ግብፅ የተቀመጠችበትን ዛፍ ነው እየገዘገዘች ያለችው፡፡ – ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ

ግብፅ የተቀመጠችበትን ዛፍ ነው እየገዘገዘች ያለችው፡፡ – ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ
(አብመድ) ኢትዮጵያ ቀጂ ግብፅ ደግሞ ጠጪ ሆነው ዘመናትን አልፈዋል፡፡ ጋን ኢትዮጵያ ሆና ሳለች ጠጪዋ ግን ግብፅ ነበረች፡፡ ኢትዮጵያ ትደግሳለች ግብፅ እንግዳ ትሸኛለች፡፡ ኢትዮጵያ በጨለማ ትናውዛለች፤ ግብፅ በኢትዮጵያ ፋኖስ ትበራለች፡፡ ከኢትዮጵያ አብራክ የሚወጣው ግዮን (ዐባይ) ምን አልባትም ዘመን ከተቆጠረ እርሱም ከተፈጠረ ጀምሮ የኢትዮጵያን አፈር እያጋዘ ወደግብፅ ይወስድም ነበር፡፡
ግዮን የኢትዮጵያን ለም አፈር እያፈሰ ምድረ በዳ የነበረችዋን ግብፅን አረሰረሰ፤ የሰው መኖሪያ እንድትሆንም አደረገ፡፡ ግዮን የኢትዮጵያን አፈር ይዞ ሲኮበልል ግብፅ ስትቀበል ዘመናት አልፈዋል፡፡ በዚህ ሁሉ ዘመን ታዲያ ግብፅ የኢትዮጵያ አርሶ አደር ላሟን ቀልቦ ከጥጃው ለተጋራው ወተት ‘‘ሺህ ሁኚ!’’ ብሎ እንደሚመርቀው ‘‘ኢትዮጵያ ሆይ ኑሪ፤ ምድርሽም ይለምልም’’ ብላ አታውቅም፡፡ ይልቁንስ ከዓባይ ውኃ ላይ ጥቂትም ቢሆን እንዳትጨለፊ ትላታለች እንጂ፡፡
በግብፅ አለማመሥገንና እብሪተኝነት የሚናደዱት የኢትዮጵያ ነገሥታት በተለያዩ ዘመናት ዓባይን ለመገደብ ወይም አቅጣጫ ለማስቀዬር አስበው ነበር፤ ነገር ግን ግብፅ ስትማፀን እየተዉ ከእኛው ዘመን ላይ ደረሰ፡፡ ኢትዮጵያውያን ከዛሬ ዘጠኝ ዓመት በፊት ከዓባይ በረከት በትንሹ ለመቅመስ ግድብ መሥራት ጀመሩ፡፡ ከወትሮውም ዓባይን ይነኩብኛል በሚል ስጋት ስትንገበገብ የነበረችው ግብፅ ግድቡ እንዲደናቀፍ የማታደርገው ጥረት አልነበረም፤ ይሄም አልተሳካም፤ ቶሎ እንዳይጠናቀቅና ከተቻለ ውኃ እንዳይዝም ጥረት አድርጋለች፤ ይህም ሕልሟ ቅዠት ሆኗል፡፡ በሕዳሴ ግድብ ውኃ አሞላልና አለቃቅ ዙሪያ ግብፅ ከኢትዮጵያና ከሱዳን ጋር ለዓመታት የዘለቀ ድርድርና ምክክር አድርጋለች፡፡ ነገር ግን እስካሁን ድረስ ራሷን ብቻ በሚጠቅመው ሐሳብ በመቆሟ ሙሉ ለሙሉ ስምምነት ላይ ሳይደረስ ቀጥሏል፡፡
በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል ስላለው ታሪክ ከአብመድ ጋር ቆይታ ያደረጉት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍ መምህሩ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ የግብፅንና የኢትዮጵያን ታሪካዊ ግንኙነት በማስረጅ ሊገልፅ የሚችል ጽሑፍ እየጻፉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ‘‘አሁን ግብፅን የተቆጣጠሯት ዐረቦች የግብፅን ምድር የረገጧት በቅርብ ነው’’ ይላሉ ፕሮፌሰሩ፡፡ ኢትዮጵያውያን ዐረቦችን ለ4 ሺህ ዓመታት እንደሚቀድሟቸው ነው የገለጹት፡፡ ኢትዮጵያውያን የዓባይን ወንዝ ተከትለው በመሄድ በግብፅ ሀገር እንደመሠረቱና እንዳቀኑም ተናግረዋል፡፡ ‘‘ግብፅን እግዚአብሔር ፈጠራት፤ ኢትዮጵያውያን አበጇት፣ ሠሯትም’’ ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ፡፡
