መንግስት የሰጠው የ72 ሰዓታት ጊዜ ወደ መጠናቀቁ እየተቃረበ ይገኛል

መንግስት የሰጠው የ72 ሰዓታት ጊዜ ወደ መጠናቀቁ እየተቃረበ ይገኛል።

የህወሓት አባላት ግን ይህንን ጥሪ አልተቀበሉትም ፤ ይልቁንም መንግስት ሽንፈት ስለደረሰበት ለመሸፋፈን የተጠቀመው ነው ብለውታል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ትላንት በሰጠው መግለጫ ለመጨረሻው ምዕራፍ ትዕዛዝ በተጠንቀቅ ላይ መሆኑን አስታውቋል።

መቐለ ከተማን የከበበው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ፣ ለ3ኛውና ለመጨረሻው ምዕራፍ በተጠንቀቅ ቆሞ ትዕዛዝ በመጠባበቅ ላይ መሆኑን ተገልጿል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት መቐለ ከተማን በ50 ኪሎ ሜትር ውስጥ መክበቡ ተገልጿል።

ዶ/ር ደብረፅዮን ትላንት ለሮይተርስ በፅሁፍ እንዳሉት “መቐለ ተከቧል የሚባለው እስካሁን እንዲህ ያለ ነገር የለም” ሲሉ አጭር ምላሽ ሰጥተዋል።

በመቐለ ከተማ ይኖራል በተባለው ኦፕሬሽን ንፁሃን እንዳይጎዱ ወታደራዊ ያልሆኑ መሰረት ልማቶች እንዳይጠቁ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና የተለያዩ ተቋማት እየተማፀኑ ነው።

ተመድ መንግስት ያስቀመጠው የ72 ሰዓት ቀነ ገደብ መጠናቀቁን ተከትሎ በመቐለ ሊከሰት የሚችለው ሁኔታ ከወዲሁ እንዳሳሰበው አሳውቋል ፤ ድርጅቱ “የጦር ወንጅል” እንዳይፈፀምም ስጋት እንዳለው ገልጿል።

ዶ/ር አብይ ከሁለት ቀን በፊት ባስተላለፉት መልዕክት ፥ “በመቐለ የሚኖረው የህግ ማስከበር እርምጃችን ጉዳትን እጅግ በቀነሰ መልኩ መከናወን እንዳለበት እናምናለን፣ ስለዚህም መቐለ ከተማን ከከፋ ጉዳት ታድገን ዘመቻውን በድል የምናከናውንበትን መንገድ እንደምንከተል ለመግለፅ እወዳለሁ” ብለዋል።

ጠ/ሚሩ የመቐለ ነዋሪዎች ከሰራዊቱ ጎን በመቆም በህግ የሚፈለጉትን አካላት ለፍርድ በማቅረብ ወሳኝ ሚናቸውን እንዲጫወቱ ጥሪ አቅርበዋል ፤ ለጥቂት ሰዎች ሲባል አንድም ሰው መሞት ፣ ንብረትም መውደም የለበትም ብለዋል።

(ቲክቫህ)