የዘር ፖለቲካ፣ የዘር አወቃቀር፣ የዘር ሕገመንግስት አስከፊ ውጤቶች ፣ በዝርዝር #ግርማካሳ

ጠቅላይ ሚኒስተር ዶር አብይ አህመድ በፓርላማ አንድ ንግግር ተናገሩ። ደስ ያለኝ ንግግር። “ትግሬ፣ አማራ፣ ኦሮሞ …መባባል ያታረፈልን ድህነትና እከክ ብቻ ነው” ነበር ያሉት። ትልቅ አባባል።  ምንም ጥርጥር የለውም ያተረፈልን ድህነት ብቻ ነው።
እኔ ግን ከዚያ አልፌ እሄዳለሁ። ድህነትና እከክ ብቻ ሳይሆን ደም መፋሰስ፣ መገዳደል፣ መተራረድንም ነው ያተረፈልን። የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ለዜግነት ለስብእና እውቅና የሚሰጥ አይደለም። ኢትዮጵያ የዜጎቿ ሳይሆነ የጎሳዎቿ ( ህገ መንግስቱ ብሄር ብሄረሰብ ህዝብ የሚለው) ናት። ስለዚህ አንድ ዜጋ በአንድ ጎሳ ጆንያ ውስጥ ካልታጠረ እውቅና አያገኘም። ያ ብቻ አይደለም የአገሪቷ ግዛቶች የተሸነሸኑት በዘር ነው። የአማራ መሬ፣ የትግሬ መሬት፣ የኦሮሞ መሬት እየተባለ።
ምን ማለት ነው ዶር አብይ አህመድ እከክና ድህነት ነው ያተረፈልን፣ እኔ ደግሞ ደም መፋሰስን ነው ያተረፈልን ያልኩት ነገር ፣ በዋናነት ምንጩ ሕወሃትና ኦነግ የዘረጉት ከፋፋይ በኢትዮጵያዉያን መካከል አጥሮች የገነባ የዘር ሕገ መንግስቱ፣ የዘር አወቃቀር፣ በአጠቃላይ የዘር ፖለቲካው ነው።

 
ምን ያህል ከዘር ጋር በተገናኝ ደም እንደፈሰሰ ለማሳየት የሚከተሉትን 41 የዘር ግጭቶች ወይም የዘር ማጥራትና ማጥፋት ወንጀሎችን በሶስት ከፍዬ እዘረዝራቸዋለሁ። አንባቢያን ምን ያህል በዚህ በሕህወሃት ሕግ መንግስትና አወቃቀር ምክንያት እንደ አገር እየደማን መምጣታችንን እንዲያውቁ። እነዚህ የተዘረዘሩት ጥቂቶቹ ናቸው። ቁጥሩ ከዚያ በላይ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። እነዚህ እኔ የማውቃቸው ናቸው።
ከደርግ ፍጻሜ እስከ አቶ ለማ መገርሳ መምጣት
ላለፉት 28 አመታት በአገራችን እጅግ በጣም መርካታ አስከፊ የዘር ተኮር ግጭቶችና እልቂቶች ተከስተዋል። ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ ጊዜ ጀምሮ ፣ አቶ ለማ መገርሳ የኦሮሞ ክልል ር እስ መስተዳደር እስኪሆኑ ድረስ ያለውን ወደ 27 አመታት የሚሆነውን ጊዜ ብንመለከት ፣ ሶሻል ሜዲያ በስፋት ስላልነበረ ብዙ ሕዝብ ስለማያውቅ ብዙ ያልነበረ ይመስላል እንጂ በርካታ ዘር ተኮር ጥቃቶች ተፈትስመዋል። ከነዚህ መካከል በፕሮፌስር መስፍን ወልደማሪያም የተመሰረተው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዬ(ኢሰመጉ) በተለያዩ ጊዜ ካወጣቸው ሪፖርቶች በመነሳት እንደሚከተሉትን መጥቀስ ይችላል፡
  1. አማርኛ ተናጋሪዎች በአርሲ አስተዳደር ፣ በአርባ ጉጉ፣ በመርቲ፣ ደጁ፣ በጎለልቻ ወረዳዎች በርካታ ሰዎች ተገድለዋል።
  2. በአርሲ ነገሌ ወረዳ ቁጥራቸው በርክታ በሆኑ የአማራና የከምባታ ብሄረሰብ ተወላጆች ላይ ግድያ ተፈጽሟል። ንብረት ወድሟል
  3. በበደኖ ከተማ ከመቶ በላይ ሰላማዊ ዜጎች፣ በዋናናት አማራዎች ፣ ነፍሰ ጡር ሴቶች ሳይቀሩ ፣ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ፣ አይኖቻቸው ተሸፍኖ ፣ ጥቅል በሆነ ገደል ውስጥ በሕይወት ተወርዉረው ተገድለዋል።
  4. በከፋና በኢሊባቡር አስተዳደር አካባቢዎች በጉራጌ ማህበረሰብ አባላት ላይ ከመኖሪያ የማፈናቀል ኢሰብዓዊና ሕገ-ወጥ ድርጊቶች ተፈጽመዋል።
  5. በኦሮሞ ክልል ጂማ ዞን የየም ብሄረሰቦች ወደ ደቡብ ክልል ለመቀላቀል ጥያቄ በማቅረባቸው በኦሮሚያ ታጣቂዎች ተገድለዋል።
  6. በሶማሌ ክልል የሚኖሩ የሬርባራባ የዱቤ ጎሳዎች፣  ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ጠይቀው በሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ ተደብድበዋል፤ ተገድለዋል።
  7. በደቡብ ክልል በሲዳማ ዞን ወንዶ ገነት ወረዳ ነዋሪ የሆኑ የጉጂ (ኦሮሞ) ብሄረሰብ አባላት ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ በማንሳታቸው ምክንያት፣  በሲዳማ ዞን በሚኖሩ የሲዳማ ብሄረተኞች ብዙዎች ተገድለዋል።
  8. በወልቃይት ጠገዴ ተደራጅተው፣ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የማንነት ጥያቄ ያነሱ ዜጎች ወደ ወህኒ ተወስደዋል።
  9. በመተከል አስተዳደር ከግንቦት ወር 1983 ዓ.ም ጀመሮ በበርካታ የአማርኛ ቋንቋ ታናጋሪ ዜጎች፣ አማራዎችና አገዎች ላይ አሰቃቂ ግድያ ተፈጽሟል።
  10. በኦሮሚያ ዞን ጊጂ፣ አዶላ ወረዳ ሸኮሶና በቦሬ እና በደቡብ ክል በጌእዶ የተፈጸሙ የጎሳ ግቶች ከፍተኛ እልቂት ፈጥረዋል።
  11. በኦሮሚያና በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ብሄራዊ ክልሎች መካከል ባሉ አዋሳኝ ቀበሌዎች ነዋሪዎች በሆኑ የኦሮሞና የጉሙዝ ብሄረሰቦች ተወላጆች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት በርካታ ሰዎች ተገድለዋል።
  12. በደቡብ በሚኖሩ የኮይራ ብሄረሰብ አባላትና በአዋሳኙ በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ የጉጂ ብሄረሰብ አባላት መካከል በተከሰተ ግጭት የሰው ሕይወት ጠፍቷል። የንብረት ዉድመት ደርሷል።
  13. በደቡብ ክልል ማጂ ዞን ጉሩፈርዳ ወረዳ ብዙዎች ሲገደሉ በሺሆች የሚቆጠሩ ፣ በአቶ ሺፈራው ሽግጤ ት እዛዝ ተፈናቅለዋል።

እነዚህን እንደ ምሳሌ አቀረብኩ እንጂ ከማንነት ፣ ከዘር ፖለቲካ ጋር በተገናኘ የደረሱ ግፎች፣ ግድያዎች፣ እልቂትች፣ ዉድመቶች ቀላል አልነበሩም።

