በመቀሌ እንዳ ጊዮርጊስ የአየር ጥቃት መፈጸሙ ተነገረ

ዛሬ ረፋዱ ላይ በትግራይ ክልል ርዕሰ ከተማ መቀሌ ውስጥ የአየር ጥቃት መፈጸሙን የከተማዋ ነዋሪዎችና የቢቢሲ ዘጋቢ ከስፍራው ገለጸ።

BBC Amharic : ዘጋቢያችን እንደገለጸው የጦር አውሮፕላን ድምጽ በተሰማበት ጊዜ በነዋሪዎች ዘንድ መደናገጥ ተፈጥሮ የነበረ ሲሆን፤ በሰዎች ላይ ጉዳት አለመድረሱንም ገልጿል።

የአየር ድብደባየክልሉ ቴሌቪዥንም ሰኞ ኅዳር 07/2013 ዓ.ም ረፋድ 04፡45 ላይ ጥቃቱ መፈጸሙን ያረጋገጠ ሲሆን፤ የጥቃቱ ኢላማም በመቀለ ውስጥ በሚገኘው ቀዳማይ ወያነ ክፍለ ከተማ ውስጥ በሚገኘው እንዳ ጊዮርጊስ በተባለው አካባቢ መሆኑን ገልጿል።

ከሁለት ሳምንት በፊት ገደማ በተቀሰቀሰው የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊትና በትግራይ ልዩ ኃይል መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት ውስጥ መንግሥት በተመረጡ ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ የአየር ጥቃት እንደሚፈጽም አሳውቆ ነበር።

እስካሁን በተደረጉ የአየር ድብደባዎች የወታደራዊ አቅርቦች ማዕከላት ጥቃት እንደተፈጸመባቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ ባይቻልም የክልሉ ባለስልጣናት አንድ አውሮፕላን መትተው እንደጣሉ መግለጻቸው ይታወሳል።

አውሮፕላንበፌደራል መንግሥቱና ትግራይን የሚያስተዳድረው ገዢ ፓርቲ መካከል ለወራት የዘለቀው ውዝግብ በክልሉ በሚገኘው ሠሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመን ጥቃት ተከትሎ ወደ ወታደራዊ ግጭት መሻገሩ ይታወሳል።

በዚህ ግጭት በምድርና በአየር ከሚደረገው ዘመቻ ባሻገር የትግራይ ኃይሎች ባለፈው አርብና ቅዳሜ በሰሜን ኢትዮጵያ በሚገኙት በባሕር ዳርና ጎንደር ከተሞች እንዲሁም ጎረቤት አገር ኤርትራ መዲና ያሉትን የአየር ማረፊያዎች ኢላማ ያደረጉ የሮኬት ጥቃቶችን መፈጸማቸውን አረጋግጠዋል።

እስካሁን በተለያዩ አካባቢዎች ጦርነቶች እየተካሄዱ ሲሆን በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ የግንኙነት መስመሮች በመቋረጣቸው የደረሰው ጉዳትን በተመለከተ አስተማማኝ መረጃ ለማግኘት አዳጋች ሆኗል።