችን ትተን የፍትህ ስራዓቱን ፣ የአቃቤ ሕግ ጽ/ቤት አሰራሮችን ብቻ እንኳን ብናይ በሕወሃት ጊዜ ከነበረው እንኳን ሊሻሻል እንደውም በአንዳንድ ጎኑ የባሰበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ለምሳሌ በመጋረጃ ጀርባ ምስክርነት የሚባለው አስቂኝ ድራማ በሕወሃት ጊዜ ያልነበረ ነው፡፡
በቴዲ አፍሮ ላይ አስቂኝ የዉሸት ድራማ ሲያቀናብሩ ከነበሩት መካከል ስለ አንዱ ትንሽ ልበላችሁ፡፡ ያኔ በአቃቤ ሕግ ጽ/ቤት ፣ በቴዲ አፍሮ ላይ የዉሸት ክስ ሰነዱን የጻፈውና ያሰናዳው ነው፡፡አቶ ፍቃዱ ጸጋ ቦካ ይባላል፡፡
አቶ ፍቃዱ አሁን በዶር አብይ አህመድ መስተዳደር ሹመት አግኝቶ ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሆኗል፡፡ ልክ ያኔ ያደርግ እንደነበረው፣ የለመደውን፣ በዉሽት ክስ፣ በሐሰትና በመጋረጃ ጀርባ ምስክርነት አሁንም ንጹሃን ዜጎችን እያሰቃየ ያለ ግለሰብ ነው፡፡(ሆ የሚባልለት የዶር አብይ መስተዳደር በምን አይነት ሰዎች እንደተሞላም ከዚህ ማየት ትችላላችሁ)
የባልደራስ አመራር አባላት፣ እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩም፣ አስካለ ደምሌና ሌሎች ይኸው ከታሰሩ አምስት ወራት ሆኗቸዋል፡፡ ከብዙ መንገላታትና መጉላላት በኋላ የኦህዴድ/ብልጽግና አቃቤ ሕግ ጳጉሜን 5 ቀን 2012 አስራ ሶስት ገጽ ያለበት፣ ከአንድ አገር አቃቤ ሕግ የማይጠበቅ እጅግ በጣም የወረደ፣ ክስ መሰረተ፡፡ ( እዚህ ጋር የኦህዴድ አቃቤ ሕግ የምለው የአቃቤ ሕግ ጽ/ቤት ለአገር ጥቅም፣ ለፍትህ መስፈን ሳይሆን ለኦህዴድ/ኦሮሞ ብልጽግና የሚሰራ ነው ብዬ ስለማምን ነው፡፡)
በክሱ ምንም አይነት የሰነድ፣ የፎረንሲክ፣ እንደ ኦዲዮ፣ ቪዲዮ ኤሜል፣ የፌስ ቡካን የትዊተር ፖስቶች የመሳሰሉ የኤሌክቶሮኒክስ መረጃዎች አልቀረቡም፡፡ ኢንሳ የነ እስክንድር ስልክ እየጠለፈ ይሰማ እንደነበረም ብዙዎች ይገምታሉ፡፡ እንደ ማስረጃ የተጠለፈ ንግግር እንኳን አልቀረበም፡፡ “ምክንያቱ ምንድን ነው ?” ቢባል መልሱ ቀላል፡፡ ምንም አይነት የከሰሱበትን ክስ የሚያረጋግጥ መረጃ ባለማግኘታቸው ነው፡፡
የባልደራስ አመራሮች ከታሰሩ ጊዜ ጀምሮ ክስ እስኪመሰረትባቸው ድረስ በርካታ ጊዜ ፍርድ ቤት ተመላልሰዋል፡፡ መጨረሻ ላይ ጳጉሜ 5 2012 ዓ/ም በሽብር ክስ ተከሰሱ፡፡ ከዚያ በኋላ መንገላታታቸው እንደቀጠለ ነው፡፡
