አማራን የሚያገልና የሚጨቁን የፌዴራሊዝም አተገባበር ነው የነበረው!!

በኩር፤ ሐምሌ 23 ቀን 2010 ዓም

አማራን የሚያገልና የሚጨቁን የፌዴራሊዝም አተገባበር ነው የነበረው!!

 

ዶክተር ሲሳይ መንግሥቴ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግና አስተዳደር መምህር ናቸው:: በሰብዓዊ መብት ዙሪያም የረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕረግ አላቸው::
ዶክተር ሲሳይ በአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ በምክትል ሀላፊነት ያገለገሉ ሲሆን በቀድሞ ስሙ የኢህዴን (ብአዴን) ታጋይም ነበሩ:: ዶክተሩ የዚህ እትም እንግዳችን ናቸው::
መልካም ንባብ!

ስምዎ በተለየ ሁኔታ ከራያ ህዝብ ጋር ብዙ ጊዜ ይነሳል:: ምክንያቱ ምንድን ነው?

ተወልጀ ያደግሁ ራያ ውስጥ ነው:: በራያ ስማር በነበረው የፖለቲካ ትኩሳት ወደ ኢህዴን ገብቸም ታግያለሁ:: ኢህዴን /ብአዴን/ በነበርኩበት ጊዜ የራያን ህዝብ መብትና ጥቅም እንዲጠበቅ እታገል ነበር:: የራያ ህዝብ ፍላጐት ሳይጠየቅ በሁለት ክልሎች እንዲተዳደር ተደርጓል:: በ2005 ዓ.ም የራያ ህዝብ የማንነት ጥያቄ እና የማዕከላዊ መንግሥታት ምላሽ ከአፄ ዮሐንስ እስከ ኢህአዴግ የሚል መጽሀፍ ከጓደኛዬ ጋር ሆነን አዘጋጅተናል:: የራያን ህዝብ ታሪክ እና ተጋድሎም እያሳወቅሁ ነው:: የራያን ህዝብ ተጋድሎ ትግራዮች ደግሞ ቀዳማዊ ህዝብ ወያኔ ትግል የሚሉትን ታሪክ በተመለከተ በማስረጃ ሞግተናል:: ቀዳማዊ ህዝብ ወያኔ የራያ ህዝብ ታሪክ ነው:: በዚህ ጉዳይ ጽፌያለሁ፤ሞግቻለሁ:: ለዚህ ይመስለኛል ስሜ ከራያ ህዝብ ጋር ጐልቶ የሚነሳው::

የራያ ህዝብ ስነ ልቦናዊና ባህላዊ ቅርበቱ ከየትኛው ማህበረሰብ ጋር ነው?

የራያን ህዝብ ሠዎች በተለያየ መንገድ ይገልፁታል:: የራያ ህዝብ ስንል በድሮው የራያ ቆቦና አዘቦ አውራጃ የሚኖር ህዝብ ድምር ነው:: የራያነት ስነ ልቦና አለው:: ራያ የነ ጥላሁን ግዛው ሀገር ነው:: አማርኛ ይነገራል:: ትግረኛ የሚመስል ራያኛ ቋንቋ ይነገራል:: አገውኛ እና ኦሮምኛም በተወሰነ መልኩ ይነገራል:: አማርኛ የሚናገረው ግን ይበዛል:: የራያ ህዝብ በስነ ልቦና፤ በአብሮነት የጁ /ወሎ/ ከአማራ ህዝብ ጋር የቀረበ ስነ ልቦና አለው:: ከላስታ እንዲሁም ከዋግ ህዝብ ጋር የጠነከረ ግንኙነት አለው:: ለምሳሌ ኮረም ከዋግ ጋር የቀረበ ነው::

በራያ እና በሌሎች አካባቢዎች የማንነት ጥያቄዎች እስካሁን እንዳልተመለሱ ህዝቡ በመግለጽ እንዲመለሱለት ይጠይቃል:: የፌዴራል ስርአቱ እና ህገ መንግስቱ ነው ያልመለሰው ወይስ የአፈፃፀም ሂደቱ?

