“ሆን ተብሎ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲቋረጡብን ተደርጓል” በሚል የተቆጡ ወጣቶች እርምጃ ወሰዱ።

በአማራ ክልል በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ፈንደቃ ከተማ ትላንት በተከሰተ ግጭት ሦስት ሰዎች መሞታቸውን እና አንድ ሰው በጠና መጎዳቱን የጃዊ ወረዳ የመንግሥት ኮሚዩኔኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ለዶይቼ ቬለ ገለጸ።

ግጭቱ የተቀሰቀሰው “ሆን ተብሎ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲቋረጡብን ተደርጓል” በሚል የተቆጡ የከተማይቱ ወጣቶች በወሰዱት እርምጃ መሆኑ ተነግሯል።

የፈንደቃ ከተማ ነዋሪዎች ትላንት ከቀኑ ሰባት ሰዓት ገደማ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት የኢንጂነር ስመኘው በቀለን የቀብር ስነ ስርዓት እየተከታተሉ ባለበት ሰዓት በከተማይቱ መብራት መጥፋቱ ወጣቶችን ማስቆጣቱን የጽሕፈት ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ተናግረዋል።

ለከተማይቱ መብራት የሚያሰራጨውን መስመር ሦስት ሰዎች ሲቆርጡ ታይተዋል በሚል ወጣቶቹ እርምጃ ወደ መውሰድ መግባታቸውንም አስረድተዋል። ከፍተኛ ድብደባ ከተፈጸመባቸው ሁለት ተጠርጣሪዎች መካከል አንደኛው ሲሞት ሌላኛው ክፉኛ ተጎድቶ ወደ ጃዊ ሆስፒታል ተወስዷል ብለዋል። ከተጠርጣሪዎቹ አንዱ ከወጣቶቹ አምልጦ ወደ ፖሊስ ጣቢያ በመግባት ሕይወቱን ማትረፉን አብራርተዋል።

በከተማይቱ ተቋርጦ የነበረው የኤሌክትሩሪክ አገልግሎት ከጥቂት ቆይታ በኋላ ቢጀምርም ብጥብጡ ግን እስከ ቀኑ 10 ሰዓት ድረስ መዝለቁን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው ገልጸዋል። የተቆጡ ወጣቶች በሌሎች ተጨማሪ ሁለት የሜቴክ ሠራተኞች ላይ በፈጸሙት ጥቃት በአጠቃላይ ሦስት ሰዎች ሞተዋልም ብለዋል። ፈንደቃ ሜቴክ እየተሳተፈ ባለበት የጣና በለስ የስኳር ፕሮጀክት አቅራቢያ የምትገኝ ከተማ ናት።

የወረዳው አመራሮች የፌደራል ፖሊስ እና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ወደ ከተማይቱ እንዲመጡ ካደረጉ በኋላ ከተማይቱ መረጋጋቷ ተነግሯል። ጉዳዩ ወደ ብሔር ተኮር ግጭት እንዳያመራ የሰጉት የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች ወጣቶችን ሰብስበው ሲያረጋጉ እንደነበር የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው አስረድተዋል። በፈንደቃ ከተማ ዛሬ መረጋጋት አለ የሚሉት ባለሙያው የመንግሥትም ሆነ የንግድ ተቋማት እንደወትሮው ሥራቸውን እያከናወኑ መሆናቸውንም ገልጸዋል።


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE