በጣና ሐይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም ለማጥፋት ዘመቻ ሊጀመር ነው


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በጣና ሐይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም በአንድ ወር ዘመቻ ለማጥፋት ከነገ ሰኞ ጀምሮ ወደ ሥራ እንደሚገባ ተገለጸ።

BBC Amharic : የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ እንዳሉት ዘመቻው የሚከናወነው ከጥቅምት 09 እስከ ህዳር 09/2013 ዓ.ም ነው።

“የጣና ሐይቅን መጠበቅ እና ከአደጋ ነጻ መሆን አለበት” የሚል እምነት ክልሉ አለው ያሉት ዳይሬክተሩ የዘመቻው ዓላማ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ጣናን ከእምቦጭ በመታደግ ወደነበረበት መመለስ እና የህዳሴ ግድብንም ከእምቦጭ አረም ስጋት ነጻ ማድረግ ነው ብለዋል።

በሦስት ዞኖች፤ 9 ወረዳዎች እና አንድ የከተማ አስተዳደርን ጨምሮ በ30 ቀበሌዎች ላይ የእምቦጭ አረሙ ተስፋፍቶ 4ሺህ 300 ሄክታር የሚሆነው የሐይቁን ክፍልም አረሙ ወሯል።

ክልሉ ሐይቁንና ሌሎች የውሃ ውስጥ አካላትን የማልማት እና የመጠበቅ ኃላፊነት የተሰጠው ኤጄንሲ ከማቋቋም ባለፈ በበጀት እና የሰው ሃይል በመመደብ በተለያየ ጊዜ ሐይቁን ከእምቦጭ ለመከላከል መሥራቱን አስታውቀዋል።

በዚህም አረሙ እንዳይስፋፋ ማድረግ መቻሉን አስታውቀው ሆኖም እምቦጭን ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት በአካባቢው ማህበረሰብ እና ክልል ብቻ ማሳካት አይቻልም ብለዋል።

በዘመቻው ከሁሉም ክልሎች እና ከሁለቱ የከተማ መስተዳደሮች መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የምርምር ማዕከላት፣ የሲቪክ ማኅበራት እና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ይሳተፋሉ ተብሏል።

እምቦጭ የሚገኝባቸውን ቀበሌዎች እና ወረዳዎች በመከፋፈል በቀን ከ250 እስከ 300 ሰው በየቀበሌው የሚሠማራ ሲሆን ይህንን የሚያስፈጽም ኮሚቴም ተቋቁሟል።

ክልሎች እና የከተማ መስተዳድሮችም ተከፋፍለው ሊያስወግዱት የሚችሉት ድርሻ እንደሚሰጣቸው ለማወቅ ተችሏል።

ለዘመቻው 106 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ እና ይህንም ከተለያዩ አካላት ለማሰባሰብ መታቀዱም ተገልጿል።