ከአቶ ለማ መገርሳ መምጣት እስከ  ብልጽግና ፓርቲ መመስረት ሰሞን

ለ”ለውጥ” ኃይል የሚባለው ወደ ስልጣን የመጣው በሁለት ምእራፍ ነው። በመጀመሪያው ምእራፍ የ”ለውጥ” ኃይሉ የኦሮሞ ክልል መንግስት ያዘ። በሁለተኛው ምእራፍ ደግሞ አራት ኪሎን ተቆጣጠረ። ለውጥ የሚለው በቅንፍ ያደረጉት ለውጥ የተባለው ለውስጥ ስላልሆነ ነው። አቶ ለማ የኦሮሞ ክልል ርእስ መስተዳደር ሆነው ከነበረ የሶስት አመት ተኩል ፣ ዶር አብይ ጠቅላይ ሚኒስተር ከሆኑ ደግሞ ሁለት አመት ከ9 ወር ሊሆን ነው።
አቶ ለማ የኦሮሞ ክልል አስተዳደሪ ከሆነ ጊዜ ጀምሮ የብልጽግና ፓርቲ ሊቋቋም ሰሞን ድረስ በርካት በጣም አስከፊ ከማንነት ጋር የተገናኙ እልቂቶች፣ ግድያዎች መፈናቅሎች ተከስተዋል።፡ከነዚህ መካከል የሚከተሉት ይገኛሉ።
  1. ሶማሌዎችና ኦሮሞዎች ለዘመናት በጋር በሚኖሩባቸው እንደ ሚኤሶ፣ ጉርሱም፣ ባቢሌና ሞያሌ ባሉ አካባቢዎች የኦሮሞ ነው የሶማሌ ነው በሚል ግጭቶች ብዙ ዜጎች ሞተዋል ተሰደዋል። ወደ ስድስት መቶ ሺህ የሚሆኑ ኦሮሞዎች ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ሲሆን ቁጥራቸው ከአራት መቶ ሺህ በላይ ሶማሌዎችም ከኦሮሚያ ተፈናቅለውል። በሺሆች የሚቆጠሩ ተገድለዋል። በአወዳይ ከተማ ብቻ በአንድ ቀን ከስድሳ በላይ ሶማሌዎች ታርደዋል።
  2. በኢሊባቡር ቡኖ በደሌ “መጤና ናችሁ” በሚል ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ኦሮሞ ያልሆኑ ኢትዮጵያዉይን በዋናነት ከአማራው ማህበረሰብ በገጀራ ተጨፍጭፈዋል።ብዙዎች ተፈናቅለዋል።
  3. በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ ከማሺ ዞን በአማራ ማህበረሰብ አባላት ላይ በተቃጣው ጥቃት ብዙዎች በገጀራ፣ በቀስትና በእሳት አልቀዋል።ብዙዎች ተፈናቅለዋል።
  4. በአርሲ ነገሌ በጉራጐዎችና በአማራዎች ንብረት ላይ ጥቃት ተፈጽሟል።
  5. በመቀሌ ከተማ በመቀሌ ከነማና በባህር ድር ከነማ የእግር ኳስ ክለቦች መካከል ይደረግ በነረበው ጨዋታ ወቅት በተፈጠረው ግጭት በርካታ የባህር ዳር ከነማ ደጋፊዎችና ተጨዋቾች ድብደባ ተፍጽሞባቸዋል።
  6. በነቀምቴ የትግራይ ተወላጆች በጠራራ ጸሃይ በድንጋይ ተወግረው ተገድለዋል።
  7. በወልዲያ የመቀሌ ከነማ ከወልዲያ የእግር ኳ ቡድን ጋር ጋር ሊያደርግ በነበረው የእግር ኩስ ውድድር ምክንያት የተፈጠረው ግጭት ዘር ተኮር ሆኖ ዘጎች የተጎዱ ሲሆን የብዙ ወገኖችም ንብረት ጠፍቷል። የብዙ የትግራይ ተወላጆ ንብረት ተቃጥሏል።
  8. በመቱ ዩኒቨርሲቲ የትግራይ ክልል ተወላጆች ዩኒቨርሲቲዎች እንዲለለቁ ተገደዋል። የአማራ ክልል ተወላጆች ደግሞ የተወሰኑቱ ዩኑቨርሲቲዉን ጥለው ወደ ወላጆቻቸው ሲመለሱ፣ የቀሩትን እየተማሩ ያሉ በፍርሃት ውስጥ ነው።
  9. በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ በተከሰተው ዘር ተኮር ግጭቶች ብዙዎች የተደበደቡ ሲሆን አንድ ተማሪ ከፎቅ ላይ ተወርዉሮ እንደተገደለ በስፋት ተዘግቧል።
  10. በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የትግራይ ተማሪዎች ከፎቅ ላይ ተወርወረዉ ተገድለዋል።
  11. የኦነግ ታጣቂዎች ባስነሱት ግጭት በኦሮሞ ክልልና በቤኒሻንጉል ክልል ከማዝ ወረዳ ከጉሙዞች ጋር በተነሱ ግጭት ከመቶ አምሳ ሺህ በላይ አብዛኞቹ ኦሮሞዎች ተፈናቅለዋል።
  12. በኦሮሞ ክልል ጉጂ ዞን የሚኖሩ ወደ 800 ሺህ የሚቆጠሩ ጌዴዎኦች ተፈናቅለዋል። ብዙዎች ተግድለዋል።
  13. የኦሮሞ ጽንፈኛ ቄሮዎች በቀሰቀሱት ሽብር ወደ ሰማኒያ ሺህ የሚጠጙ ዜጎች ፣ በዋናንተ ጋሞዎች በግፍና በጭካኔ ተፈናቅለዋ፤ ብዙዎች ተገድለዋል።
  14. በምስራቅ ሸዋ ፈንታሌ ወረዳ የአማራ ገበሬዎች በአክራሪ ኦሮሞዎች ተፈናቅለኣል። የተገደሉን ብዙ አሉ።
  15. በአማራ ክልል ምእራብ ጎንደር ዞን፣ በርካታ የትግራይ ተወላጆች ለሕይወታቸው ስለሰጉ ወደ ሱዳን ተፈናቅለዋል።
  16. ከአዋሳ ከተማ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ሲዳማ ያልሆኑ ዜጎች በተለይ ወላይታዎች ተገድለዋል፣ ተፈናቅለዋል።
  17. በጎንደር ቅማንትና አማራ በሚል በተነሳው ግጭት ከ80ሺህ በላይ ዜጎች ተፈናለዋል። ብዙ ወገኖች ሞተዋል።