በግብፅ ምድር ንጉሥም ካህንም የነበሩት ኢትዮጵያውያን መሆናቸውንም ያስረዳሉ፡፡ በግብፅ የቆሙት ፒራሚዶች፣ የግብፃውያን ጥንታዊ ፊደል ኬይሮግራፊክስን የመሠረቱትም ኢትዮጵያውያን ናቸው ብለዋል፡፡ ዓለም የተፈላሰፈበትን ፍልስፍና የጀመሩትም በግብፅ ሲኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ነግረውኛል፡፡ ፍልስፍና በግሪክና ሮም ተጀመረ የሚባለውም ውሸት ነው፤ የሚናገር አፍ ጠፍቶ እንጂ ጀማሪዎቹ ኢትዮጵያውያን ናቸውም ነው ያሉኝ፡፡ የግሪክና የሮም ፈላስፋዎች ኢትዮጵያውያንን ፍለጋና ከእነርሱ ጥበብ ለመቅሰም ወደኢትዮጵያውያኑ ይመጡ ነበር፡፡ ‘‘ከእነርሱ ተምረውም ነው ፈላስፋ የሆኑት’’ ብለውኛል፡፡ ‘‘ግሪክ እንዲውም የፍልስፋናና የፈላስፋ ጠላት ነበረች’’ ያሉት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ከኢትዮጵያውያን ተምሮ የተመለሰውን አርስቶትል የተባለውን ፋላስፋ ‘‘የውጭ ሀገር ትምህርት አመጣህብን’’ እያሉ ያሳድዱት እንደነበርም ያስረዳሉ፡፡ ዛሬ ላይ ግን አስተማሪዋን ኢትዮጵያን ረስተው የፍልስፍና ፈር ቀዳጆች እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡
ግብፅን ኢትዮጵያውያን እንደመሠረቷትና የግብፅ ስልጣኔ የሚባሉት ሁሉ የኢትዮጵያውያን ስለመሆናቸው ሲያስረዱ ‘‘የታሪክ አባት እየተባለ የሚጠራው ሄሮዳተስ በግብፅ የነበሩትን ስልጣኔዎች ለማዬት ከግሪክ አስንቶ መጣ፡፡ በሀገሪቱ የነበረውን ጥበብና ስልጣኔም አዬ፡፡ በሥፍራው ያገኛቸውን ካህናትና ሌሎች ነዋሪዎች ‘‘እናንት ሰዎች ከዬት ነው የመጣችሁ?’’ ብሎ ጠዬቃቸው፡፡ ‘‘እኛስ ኢትዮጵያውያንን ነን፤ ዘራችንም ይኼው’’ ብለው የዘር ሐረጋቸውን ቆጠሩለት፡፡ በብራና የተመዘገበውን የዘር ግንዳቸውንና ታሪካቸውን እንዳሳዩት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ገልፀዋልኝ፡፡ ሄሮዳተስም ‘‘በዚያች ምድር የሚኖሩ ሰዎች ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ነገሩኝ፣ አሳዩኝም፣ እኔም አረጋገጥኩ፤ ሁሉንም የሠሯቸው ኢትዮጵያውያን ናቸው’’ በማለት መመስከሩንም ነው ፕሮፌሰር ፍቅሬ ያስገነዘቡት፡፡
እንደፕሮፌሰር ፍቅሬ ግብጻውያን ኢትዮጵያን ተዋግተው አሸንፈው አያውቁም፤ ከቱርክ ጋርም አብረው ተሸንፈው ነው የተመለሱት፡፡ በግብፅ ዛሬ ላይም የሚገኙት ጥንታውያን አጽሞችና ጌጣጌጦች የግብጻውን ሳይሆኑ የኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ‘‘ኢትዮጵያውያን ዓባይን የመጠቀም መብት አለን፡፡ እነርሱ ‘ድሆች ናችሁ’ ይሉናል፤ እኛ ግን ከየትኛው ዓለም የተለዬ የተፈጥሮ ሀብት ያለን ሀብታሞች ነን፡፡ ችግሩ አለመጠቀማችን ነው’’ ሲሉም ዐባይን ጨምሮ የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን መጠቀም እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡
‘‘ግብፅ የተቀመጠችበትን ዛፍ ነው እየገዘገዘች ያለችው’’ ያሉት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ኢትዮጵያውያን ግብፅን ስለሠሯት እንደአንድ የኢትዮጵያ አካል እንደሚመለከቷትም ገልጸዋል፡፡ ‘‘እኛ የሠራናትን ሀገር እኛው አናፈርሳትም’’ እያሉ እንጂ ሀብታቸውን ለመጠቀም ሳያውቁ ቀርተው እንዳልሆነም ያመላክታሉ፡፡ ‘‘ኢትዮጵያ ሀብቷን የመጠቀም መብት አላት፤ ልጠቀም እያለች ያለችውም በፍትሐዊነት ነው፡፡ ግብፅ የኢትዮጵያን ሐሳብ ልትጋራና ልትወስድ ይገባል’’ ነው ያሉት፡፡
ፕሮፌሰሩ በቅርብ በሚወጣው መጽሐፋቸው ግብጻውያን ኢትዮጵያንና ታሪኳን በደንብ እንዲያውቁና ኢትዮጵያም በግብፅ ላይ ያላትን ታሪክ በግልጽ እንደሚያሳዩ ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ታሪካቸውን በሚገባ ማጤንና ማወቅ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ስልጣኔን ለዓለም ያሳዬች፣ ዘምና ያዘመነች፣ ቀድማ ያስከተለች ሀገር ናትና፡፡