- ኢትዮጵያ በትግራይ የምታካሂደው ህግን የማስከበር ዘመቻ የውጭ ጣልቃ ገብነት አያስፈልገውም -አምባሳደር ዣኦ ዢዩአን
EBC : ኢትዮጵያ በትግራይ የምታካሂደው ህግን የማስከበር ዘመቻ የውጭ ጣልቃ ገብነት እንደማያስፈልገው አዲሱ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዢዩአን አረጋገጡ።
–
አዲሱ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዢዩአን የሹመት ደብዳቤያቸውን ኮፒ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሬድዋን ሁሴን አቅርበዋል።
የሹመት ደብዳቤውን ኮፒ ባቀረቡበት ወቅት በሁለትዮሽ፣ ባለብዙ ዘርፍ ግንኙነትና በጋራ ጥቅም ዙሪያ መክረዋል።
–
በውይይቱ ወቅትም “ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ህግን ለማስከበር የምታደርገው ዘመቻ የውስጥ ጉዳይ እንደሆነ ቻይና ትረዳለች” ብለዋል አምባሳደር ሬድዋን።
–
የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዢዩአን በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት ህግን ለማስከበር የሚያካሂደው ዘመቻ የውጭ ጣልቃ ገብነት የማያስፈልገውና በኢትዮጵያ መንግስት አቅም የሚፈታ ጉዳይ እንደሆነ አረጋግጠዋል።
–
የቻይና መንግስትና የቻይና የግል ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያላቸውን የኢኮኖሚ ዘርፍ ተሳትፎ ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ተወያይተዋል።
–
አምባሳደር ሬድዋን ቻይና ለኢትዮጵያ ኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመከላከል ረገድ ያደረገችውን ወሳኝ ድጋፍ አድንቀው ምስጋና አቅርበዋል።
ወረርሽኙን ለመከላከል በሚደረገው ጥረትም ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር በመተባበር እንደምትሰራ ገልጸዋል።
–
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ባደረጉት ውይይትም፤ የግድቡ የድርድር ሂደት በውይይት ብቻ መፈታት እንዳለበት ተነጋግረዋል።
–
ለጊዜው የተቋረጠው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደቻይና የሚያደርገው በረራ ስለሚቀጥልበት ሁኔታም ተወያይተዋል።
አምባሳደር ዣኦ ዢዩአን በኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው አገራቸው ቻይናን ማገልገል መቻላቸው እንደሚያኮራቸው ገልጸዋል።
–
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋንም አዲሱ የቻይና አምባሳደር በኢትዮጵያ ስኬታማ ጊዜ እንደሚያሳልፉ ያላቸውን ምኞት መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።