ከብልጽግና ፓርቲ ምስረታ እስከ አሁን

የብልጽግና ፓርቲ ይዞት የተነሳው አላማ ፣ ቢያንስ በወረቀት ፍቅር፣ መደመር፣ አንድነትን ነው፡ ሆኖም ግን የብልጽግና ፓርቲ ላይ ላዩን መደመርን ቢልም ላለፉት 28 አመታት የነበረው የጎሳ ፖለኢትካ፣ን የጎሳ አወቃቀቀና በዜግነት ላይ ሳይሆን በጎሳ ላይ ያተኮረ ሕገ መንግስት በማስቀጠሉ ችግሮችም እንደውም እየተባባሱ መጡ። የፌዴራል መንግስቱ ድክመት ተጨምሮበት ፣ እነ ኦነግ፣ እነ ሕወሃት፣ ጽንፈኛ ቄሮዎች ፣ ጉሙዞች የመሳሰሉት የዘር እልቂቱ እንዲባባስ አደረጉት።

አቶ ገዱ አንዳራጋቸው ከጥቅምት እስከ ጥቅምት ነው ያሉት። ብልጽግና ፓርቲ ምስረታ ሂደት ጀተጀመረበት ጊዜ የነበረውን ላለፉት 14 ወራት ብቻ ብንመለከት  በአገራችን የተከሰቱትን ከዘርና ከማንነት ጋር የተገናኙ ግጭቶች፣ ዘር ተኮር ጥቃቶች የዘር ማጥፋት ወንጀሎች እጅግ በጣም ብዙ ናቸው። ዘር ተኮር ግድያዎች መብዛታቸው ብቻ አይደለም፤  የግዳያዎቹ የጭካኔ መጠን እየጨመረ መምጣቱን ነው የምናየው።
  1. ጥቅምት 2012 አቶ ጃዋር ተከበብኩ ያለውን ተከትሎ በኦሮሞ ክልል የመንግስት መዋቅር ውስጥ ባሉ ሃላፊዎችና ፖሊሶች ቀጥተኛ ወይንም በተዘዋዋሪ መንገድ ትብብር፣ አሊያም ዝምታ ፣ በኦነግና በጃዋር ደጋፊዎች በተለይም በሃረርጌ፣ ባሌና አርሲ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ተፈጽመዋል።
  2. በሕዳር 2012 ደምቢደሎ ዩኒቨርሲት ተማሪ የነበሩ በማንነታቸው ተለይተው በኦነግ ታጣቂዎች ታፍነው እስከ አሁን የት እንዳሉ አይታወቅም።
  3. በአዲስ አበባ የተሾሙ የኦሮሞ ብልጽግና ሃላፊዎች አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት ከሚል ስሌት፣ በአዲስ አበባ ቆጥበው ዜጎች የሰሩትን ኮንዶሚየም ለአንድ ጎሳ አባላት በነጻ ሰጥተዋል። በአዲስ አበባ ተራው የኛ ነው ከሚል የአንድ ጎሳ አባ ልዩላት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በሰፋት እነርሱ ብቻ እንዲቀጠሩ የተደረገበት ዘረኛና አፓርታይዳዊ አሰራር ያለበት ሁኔታ ነው የነበረው። አሁንም ያለው።
  4. በሰኔ 2012 ብልጽግና የሚመራው መንግስት የፌዴራል ሆነ የኦሮሞ ክልል መንግስት ቸልተኝነት ከሰባት ወራት በፊት ለተፈጠረውም የዘር ማጥፋት ወንጀል ተጠያቂነት ባለመኖሩ፣ የሃጫሉን ግድያ ተከትሎ በኦሮሞ ክልል በድጋሚ ከፍተኛ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል። እንደ ሻሸመኔ ያሉ ከተሞች ወድመዋል። ከዚህ ጋር በተያይዘ እነ ጃዋር መሐመድ ታስረዋል። ሆኖም የሚያሳዝነው እነ ዶር አብይ ጽንፈኞችን ለማባበል፣ ለማባያ ፣ ሕግን በማስከበር፣ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለ እኩል ተጠቃሚነት የሚታገሉት የባልደራስ አባላትን ፣እነ እስክንድርንማሰራቸው ነው።
  5. በጳጉሜን 2012 በቤኔሻንጉል ክልል በመተከል ዜጎች ተለይተው በማንነታቸው ብቻ አማራዎችና አገዎች ታርደዋል። ተጨፍጭፈዋል።
  6. በመስከረም 14 ፣ በመስከረም ሃያዎቹም 2013 ዓ.ም በድጋሚ ጥቃቶች በጉሞዝ ጽንፍኞች መተከል ላይ ተፈጽመዋል።
  7. ጥቅምት 2013 በጉሩፈርዳ ፣ ቤንቺ ማጂ ዞን አማራዎችና አማራ ይመስላሉ ተብለው ኦሮሞዎችን ተገድለዋል።
  8. በጥቅምት 2013 መጨረሻ በምእራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ከሁለት መቶ በላይ አማራዎች ለስብሰባ ተጠርተው በክፍሉ ውስጥ እንዳሉ ጥቃት ተፈጽሞባቸው መንግስት ወደ 50 ይላል ግን እስከ 200 የሚደርሱ ዜጎች መገደላችው ተዘግቧል። (በዚህ ጊዜ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ዶር አብይ አህመድ በማንነት ላይ ያተኮረ ጭፍጨፋ እንዳለ የተናገሩት)
  9. ከሕወሃት ጋር በተደረገው ዉጊያ በማይካድራ ከ500 በላይ አማራዎች በማንነታቸው በሚሸሹ የሕወሃት ታጣቂዎች የጅማ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል።
  10. በመተከል በባስ ተሳፍረው ይጓዙ የነበሩ በጽንፈኞች በማንነታቸው ተለይተው ተገድለዋል። አሁን ድረስ በመተከል አማራዎችና አገዎች ያለ ማቋረጥ እየተገደሉ ነው።
  11. በደቡብ ክልል አማሮ ወረዳ ከ500 በላይ አማራዎች ተፈናቅለዋል። የሞቱም አሉ።

በአገራችን እንደ ኢትዮጵያዉያን እንደ አንድ አገር  ልጆች ሳይሆን የተለያየን እንደሆንን አድርገን እንድናይ ነው የተደረገው። ሁላችንም በጎሳች በጎጣችን ጆንያ ውስጥ ገብተን፣ እንድንጠብ ነው የተደረገው። ከዚህም የተነሳ በጋራ ፣ በፍቅር፣ ያለንን በመከፋፋል ፣ አብረን በመብላት፣ በመተጋገዝ  ከመኖር ይልቅ እኛና እናንተ በሚል. ይሄ መሬት የኛ ነው እናነት መጤ ናችሁ በሚል እርስ በርስ እየተገዳደልን ነው።

ህወሃት ከመቀሌ ብትወገድም አሁን ህወሃትና ኦነግ በአገራችን የዘረጉት ፖለቲካ እስካልታገደ ድረስ፣ እኛ ኢትዮጵያዉያን የዘርና የኃይማኖት ልዩነቶች ሳይደረጉ ተከባብንረም በሁሉም የአገሪቷ ግዛቶች በነጻነት የመኖር፣ የመስራት፣ የመማር፣ የማስተማር፣ ህብት የማፍራት፣ የመመረጥና የመምረጥ መብታችን ካልተከበረ ፣ እንደ አገር የመቀጠል እድላችን በጣም የሰፋ ነው የሚሆነው።