የፌዴራሉ ህገ መንግሥት የሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጥያቄ ይመልሳል:: ምቹ ሁኔታም ፈጥሯል:: በተግባር ሲገባ ግን የአፈፃፀም ችግር አለ:: በትግራይ ክልል የተካለሉ ራያዎች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ አይደለም:: የከተማ ከንቲባዎችም ሆነ የገጠር አስተዳደሮች ውስጥ ራያዎች የሉም:: ራያዎች ራያን አይመሩም:: በአማራ ክልል ያለው ራያ ግን የተሻለ ቦታ አለው:: ማንነቱ ተከብሮለታል:: በትግራይ ክልል የተካለሉ ራያዎች አንድ ቀን “ወይ ራሳቸውን ይችላሉ ወይም ወደ አማራ ክልል ይሄዳሉ” ብለው ያስባሉ:: የልማት ስራም አልተሠራም:: በአማራ ክልል የሚገኘው ራያ ግን ቀጥተኛ ተሳትፎ አለው:: የቆቦ ጊራና የመስኖ ልማት በአማራ ክልል ይገኛል:: ራያዎች ተጠቃሚ ናቸው:: በትግራይ ክልል የተካለሉት ራያዎች ግን ያለ ቋንቋቸው እንዲማሩም ይገደዳሉ::

የብሔር ፌዴራዝም በማንነት ላይ የተመሰረተ ነው:: ከሆነ ፌዴራሊዝሙ ለምን የማንነት ጥያቄን መመለስ ተሳነው?

ህገ መንግሠቱ በአንቀጽ 39 ማንኛውም ብሔረሰብ ራሱን ያስተዳድራል ይላል:: ነገር ግን በሽግግር መንግሥቱ ወቅት ክልሎች ሲዋቀሩ የተሟላ ጥናት አልተደረገም::
በጊዜያዊነት በሽግግር መንግስቱ የተካለሉት ሁሉ ክልል ሆነው ቀጥለዋል:: አከላለሉ በጥናት መመለስ ነበረበት:: በተለይ በአማራ እና በትግራይ አዋሳኞች ላይ በጊዜው የህወሐት ካድሬዎች አማራ ክልል ውስጥ ገብተው ይሠሩ ስለነበር የወልቃይት ፀገዴም ሆነ የራያ ህዘብ በዚህ ምክንያት ተካሏል:: የተወሰነ ትግርኛ የሚመስል የሚናገሩ ህዝቦች ያሉበት አካባቢ እና መሬቱ ለም የሆነውን ሁሉ የመጠቅለል አካሄድ ነበር::
ህገ መንግሥቱም ሆነ ክልሎች የተዋቀሩበት አዋጅ 7/84 በተሟላ መልኩ አልተተገበረም:: አንድ ሺህ ትግሬኛ ቃላት ተወስደው ከራያ ትግርኛ ጋር የተመሳሰሉት ከ200 ብዙ የሚዘሉ አይደሉም:: የራያ ትግርኛ እና ሌላው በጋራ የሚዋሰኑት ትንሽ ነው:: ከ70 እስከ 80 በመቶ የራያ ትግርኛ ከሌላው ትግርኛ ይለያል:: በስነ ልሳን ደግሞ አንድ ቋንቋ ከሌላው በ60 በመቶ ከተለየ የተለየ ቋንቋ ተደርጐ ይወሰዳል:: ይሄ ሁሉ ግምት ውስጥ አልገባም:: የህዝቡ ስነ ልቦና እና ማንነት በደንብ አልተጠናም:: አጠቃላይ በሀገሪቱ ይሄ ችግር አለ:: ከህንድ ተሞክሮ ቢወሰድ መልካም ነው:: ህንድ የፌዴራል ስርዓት ከመሰረተች 10 ዓመት እንኳን ሳይቆይ በወሰን አካባቢ ችግር ሲነሳ የድንበር ኮሚሽን አቋቁማ እንደገና አዋቅራለች:: አሁንም ጠቅላይ ማኒስትራችን እንዲህ አይነት ሀሣብ እንዳላቸው ሰምቻለሁ:: ለዚህ ደጋፊ እሆናለሁ ብየ አስባለሁ::

እርስዎ የኢህአዴግ ታጋይም፣ የፌዴራሊዝም መምህርም ነዎትና በሽግግር መንግስቱ ወቅት የአማራ ህዝብ ትክክለኛ ወኪል እንደነበረው የሚያስታውሱት ነገር አለ?

