የህወሓት ጁንታ ታጣቂ ሃይል በማይካድራ የፈጸመውን ጭፍጨፋ በመቀሌ ለመድገም ዝግጅት እያደረገ ነው- ሜ/ጀኔራል መሀመድ ተሰማ

ኢዜአ – የህወሃት ጁንታ ታጣቂ ሃይል በማይካድራ የፈጸመውን ጭፍጨፋ በመቀሌ ለመድገም ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የመከላከያ ኢንዶክትርኔሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጄር ጀኔራል መሀመድ ተሰማ ተናገሩ።የትግራይ ህዝብ ሰራዊቱ በተቆጣጠራቸው ቦታዎች ሁሉ ለሰራዊቱ ያለውን ድጋፍ በተግባር እያሳየ መሆኑንም ገልጸዋል።ቡድኑ ድርጊቱን የሚፈጽመው ልዩ ቡድን አዘጋጅቶና በአልመዳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ያዘጋጀውን የመከላከያንና የኤርትራ ሰራዊት ዩኒፎርሞችን በማልበስ እንደሆነም ነው የጠቆሙት።
ሜጀር ጀነራል መሀመድ ተሰማ ይህን ያሉት ወቅታዊ ጉዳይን አስመልክቶ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ነው።የህወሃት ፅንፈኛ ሃይል በየጊዜው እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ መረጃዎችን በማሰራጨት ህዝብን እያደናገረ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት።ለአብነትም ቡድኑ ከቀናት በፊት “በራያ ግንባር 21ኛ ክፍለጦርን ደምስሰናል፤ አድዋ ላይ የመጣውን ሃይል በመደምሰስ አካባቢውን ተቆጣጥረናል” ሲል መናገሩን አንስተዋል። ነገር ግን በእለቱ እርሳቸውን ጨምሮ የሰራዊቱ አመራሮች በተገለጹት ስፍራዎች ላይ በመገኘት ለመገናኛ ብዙሃን ገለጻ ማድረጋቸውንና ገለጻውም አየር ላይ መዋሉን ነው የተናገሩት።
ይህም የጁንታውን የሃሰት ፕሮፓጋንዳ የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል።የቡድኑ አፈቀላጤዎች ተደብቀው መግለጫ ከመስጠት ይልቅ እውነታቸውን ከሆነ “ደምስሰን አስለቅቀናል” ባሏቸው ቦታዎች ላይ በመገኘት መግለጫ መስጠት በቻሉ ነበር ብለዋል።የቡድኑ መሪዎች ህግ የማስከበሩን ዘመቻ በትግራይ ህዝብ ላይ የተቃጣ ህዝባዊ ጦርነት ለማስመሰል እየጣሩ መሆኑንም ገልጸዋል።ነገር ግን የትግራይ ህዝብ ዘመቻው ጽንፈኛ ቡድኑን ብቻ እንደሚመለከት በተግባር ማሳየታቸውን አብራርተዋል።
የትግራይ ህዝብ ሰራዊቱ በተቆጣጠራቸው ቦታዎች ለሰራዊቱ ያለውን ድጋፍ በተግባር ከማሳየቱም በላይ ጁንታው ምን ያህል ሲበድላቸው እንደቆየ እየገለጹ ይገኛሉ ነው ያሉት።የህወሃት የጥፋት ሃይል ያሰበው ሴራ ሁሉ እየከሸፈበት መሆኑን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ ደግሞ አዲስ የጥፋት እቅድ ማውጣቱን ደርሰንበታል ብለዋል ሜጀር ጀነራል መሀመድ።በዚህም በማይካድራ ንፁሃን ላይ የፈጸመውን ጭፍጨፋ በመቀሌ ለመድገም ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጸው ድርጊቱን ለመፈጸም ደግሞ ልዩ የገዳይ ቡድን ማዋቀሩንም ነው የተናገሩት።የገዳይ ቡድን አባላቶችን በአልመዳ ጨርቃጨርቅ ፍብሪካ አማካኝነት ያዘጋጀውን የኢፌዴሪ መከላከያ እና የኤርትራ ሰራዊት ዩኒፎርሞችን በማልበስ ጭፍጨፋውን ለመፈጸም ተዘጋጅቷል ብለዋል።
ቡድኑ ይህን የሚያደርገው የኢትዮጵያና የኤርትራ ሰራዊት በጋራ በመሆን ንፁሃንን እንደጨፈጨፉ በማስመሰል ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ ለማግኘት መሆኑንም ገልጸዋል።የህወሃት ፅንፈኛ ቡድን ከስልጣን ውጭ ለህዝብ ምንም አይነት ርህራሄ እንደሌለው አመላካች መሆኑንም ጠቁመዋል።ቡድኑ በየጊዜው የሚፈጽማቸው ድርጊቶች ተስፋ መቁረጡን የሚያመላክቱ ስለመሆናቸውም ሜጀር ጀነራል መሀመድ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ህዝብ ክደው ከጽንፈኛ ቡድኑ ጋር የተሰለፉ የሰራዊቱ አባሎችም ሆኑ ቡድኑ ያደራጃቸው ታጣቂዎች በሁሉም ግንባሮች በመሸነፍ ወደ መቀሌ እንደሸሹም ነው የተናገሩት።በትግራይ ክልል ሰራዊቱ በተቆጣጠረባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች እንዳደረጉት ሁሉ የመቀሌ ነዋሪዎችም ውግንናቸው ለሰራዊቱና ለኢትዮጵያዊያን ወንድሞቻቸው እንደሚሆንም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ተገደው ለቡድኑ እየተዋጉ ያሉ ታጣቂዎችም በሀሰት ፕሮፓጋንዳ ሳይታለሉ በአቅራቢያቸው ላለው የመከላከያ ሰራዊት እጃቸውን እንዲሰጡም ጥሪ አቅርበዋል።የኢትዮጵያ ህዝብ ሰራዊቱ እያከናወነው ያለውን የህግ ማስከበር ዘመቻ በመደገፍ ረገድ እያደረገው ላለው አስተዋፆም ሜጀር ጀኔራል መሀመድ ምስጋናቸውን ምስጋና ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።