  • ለመስከረም 12 በዕለተ ማክሰኞ ….የዋስተና መብት ይሰጥ ወይስ ይቅር የሚለውን ለመወሰን ተቀጠሩ፡፡ ነገር ግን የዋስ መብት መከበርን በተመለከተ በዚያን ቀን ውሳኔ እሰጣለሁ ያለው ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ የመሰረተውን ክስ ግልፅነት ይጎድለዋልና ከሱ ተሻሽሎ ይምጣና በሚቀጥለው ሳምንት እወስናለሁ ብሎ ለሚቀጥለው ሳምንት ማለትም ለመክሰረም 19 ቀጠሮ ይዞ ችሎቱ ተዘጋ፡፡
  • አቃቢ  ሕግ ክሱን አሻሽሎ አቀረበ፡፡ በቀረበው ክስ ላይ መቃወሚያ የተከሳሽ ጠበቆች፣ መሰከረም 29 በፁሁፍ እንዲያቀርቡ፤ እነ እስክንድር ደግሞ ጥቅምት 12 ፍ/ቤት እንዲገኙ ፍርድ ቤቱ ወሰነ፡፡
  • ጥቅምት 12 ቀን ፣ እነ እስክንድር ረጅም ቀጠሮ 50 ቀናት ለህዳር29 /2013 ተሰጠባቸው። አቃቤ ሕግ ምስክሮቼን በዝግ ችሎትና ከመጋረጃ በስተጀርባ ነው የማሰማው በማለቱ ፣ እነ እስክንድርና ጠበቆቻቸው፣ “ምስክር መደመጥ ያለበት በግልጽ በህዝብና በሚዲያ ፊት ነው እንጅ ከመጋረጃ በስተጀርባ መሆን የለበትም፡፡ ማንና እንዴት በኛ ላይ እንደሚመሰክር ስለማናውቅ፣ ምስክሮች የሚሰጡት ቃል ታአማኒንት በጅጉ ስለሚያሳስበን፣ ምስክሮቹ በግልፅ መቅርብ አለባቸው” በሚል ተቃውሞ አሰሙ፡፡ ፍ/ቤቱ ምስክሮቹ በምን መልኩ ይቅረቡ የሚለውን ለመወሰን ፣ ለህዳር29 ቀን የ50 ቀን ቀን ረጅም ቀጠሮ ሰጡ፡፡
እዚህ ጋር እንግዲህ የምናየው ምን ያህል፣ ምንም እንኳን ከሕወሃት ትግራይ ነጻ ብትወጣም፣ የፌዴራል መንግስቱና የኦሮሞ ክልልን የሚቆጣጠሩት የኦሮሞ ብልጽግናዎች የድሮውን አፋኝ ፣ ዘረኛ የሕወሃትን አሰራር ይዘው እንደቀጠሉ ነው፡፡
ባልደራሶች የታሰሩት የአዲስ አበባ ህዝብ መብት እንዲከበርና “እኩል ተጠቃሚነት ይኑር” በማለታቸው ነው፡፡ ሕወሃት በወልቃይትና በራያ የማንነት ጥያቄ ያነሱ የነበሩትን በኃይልና በጉልበት ለመጨፍለቅ ሲሞክር እንደነበረው፣ አሁንም የኦሮሞ ብልጽግናዎች ፣ “ፊንፊኔ ኬኛ” የሚለውን ፖለቲካቸውን ቻሌንጅ የሚያደርጉትን፣ “በአዲስ አበባ ሁሉም ነዋሪዎች እኩል ይሁኑ፣ የዘር ልዩነት፣ አፓርታይዳዊ አሰራር መድልዎ አይኖር፣ ኦሮሞ፣ አማራ ትግሬ መባባል ይቁም” ያሉትን፣ እንደ ጠላት ነው የሚቆጥሩት፡፡
የኦሮሞ ብልጽግናዎች ፣ ስግብግብ ሆነው ፣ “ አሁን ተራው የኛ ነው” በሚል ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡ ወደ ቀኝ ወደ ግራ ሳይሉ የሕወሃትን መስመር ነው እየተከተሉ ያሉት፡፡ ተረኛ ነን በሚል ሲዘርፉ፣ ሲያፍኑ፣ ህዝብ ሲያሰቃዩ ፣ ለሕዝብ ንቀትን ሲያሳዩ፣ የአንድ ጎሳ የበላይነት ለመጫን ሲሞክሩ፣ ነገር ግን የዛሬው የሕወሃት ተራ እንደሚደርሳቸው የዘነጉ ይመስለኛል፡፡ የሕወሃትን የተሳሳተ ፣መንገድ መከተል ከሕዝብ ያጣላል፡፡ የሕወሃት ፖሊሲና ሌጋሲ፣ ኮተቶችን ተሸክሞ መጓዝ መጨረሻዉም ዉድቀት ነው፡፡