በወቅቱ የአማራን ህዝብ የሚወክል ፓርቲ አልነበረም:: ኢህዴን በዋናነት የሚንቀሳቀሰው በአማራ ክልል ነው:: የአማራ ክልል ህዝቦችን መርቷል:: በጊዜው ኢህዴን የአማራ ክልል ህዝቦችን ይወክላል ብለን እናምን ነበር:: ግን የአማራን ህዝብ በትክክል የሚወክል አልነበረም:: ጠንካራ ወኪል አልነበረውም:: ኋላ ላይ በፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት /መአህድ/ ተደራጀ:: ኢህዴን በ1986 ብአዴን ተባለ:: ስሙን ብአዴን ብሎ ይቀይር እንጅ የአማራን ህዝብ አይወክልም ነበር:: እኔ በዚህ ጉዳይ በ1993 ከህወሓት ለሁለት መሰንጠቅ ጋር ተያይዞ ብአዴን አማራን በትክክል እንደማይወክል እሞግት ነበር:: በተሀድሶው መድረክ ብአዴን አማራን እንደማይወክል እኔና ሌሎች ሞግተናል:: በ1997 ዓ.ም ተፎካካሪ ፓርቲዎች በስፋት የተንቀሳቀሱት በአማራ ክልል ነው:: ባለኝ መረጃ በወቅቱ ብአዴን 52 በመቶ ብቻ ነው አሸነፍኩ ያለው:: በወቅቱ ብአዴን ከሽንፈት የዳነው ምን ያህል ዴሞክራሲያዊ ሆኖ ነው የሚለው ሌላ ጥያቄ ሆኖ፤ በመጀመሪያው ምክር ቤት ሞልዓተ ጉባኤ ማሟላት ስላልቻለ ህገ መንግስት እስከ ማሻሻል ተደርሷል:: ከምርጫ 97 በኋላም ብአዴን በሌላ ክልል የሚኖርን አማራ እንዳልጠበቀው ጥያቄ አነሳ ነበር:: አማራ በየጊዜው ይፈናቀላል:: በሀረሪ የሚኖር አማራ ከሀረሪዎች ይበልጣል:: ሆኖም በአስተዳደሩ አማራ ውክልና የለውም:: ሀረሪን ኦሮሞና ሀረሪ ናቸው የሚያስተዳድሩት:: ኦህዴድ የተሻለ የመደራደር አቅም ስለነበረው ሀረሪ ላይ ውክልና አለው:: ብአዴን ከሀረሪ ሊግ ጋር መደራደር አልፈቀደም:: ቢኒሻንጉል ጉምዝ ከበርታ ቀጥሎ በቁጥር ሁለተኛው አማራ ነው:: ግን ወኪል የለውም:: እንዳውም ይፈናቀላል:: ከጉራ ፈርዳ፣ ከደቡብ ክልል አማራ ይፈናቀላል:: አሁንም አማራ መፈናቀሉ ቀጥሏል:: ወሰኑንም ብአዴን አላስከበረም:: እኔ ብአዴንን በተለያየ መንገድ የአማራን ህዝብ ጥያቄ እንዲመልስ በመጠየቄ ተስፋፊ፣ ትምክህተኛ የሚል ስም ተሰጥቶኛል:: በዚህ ምክንያትም ከብአዴን ራሴን አግልያለሁ::

በኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ሲፀነሰስ አማራውን ጨቋኝ፣ ሌላውን ተጨቋኝ በሚመስል መንገድ ፈርጇል:: መነሻው ምንድን ነው?

