የአንድነት ኃይሉ ዕጣ (ሚኪ አምሐራ )

የአንድነት ኃይሉ ዕጣ (ሚኪ አምሐራ )

ዶ/ር አብይ እና ዲያስፖራዉ ጥሩ የሚባል ግንኙነት እያካሄዱ ነዉ፡፡ እነ ታማኝንና ሌሎች አክቲቪሰቶችን ማግኘቱ ለጠሚዉ የወደፊት ስራዉ ቀና ያደርግለታል፡፡እነ ታማኝ ትልቅ ቡድን የሚመሩ እና ሚዲያ ጨምሮ ትልቅ ተጽእኖ ያለዉ ሰዉ ነዉ፡፡ ኢሳትንና ኢሳት ዉስጥ የሚሰሩ ሰዎችንም ጠሚዉ ማሞጋገሱ በእርግጠኝነት የወደፊት ስራዉን እጅግ አቅልሎለታል፡፡ አሁን ባጠቃላይ የአንድነት ካምፑን በእጁ አስገብቷል፡፡ዲያስፖራዉ በጠሚዉ እጅግ ደስተኛ ነዉ፡፡ የፓርቲ አባላት እንኳን ጠሚዉን ላለማስቀየም በሚመስል ሁኔታ የሚጠይቁት የፖለቲካ ጥያቄ አስቂኝ ነበር፡፡ በዚህ መሃል ያሳዘነኝ አምባሳደር ተክለብርሃን ነዉ፡፡ ዝግጅቱን በተቻለ መጠን ለማጥበብ እና አንዳንድ ሰወች ከጠሚዉ ጋር እንዳይገናኙ የማድረግ ስራ ሰርቷል እየተባለ ሲወቀስ ሰንብቶ ነበር፡፡ ከዛም በላይ ግን ዶ/ር አብይ እነ ተስፋየን፤ እነ ገዱን እና አምባቸዉን ሲያመሰግን ፊቱ ይቀላ ነበር፡፡ ስለ ሌብነት እና አጎብዳጅነት ሲያወራም እንዲሁ፡፡ የተከለከለዉ ታማኝ መድረክ ላይ ሲወጣም እንዲሁ፡፡

የዶ/ር አብይ የአንድነት ሃይሉን በእጁ ማስገባቱ ግን የብሄር ፖለቲካዉን በደንብ ማጦዙ አይቀርም፡፡ በ 2012 ምርጫ ከኢህአዴግም ከሌሎች የአንድነት ፓርቲም በተሻለ የብሄር ፓርቲ እና ፖለቲካ የበለጠ ተቀባይነት ይኖረዋል፡፡ ለምን?

1.የአንድነቱ ቡድን ከዚህ በኋላ ከኢህአዴግ የተለየ የፖለቲካ አማራጭ የማምጣት አድሉ ጠባብ ነዉ፡፡ ለምሳሌ ኢህአዴግ እዉነተኛ ዲሞክራሲ ማራመድ ከጀመረ ለምሳሌ ነጻ ሚዲያ፤ ፍርድ ቤት፤ የምርጫ ሁኔታ፤ ወታደሩን ደህንነቱን እና የመሳሰሉትን ሪፎርም አድረጎ ሌሎች ተቋማትንም በሁለት አመት ዉስጥ ከፖለቲካ ነጻ አድርጎ ከመሰረተ የአንድነቱ ቡድን ከዚህ የተለየ የፖለቲካ ርዮተ አለም ወይም አጀንዳ አይኖረዉም፡፡ምናልባት ኢህአዴግ እና የአንድነቱ ቡድን የብሄር ፖለቲካዉን ለመቀነስ ሊተባበሩ ሁሉ ይችላሉ፡፡በዚህም የተነሳ ኢህአዴግ ከተፎካካሪ አገራዊ ፓርቲ በተሻለ ጠንካራ ሊሆን ይችላል፡፡ባጠቃላይ ኢህአዴግ የዲያስፖራዉን እና የአንድነት ፖለቲካ አቀንቃኙን አጀንዳ ተረክቧል በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካኝነት፡፡

