በሴኪዩላሪዝም ሽፋን በሂጃባቸው ምክንያት ከስራቸው የተፈናቀሉ ሙተነቂብ እህቶቻችን ወደ ስራቸው እንዲመለሱ ተወሰነ።

በሂጃባችሁ ምክንያት ከስራ ገበታችሁ ለተፈናቀላችሁ ሙተነቂብ እህቶቻችን እንኳን ደስ አላችሁ!

ሙተነቂብ በመሆናቸው ከስራ ገበታቸው የተፈናቀሉት እህቶቻችን ወደ ስራቸው በክብር እንዲመለሱ ተወሰነ!

አቡ ዳውድ ኡስማን

ላለፉት አመታት በደቡብ ክልል በስልጤ ዞን መንግስት አክራሪነትን እዋጋለው በሚል ዘመቻ ሽፋን ሙስሊሞች ሃይማኖታዊ ድንጋጌዎቻቸውን እንዲጥሱና የሃይማኖት ነፃነታቸው ተገፎ እምነታቸውን የሚያዛቸውን ትዕዛዛት እንዳይፈፅሙ ሲደረግ ቆይቷል፡፡

ከሌሎች የሃገራችንን ዞኖች በተለየ የስልጤ ዞን ሙሉ በሙሉ ሙስሊም እንደመሆኑ መጠን በቀድሞ በፌደራል ጉዳዬች ሚኒስትር በኩል ከፍተኛ ጫና ይደረግብት የነበረ ዞን ነው፡፡
የዞኑ አመራሮች ሁሉም ሙስሊሞች ቢሆኑም ወይ ስልጣናቸውን አልያ ደግሞ እምነታቸውን እንዲመርጡ ሲገደዱ ነበር፡፡ በስልጤ ዞን በፀረ አክራሪነት ዘመቻ ስም ከተደረጉ ፀረ ህገ መንግስት ተግባራት መካከል ሙስሊም ሴት እህቶች ኒቃብ እንዳይለብሱ የሚከለክል ተግባር ነበር፡፡

ተወላጆቹ ሙሉ በሙሉ ሙስሊም በሆኑባት የስልጤ ዞን ከበላይ የመንግስት አካል በተሰጣቸው መመሪያ መሰረት አክራሪነትን እንዲዋጉ አልያ ከስልጣናቸው እንደሚነሱ ተዝቶባቸው ቆይቷል፡፡

ይደረግባቸው ከነበሩት ጫናዎች መካከል በዞኑ ኒቃብ የሚለብሱ ሙስሊም ሴቶች በአክራሪነት የተፈረጁ በመሆናቸው ኒቃባቸውን እንዲያወልቁ ማስገደድ እንዲሁም የዞኑ የመንግስት አመራሮችም የገዛ የትዳር አጋራቸውንም ቢሆን ኒቃቧን በማሶለቅ በዞኑ ኒቃብ የማሶለቅ ዘመቻውን በተግባር እንዲያሳዩ ሲገደዱ ነበር፡፡

በመንግስት መስሪያ ቤት የሚሰሩ ኒቃብ የሚለብሱ ሴቶች ኒቃባቸውን እንዲያወልቁ አልያ ደግሞ ከስራቸው እንዲሰናበቱ ተወሰነ፡፡ በዚህም በርካታ ሙተነቂብ እህቶች ከመንግስት መስሪያ ቤት እና ከትምህርት ገበታቸው እንዲፈናቀሉ ተደርጓል፡፡

ለሚሰሩበት የመንግስት መስሪያ ቤት ለቦታው የሚመጥን እውቀት፣ችሎታ እና ብቃት ቢኖራቸውም ሃይማኖታቸው ያዘዛቸውን ኒቃብ በመልበሳቸው ብቻ ከስራ ገበታቸው እንዲፈናቀሉ ተደርገው ቆይተዋል፡፡ኒቃብ በመልበሳቸው ብቻ ከስራ ተባረው የሚያስተዳድሩ ቤተሰባቸው የኑሮ ጫና እንዲከብዳቸው ተደርጓል፡፡

ኒቃባችንን ለዱኒያዊ ህይወት ስንል አናወልቅም በሚል በፅናት ከስራ መሰናበቱን ምርጫቸው ያደረጉ ቆራጥ እህቶቻችን መጀመሪያውኑ ከስራ ሲሰናበቱ ተወኩላቸው በአላህ ነበርና ዛሬ ላይ ቀን እንዲለወጥ አላህ አድርጎላቸዋል፡፡

የስልጤ ዞን ካቢኔ በኒቃብ ምክንያት ከስራ ገበታቸው እንዲባረሩ የተደረጉት እህቶች በሙሉ ወደ ቀድሞ ስራቸው እንዲመለሱ፣እስከዛሬ ድረስ ከስራ ታግደው በቆዩባቸው ጊዜያቶች በሙሉ ደሞዛቸው ታስቦ እንዲከፈላቸው በመወሰን ወደ ስራቸው እንዲመለሱ ወስኗል፡፡

ለጊዜያዊ ጭቆና በሚል የእምነታቸውን መመሪያ አንጥስም በሚል ለታገሱት እህቶቻችን አላህ(ሱ.ወ) ትዕግስታቸውን አይቶ በክብር ወደ ስራቸው እንዲመለሱ ጊዜውን ቀይሮላቸዋል፡፡

በእርግጥም ከችግር ቡኋላ ምቾት አለ፡፡ ትላንት ተበዳይ ነበሩ፡፡ ዛሬ ደግሞ ይቅርታ ተጠይቀው ወደ ክብር ቦታቸው እንዲመለሱ ሆኗል፡፡

በእምነትህ ፅኑ በመሆንህ ዛሬ ላይ የተጎዳህ ቢመስልህም አላህ ዘንድ የተከበርክ በመሆንህ ጊዜውን አላህ እንደሚለውጥልህ እርግጠኛ መሆን እንደሚገባህ ከነዚህ እህቶችም መማር ይገባናል፡፡

እህቶቻችን እንኳን ደስ አላችሁ

አልሃምዱሊላህ


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE