ለአያቶች መኖር የልጅ ልጆች መስዋዕት መሆን የለባቸውም። – ሌተናል ጄኔራል ዮሃንስ ገ/ሚካኤል

  • የትግራይ ሕዝብ የ80 እና 90 ዓመት ሽማግሌዎች ምክንያት ለሶስተኛ ጊዜ ልጆቹን ለጥፋት እንዲያቀርብ እየተገደደ ነው … ለአያቶች መኖር የልጅ ልጆች መስዋዕት መሆን የለባቸውም። ሌተናል ጄኔራል ዮሃንስ ገ/ሚካኤል
  • “በወንጀለኛው ቡድን አማካኝነት በመከላከያ ላይ የተፈጸመው የክህደት ጥቃት ከህወሓት በኋላ ያለች ኢትዮጵያን የምናይበት ነው” – ሌተናል ጄኔራል ዮሃንስ ገ/ሚካኤል
(ኢ ፕ ድ) – የህወሓት ወንጀለኛ ቡድን በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ የፈጸመው ጥቃት ከህወሓት በኋላ ያለች ኢትዮጵያን የሚታይበት መሆኑን ሌተናል ጄኔራል ዮሃንስ ገ/ሚካኤል አስታወቁ ።ጥቃቱ በትግራይ ሕዝብ ላይም የተፈጸመ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን አመለከቱ ።ሌተናል ጄኔራል ዮሃንስ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፤ ምንም እንኳን ህወሓት የፖለቲካ ድርጅት ቢሆንም ህወሓትን የሚመሩ ወንጀለኛ ስብስቦች ፖለቲከኛ መሆን ተስኗቸው ከተጠያቂነት ለመደበቅ ሕዝቡን አታልለው ወደ ትግራይ ሸሽተው ተቀምጠዋል።
Image may contain: 1 personቡድኑ ሰላም የሆነች ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ሕዝቦች በነጻነት ሊናገሩና ሊጠይቁ የሚችሉባት የትግራይ ክልል ከተፈጠረች ከተጠያቂነት እንደማያመልጡ ስለሚያውቁ ኢትዮጵያን ወደማተራመስ መግባታቸውን አመልክተው ፣ይሄን ተከትሎም የመጨረሻ ያሉትን የጥፋት ተግባር በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ እንደፈጸሙ አስታውቀዋል ። ይህ ተግባራቸው ግን ካሰቡት በተቃራኒ ተጉዞ ከህወሓት በኋላ ያለችውን ኢትዮጵያ ለማየት የሚያስችል ሆኗል ብለዋል።
እንደ ሌተናል ጄኔራል ዮሃንስ ማብራሪያ፤ ወንጀለኛ ቡድኑ ከትጥቅ ትግል ጀምሮ በትግራይ ህዝብ ላይ ሲሰራ የነበረውን ሴራ ከድል ማግስት በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ ሲፈጽም ቆይቷል። ለውጡን ተከትሎም የበዛ ወንጀሉ እረፍት ስለነሳው ሸሽቶ ሕዝቡን በማታለል መቀሌ ገብቷል። መቀሌ ከገባ በኋላ ግን ሁለት ዓመት ሙሉ ለሕዝቡ የልማት ስራ ከማከናወን ይልቅ ከ18 ዓመት በታች የሆናቸው ህጻናትን በመመልመል ልዩ ኃይል በማሰልጠን ህልውናውን የሚያቆይበትን መንገድ ሲያመቻች ቆይቷል።
ግፉ ሞልቶ ሲተርፍ አገር የማፍረስና የማተራመስ ምኞቱ ጫፍ ሲወጣ የእኔ ያልሆነች አገር ምንም ትሁን በሚል እሳቤው በመከላከያው ላይ ጥቃት መፈጸሙን አመልክተው፣ የትግራይ ሕዝብ ልጆችም በማያውቁትና ባላመኑበት ተግባር ውስጥ ለደመወዝና ጥቅም ብለው መስዋዕት እንዲሆኑ እያደረጋቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል።
” ይህ ወንጀለኛ ቡድን ከትጥቅ ትግል ጀምሮ ወደ ጦርነት ገብቶ አያውቅም። ቀድሞም መስዋዕት የሆኑን የምስኪኑ ሕዝብ ልጆች ናቸው። በዚህ መልኩ የትግራይ ምድር ቀድሞ በነበረው የእርስ በእርስ ግጭት፣ ቀጥሎ በተከሰተው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት፣ አሁን ደግሞ ወንጀለኛው ቡድን ራሱን ከተጠያቂነት ለማዳን ሲል በፈጸመው ጥቃት የግጭት አውድማ እየሆነች ነው ብለዋል።
በእነዚህ ወንጀለኞች የ80 እና 90 ዓመት ሽማግሌዎች ምክንያት ለሶስተኛ ጊዜ ልጆቹን ለጥፋት እንዲያቀርብ እየተገደደ ነው ያሉት ሌተናል ጄኔራል ዮሃንስ ፣ ለአያቶች መኖር የልጅ ልጆች መስዋዕት መሆን ስለሌለባቸው፤ ይህ ወንጀለኛ ቡድን የፈጸመው ጥቃት የቡድኑ ማብቂያ እና ከህወሓት በኋላ ያለችውን ኢትዮጵያ እንድናይ ማድረጉን አስታውቀዋል።
ይህ ተግባር የቡድኑ የወንጀለኝነትና ድንቁርና ውጤት ነው ያሉት ሌተናል ጄኔራል ዮሃንስ፤ ወደ እነሱ የሰበሰቡትን ጄኔራልና ኮሎኔል በመተማመን መከላከያው ላይ ጥቃት በመፈጸም እንዳሰቡት በተለያየ ምክንያት በእዛ አካባቢ የተከማቸውን የጦር መሳሪያ በእጃቸው አስገብተው ቢሆን ኖሮ በአገርና ሕዝብ ላይ ሊያደርሱ ይችሉ የነበረው ጉዳት ከባድ እንደነበር ጠቁመዋል።