በመሆኑም የዶር አብይ አስተዳደር፣ ጥፋቶች፣ ስህተቶች ሌሎች ላይ ማለከኩን፣ ችግሮችን externalize ማድረጉን አቆሞ፣ ፍትሃዊ የሆነ አሰራርን መከተል መጀመር አለበት፡፡ ህዝብ ያያል፡፡ ህዝብ ይከታተል፡፡ “እስከ አሁን ለነበረው ህወሃት ነው ተጠያቂው” በሚል በህወሃት ላይ ለማላከክ እንደተሞከረው፣ ወይም “እኔ ጠቅላይ ሚኒስተር እንጂ ከንቲባ አይደለሁም፣ አቃቤ ሕግ አይደለሁም፣ አልሰማሁም ..ምናምን” እያሉ መደለል አይቻልም፡፡
በመሆኑም ሌላው ቢቀር ቢያንስ የሚከተሉት በጣም ቀላል እርምጃዎች በመዉሰድ በርግጥ ከሕወሃት የተሻለ የመሆን ፍላጎት እንዳለቸው ማሳየት መጀመር አለባቸው፡፡
  1. በጠቅላይ አቃቤ ህግ ጽ/ቤቶች ያሉ ሕወሃታዊ አሰራሮች እንዲቀየሩ ማድረግ መጀመር አለበት፡፡ የባልደራስ አመራሮች ሆነ የሌሎች ፣ ምንም አይነት የሰነድ፣ የኦዲዮ፣ የቪዲዮ፣ የፎረንንሲክ …ማስረጃዎች ያልቀረበባቸው ክሶች፣ በሰዎች ምስክርነት ላይ ብቻ ያተኮሩ ክሶች ውድቅ ተደርገው እስረኞች በአስቸኳይ መፈታት አለባቸው።
  2. እነ አቶ ፍቃዱ ጸጋ ያሉ ስለ ህግና ስለ ፍትህ ምንም አይነት የጠራ ግንዛቤ የሌላቸው፣ የHግ አዋቂ ነን ባይ ካድሬዎች፣ ከሃላፊነታቸው መነሳት አለባቸው፡፡የአቃቤ ሕግ ጽ/ቤት ገለልተኛና ብቃት ባላቸው ሰዎች መሞላት አለበት፡፡ ላድሬዎች እዚያ አስይፈልጉም፡፡ (እርግጥ ነው በቅርብ ጠ/አቃቢ ሕግ የተሾመው ዶር ጌዲዮን ማቴዎስ አለ፡፡፡ ነገር ግን እርሱም ቢሆን ከዶር አብይ ፍቃድ ውጭ የመውጣት ድፍረት የለውም፡፡ እንደ ዶር ዳን ኤል በቀለና እነ ወ/ት ብርቱካን ሚደክሳ፡፡ ደጎ በስሩ ምክትል አቃቤ ሕጎች ተብለው ቱባ ቱባ የኦሮሞ ብልጽኛ ሰዎች እንዲቆጣተሩት ተቀምጠዋል)
የኦሮሞ ብልጽግናዎች በራሳቸው የሚተማመኑ ከሆነ፣ የባልደራስ አመራሮችን ይፍቱና በምርጫ ባልደራስን ይግጠሙ፡፡ ባልደራስ እንደ ህወሃት ነፍጥ አንስቶ አይደለም የሞገታቸው፡፡ ነፍጥ ያነሱት ላይ እንኳን እርምጃ ለመዉሰድ ሲዳክሩና ሲያመነቱ አልነበረም እንዴ ? ኦነግ ትጥቅ አልፈታም ሲል የአፍ ወለምታ ነው ምናምን እየተባለ ሰበብ ሲፈለግለት አልነበረም እንዴ ? ታዲያ በሐሳብ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሚንቀሳቀሱት ላይ ፣ አሁን ባለ ጡንቻ፣ ተረኞች ስለሆንን ብቻ የኃይል እርምጃ መውሰድ ምን ይባላል ?
ዶር አብይ አህመድ እንደሚለው በምርጫ የሚያምን ከሆነ፣ የሰለጠነ ፖለቲካ አራማጅ ነኝ ካለ፣ ተቃዋሚዎች መምከር አቁሞ፣ ራሱን ይምከር፡፡ የባልደራስ አመራሮችን ፈቶ በሐሳብ ባልደራስን ለመሞገት ይዘጋጅ፡፡ እርሱን የኦሮሞ ብልጽግ ናዎች በተለይም የአዲስ አበባ ህዝብ ከመረጣቸው የፈለጉትን ማስረግ ይችላሉ፡፡