2. የአንድነት ፖለቲካ የሚከተለዉ ቡድን በየብሄሩ ዉስጥ ያለዉን ችግር ለማንሳት እና አጀንዳ ለማድረግ ይከብደዋል፡፡ ዲሞክራሲ ካለ ሁሌም ቢሆን ሎካል ፖለቲከስ ጠንካራ ይሆናል፡፡ ሎካል ፖለቲካዉን ሊመሩ የሚችሉ የብሄር ድርጅቶች ከፍተኛ ተሰሚነት ይኖቸዋል ምክንያቱም በየአካባቢዉ ያለዉን ችግር እንደ ዋና አጀንዳ አድርገዉ የሚያነሱት ሰለሚሆን፡፡ ለምሳሌ የአማራን እንይ፡፡ ሃገረ አቀፍ ፓርቲ የወልቃይትን ጉዳይ አጀንዳ ያደርጋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ወልቃይት ግን ለአማራ ህዝብ የሞት የሽረት ነዉ፡፡ ስለዚህም አብን የዚህ አጀንዳ ዋና ተሸካሚ ይሆናል ህዝቡም እሱን የሚመርጥ ይሆናል ማለት ነዉ፡፡በኦሮሚያ በኩልም እነ ኦፌኮ የአካባቢዉን ችግር በተሻለ አጀንዳ ያደርጋሉ ማለት ነዉ፡፡ሲዳማ ስንሄድ የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ ያነገበ ፓርቲ ይመረጣል ከአንድነቱ ፓርቲ ይልቅ፡፡

3. ዲያስፖራዉ እና የአንድነት ፖለቲካዉ መሬት ላይ ያሉ ተጨባጭ ችግሮችን እያለባበሳቸዉ በመሆኑ እና ወይም ችግሮችን ነቅሶ የማየት ችግር ስላለ ህዝቡ ወደ ሌላ አማራጭ መዞሩ አይቀርም፡፡

4. የአንድነት ሃይሉ በዋና ዋና ከተሞች እና አንዳንድ ክልሎች ላይ የተሻለ ተጽእኖ መፍጠር የሚችል ቢሆንም በሚቀጥሉት ትቂት አመታት የአንድነት ፖለቲካ ሊደርስባቸዉ የማይችልባቸዉ ከተሞችና እና ክልሎች አሁንም በስፋት ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ የአንድነት ሃይሉ ትግራይ አካባቢ ተጽእኖ ሊኖረዉ አይችልም፡፡ ምክንያቱም ህወሃት በሃይልም ቢሆን ያን አካባቢ ተቆጣጥሮ ይቆያል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የአንድነቱ መሰረት የነበረዉ የአማራ ህዝብ በራሱ በስፋት ወደ አዲሱ ፓርቲ የሚዞር ይሆናል፡፡ ቀሪዉም ከብአዴን ጋር የሚጓዝ ይሆናል፡፡

የኔ ፕሪዲክሽን መንግስት በ 2012 ደርሶ ጥሩ ምርጫ ካካሄደ more democratic country but fragile government ይኖረናል ማለት ነዉ፡፡ ምናልባትም በኢትዮጵያ ታሪክ ልክ በሌሎች አገሮች እንደምናየዉ የ coalition government ይኖራል ማለት ነዉ፡፡ የዶ/ር አብይ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን እባካችሁ አንድ ጠንካራ ፓርቲ መስርቱ እና እንፎካከር የሚለዉ ዉትወታም ምናልባትም ብሄር ተኮር ፖለቲካዉን ለማስተንፈስ ይጠቅማል ብሎ ያሰበ ይመስለኛል፡፡ ኢህአዴግ እና አገር አቀፍ ፓርቲዎች ወጣም ወረደም የተቀራረበ ሀገራዊ ቪዥን ስለሚኖራቸዉ ከመቸዉም ጊዜ በበለጠ ኢህአዴግ አሁን የአንድነቱን ፖለቲካ ይፈልጋል ምክንያቱም አሁን ላይ ለዶ/ር አብይ ትልቁ ፈተና የብሄር ፖለቲካዉ ነዉ፡፡ለብሄር ፖለቲከኞች ደግሞ የአንድነት ቡድኑ ከኢህአዴግ ጋር መለጠፉ ለነሱ ትልቅ እድል ነዉ፡፡ምክንያቱም አማራጭ ሁነዉ ይቀርባሉ፡፡