የፌዴራል ስርዓት በባህሪው ሶስት መንገዶችን ተከትሎ ይመጣል:: አንደኛው ሁለት ሀገር የነበሩ ህዝቦች አንድ ጠንካራ ሀገር ለመመስረት በፌዴራል ስርዓት ሲገናኙ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አንድ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት የነበራት ሀገር ክልል በመፍጠር የሚመጣ የፌዴራል ስርዓት አለ:: ሶስተኛው መንገድ ሁለቱንም አይነት ባህሪ ይዞ ሊመጣ ይችላል:: የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ስርዓት ወደ ስራ ሲገባ አንድ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት የነበረውን አገዛዝ በማስወገድ ህዝቦች በማንነታቸው ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ነው ያደረገው:: ከመርህ አንፃር ጥሩ ነገር ነው:: ግን ትልቁ ችግር የነበረውን አፋኝ ስርዓት ለማስወገድ በትጥቅ ትግል የተንቀሳቀሱት እነ ህዋሓት፣ ኦነግ… መነሻቸው የአማራ ገዥ መደብ ጨቋኝነት ነው:: 1950/1960/ የነበረው የፖለቲካ ትርክት የመደብና የብሔር ጭቆና አለ የሚል ነበር:: አሸናፊ ሆኖ የወጣው ቡድን የብሔር ጭቆና አለ የሚለው ነው:: የብሔር ጭቆና አለ ለሚለው ትርክት ደግሞ አማራን ጨቋኝ አድርገው እየሰበኩ የትግራይን ህዝብ አሰልፈዋል:: በኦነግ በኩል ደግሞ ነፍጠኛ አማራ የሚል ቅስቀሳ ስለነበር ምንም የማያውቀው ጭቁኑ አማራ ለመፈናቀልና ለመንገላታት ተዳርጓል::
ኢህዴን/ብአዴንም የአማራ ገዥ መደብ አለ ብሎ ማመኑ፣ የህዋሓት እና የኦህዴድ ጫና ትምክህተኛ ያሰኘኛል ብሎ በመስጋት ለአማራ ህዝብ ጥቅም መቆም ተስኖታል:: ሌላው ነባሩ የብአዴን አመራር አባላት የአማራ ተወላጆች አለመሆናቸው፣ ኢህዴን ከኢህአፓ የወጣ ህብረ ብሔራዊ ስለሆነ እንደ ኢትዮጵያ እንጅ እንደ አማራ አያስብም:: በመሆኑም የአማራ ህዝብ መሪ የለውም:: አማራ ክልል ሲዋቀር በዙሪያው ቦታ ተወስዶበታል:: ተሟግቶ የቆመለት መሪ የለውም:: የፌዴራል ስርዓቱ በባህሪው ሳይሆን በፈፃሚው ቸልተኝነት አማራው እንዲፈናቀል ሆኗል::
አንድ ወቅት ለአራቱም ክልሎች አመራር ስልጠና እንሰጥ ነበር:: ከኦሮሚያ እና ከደቡብ የመጡ አመራሮች አባይን ተሻግረው የደጀንን አርሶ አደር ባዶ እግሩን ቡትቶ ለብሶ ሲሄድ አይተው “ይሄ አማራ ነው ወይ?” ብለው ጠይቀውኛል:: በየቦታው እንደዚህ ያሉኝ የዞን አመራሮች ናቸው:: በአማራ ላይ የተሳሳተ ግንዛቤ ተፈጥሯል:: አማራን የሚያገል፣ የሚጨቁን የፌዴራሊዝም አተገባበር ነው ያለው:: በዚህ አማራው ከስልጣን ተገልሏል::
ህብረ ብሔራዊ በሆነች ሀገር ውስጥ የብሔር ፌዴራሊዝም መከተል ስህተት ነው?
ናይጀሪያ በመጀመሪያ ሶስት ክልሎችን ይዘው በቋንቋ ተካለው ነበር:: በኋላ ግን እየሰፋ መጥቶ ወደ መልካ ምድራዊ አከላለል ተቀይሮ ወደ 36 ክልሎች ደርሰዋል:: በናይጀሪያ በብሔር ላይ የተመሰረተ ፓርቲ ማቋቋም አይቻልም:: የናይጀሪያ እና የኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ስርዓት አይመሳሰልም:: በተወሰነ ደረጃ ከህንድ ይመሳሰላል:: የህንድ ክልሎች በቋንቋ ተመስርተዋል:: የህንድ የተሳካ ነው:: ስዊዘርላንድም በሀይማኖት እና በቋንቋ የተመሰረተ ፌዴራሊዝም ስርዓት ትከተላለች:: ዋናው ፌዴራሊዝም የሚጠይቀው ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ነው::
ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ ነው የጠፋው:: የዜጐች ፈቃደኝነት መጠየቅ አለበት:: ኢህአዴግ በባህሪው ዴሞክራሲያዊ ሊሆን አይችልም:: የላብ አደር አርሶ አደር አምባገነን መንግስት ለመመስረት ነው የተደራጀው:: የትጥቅ ትግሉ አምባገነናዊ ስርአትን ለማስፈን ነበር:: ነገር ግን ዓለማዊ ሁኔታው ገፍቶት አብዮታዊ ዴሞክራሲን እከተላለሁ አለ:: በሽግግር መንግሥቱ ወቅትም የዜጐችን ፍላጐት ለማክበር ሞክሮ ነበር:: ነገር ግን የትጥቅ ትግሉ ባህሪው ስለሚጐትተው ዴሞክራሲያዊ ለመሆን ይቸግረዋል::
በዘር ላይ በተመሰረተው ፌዴራሊዝም ውስጥ አማራ ሀገር ለማቅናት በየቦታው ስለሚኖር ተጠቂ ሆኗል:: ከዳግማዊ ቴዎድሮስ ጀምሮ አማራ ለኢትዮጵያ አንድነት በየቦታው ተበታትኗል:: በየቦታው የተበተነው አማራ በፖለቲካው እንዳይሳተፍ ሆኗል:: ለዚህ ዴሞክራሲ ያስፈልጋል::

ኢትዮጵያ ውስጥ ብሔርተኛ አለመሆን ይቻላል?

አይቻልም:: ከ1950/60/ ጀምሮ አሸናፊ የሆነው የብሔር ፖለቲካ ነው:: አማራዎችም በብሔር ፖለቲካ ተሳትፈዋል:: እነ ዋለልኝ መኮንን ኢትዮጵያ ውስጥ ስለብሄሮች ጽፈዋል:: የዋለልኝን ሀሣብ ግን ጠባብ ብሄርተኞች ያላግባብ ተጠቅመውበታል::
በዚህ ረገድ የአማራ ብሔርተኝነት ዘግይቷል:: ሌሎች ተጨቆን በሚል ሰበብ ቶሎ ብሔርተኛ ሆነዋል:: በነገራችን ላይ ጨቋኝ ገዥ መደብ ነበር:: ጨቋኙ መደብ ግን የአንድ ብሔር ሳይሆን ከትግሬም፣ ከኦሮሞም፣ ከአማራም … ወዘተ ሊሆን ይችላል::
አፄ ምኒሊክ አጋጣሚ የኢትዮጵያን አንድነት በማምጣት ረገድ ስለተሳካላቸው አማራ ገዥ መደብ ነው ማለት አይደለም:: ሁሉም ብሔር ተሳታፊ ነበር:: በኢትዮጵያ ወሳኝ የብሔር ገዥ መደብ የለም::

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የመደመር እሳቤ እና የአማራ ብሔርተኝነት የመጋጨት ዕድል ይኖራቸዋል ብለው ያስባሉ?

አማራው ኢትዮጵያን ያስቀድማል:: በእርግጥም አማራው ለኢትዮጵያ አንድነት ዋጋ ከፍሏል:: ስለዚህ ራሱን ከኢትዮጵያ ነጥሎ አያይም:: ነገር ግን ራስን መሆን የግድ ያስፈልጋል:: አማራ ነኝ:: ኢትዮጵያዊም ነኝ ማለት ያስፈልጋል:: ከሌሎች በበለጠ ለኢትዮጵያ ተቆርቋሪ መስሎ መታየት የለበትም:: የጋራ ሀገር ነው::
የአማራ መፈናቀል፣ በልማት ወደ ኋላ መቅረት፣ የእኩልነት ጥያቄ ቁጭት ፈጥሯል:: ይሄን ሁሉ ለማስተካከል ብሄርተኝነት ጐልቶ መውጣት ነበረበት:: አማራ ነኝ የሚል ሰው በዝቷል:: ብአዴን ውስጥ ያሉ አካላት ሁሉ ብሔርተኛ እየሆኑ ነው:: አሁን አማራው ወደ ቀልቡ ተመልሷል:: የአማራ ብሔርተኝነት ከኢትዮጵያዊነት ጋር አይጣላም:: አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ስለ ኢትዮጵያዊነት እያወሩ ነው:: በዚህን ወቅት አማራው ቀልቡን ገዝቶ ሁለቱን ማጣጣም አለበት:: ከክልሉ ውጭ ያለውን አማራ የሚወክል የፖለቲካ ስርዓት መፈጠር አለበት:: የየክልሉ አደረጃጀትና ህገ መንግስቱ መሻሻል አለበት::
የህዝቦቹ ፈቃደኝነት መጠየቅ አለበት:: በፖለቲካ ፓርቲዎች ፈቃድ ብቻ ማንነት መመስረት የለበትም::

