ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በዓለምአቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ክስ የሚመሰረትባቸው መሆኑ ተሰማ

የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በዓለምአቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት በቀጣይ የዛሬ ሳምንት ማክሰኞ (December 01/2020) ክስ የሚመሰረትባቸው መሆኑ ተሰማ። ጉዳዩን አስመልክቶ መረጃውን ያወጣው አዲስ ዘይቤ አዘጋጅ የመረጃውን እና ከታማኝ ምንጭ የተገኘ መሆኑን አረጋግጦል። በመጭው ማክሰኞ የሚገባው አቤቱታ ዶ/ር ቴድሮስ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የህወሐት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል በነበሩበት ወቅት በተፈፀመ የዘር ማጥፋት እና ሌሎች ወንጀሎችን የተመለከተ መሆኑን አዲስ ዘይቤ ከታማኝ ምንጭ አረገጋግጣለች፡፡

እንደ አቤል አገላለጽ መረጃው በዶ/ር ቴድሮስ ላይ ክስ መመስረቱ እርግጥ እንደሆነና የክስ ፋይሉም በቀጣዩ ማክሰኞ ሄግ በሚገኘው የዓለምአቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት መታየት እንደሚጀመር ገልጿል። የመረጃውን ምንጭ አስመልክቶ  “በቀጣይ ሳምንታት የሚከናወኑ ክስተቶችን አስመልክቶ በተለያዩ የዓለም ሀገራት ለሚገኙ የሚዲያ ተቋማት ቅድመ መረጃ የሚልክ የውጪ ድርጅት እንደሆነ በመግለፅ ድርጅቱ የአዲስ ዘይቤ ቋሚ ደንበኛ እና ታማኝ የመረጃ ምንጭ መሆኑን ተናግሯል።

በዚህ መሠረት በቀጣይ ሳምንት ማክሰኞ እለት የሚዲያዎችን ትኩረት ከሚስቡ ክስተቶች አንዱ ተብሎ ከተላኩት ውስጥ “በአለምአቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር በሆኑት ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ላይ የቀረበው የክስ ፋይል ይታያል” የሚል ይገኝበታል።