ብዙ አማራዎች ራሳቸውን ኢትዮጵያዊ ነኝ ብለው ይገልፃሉ:: ይሄን እንዴት ያዩታል?

እኔ አማራ ነኝ:: በአማራነቴ ነው ኢትዮጵያዊነቴን የምገልፀው:: አማራነቴ ኢትዮጵያዊነቴን አይቀንሰውም:: እያንዳንዱ ግለሰብ መንስኤው ቤተሰብ ጐረቤት ማህበረሰብ ብሄረሰብ ብሄር እያለ ነው የሚሄድ:: ኢትዮጵያን ለማግኘት ብሔርን መሳብ አለብህ:: ኢትዮጵያዊነት የሁላችን ነው:: ለመደመር አማራ አማራነቱን ሊያጠናክር ይገባል:: አንዱን ማንነት ማኮሰስ ሌላውን ማንገስ ጐደሎነት ነው:: የሠው ልጅ የተደራረበ ማንነት አለው:: የአማራ ምሁራን ለአማራነታቸው ሊሰሩ ይገባል::

እርስዎ ከትጥቅ ትግሉ ከኢህዴን ጀምረው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የብአዴን አባል ነበሩ:: ብአዴን የአማራን ህዝብ የመወከል አቅሙን አሳድጓል ወይም ሊያሳድግ ይችላል?

ኢህዴን በወጣቶች የተመሰረተ ድርጅት ነው:: ኢህዴን ብአዴን የሆነው በ1986 ዓ.ም ነው:: ሆኖም የስያሜ እንጅ የተለየ ለውጥ ብዙም አልታየበትም:: በመሆኑም ብአዴን ህብረ ብሔራዊ / የኢትዮጵያ ህዝብና ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ ድርጅት ስለነበር የአማራን ብሔርተኝነት ማጐልበት ተስኖታል:: አማራ ከሀገሪቱ መጠቀም አልቻለም:: የአማራ ህዝብ የሚገባውን ያህል አልተጠቀመም::
ብአዴን በተለይም አዲሱ አመራር እየተራመደ ነው:: ለአማራ ህዝብ የሚጠቅም ሀሣብ ያመጣል ብየ አስባለሁ:: ምሁራንን አካቶ መስራት አለበት::
ብአዴን የመጣበትን መንገድ ላይመለስበት ሊያወግዝ ይገባል:: ብአዴን የራሱን ልጆች በነባር አመራሮቹ አማካኝነት ገፍቶ አስወጥቷቸዋል:: እነዚህን ሰዎች መመለስ አለበት:: ብአዴን ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር መስራት ይገባዋል:: በዴሞክራሲ ውስጥ የሀሣብ ልዩነት መኖሩ መብት ነው:: ብአዴን ለአዲሱ የፖለቲካ አካሄድ ራሱን ካላላመደ፣ የአማራ ህዝብ ሊሸከመው አይችልም:: ህዝቡ ነቅቷል:: በባህር ዳሩ ሠልፍ የኢፌዴሪ ም/ጠ/ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እንዲሁም የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአማራን ህዝብ የሚጠቅም ሀሣብ ሰንዝረዋል:: ለቃላቸው ካደሩ አማራን የሚጠቅም ስራ መስራት እንደሚችሉ አምናለሁ::

ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ!

እኔም አመስግናለሁ!


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE