በደምቢዶሎ በምጥ የተያዘችዋን እርጉዝ ሴት የገደሉት የኦሮሚል ልዩ ፖሊሶች መሆናቸው ታውቋል።

የዘግናኙ ወንጀል ፈጻሚዎች እነማናቸው?
በትናንትናው ዕለት እኩለ ሌሊት አከባቢ በምጥ ጣር ተይዛ ወደ ደምቢዶሎ ሆስፒታል በመሄድ ላይ በነበረችው የ35 ዓመት ወጣት ላይ ስለተፈጸመው ዘግናኝ ግድያ ያጋራሁዋችሁ መረጃ ነበር።
ቀጥሎ ያለውን ተጨማሪ መረጃ(follow up) ያገኘሁት የእስር አጋሬ ከነበረው ‘Lammi Beenyaa’ ገጽ ላይ ሲሆን መልዕክቱንና መረጃውን ከአፋን ኦሮሞ ወደ አማርኛ አጠር አድርጌ በመመለስ ላካፍላችሁ።
ወ/ሮ ብርሃኔ ማሞ ከደምቢዶሎ አምስት ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ሜጢ የህክምና ጣቢያ ከደረሰች በሁዋላ ከምጧ ከባድነት የተነሳ በጣብያው ልትረዳ ስላልቻለች ሪፈር የተባለች ሲሆን፤ ሲስተር ሲቲና የተባለችው የህክምና ባለሙያ ሪፈር ከመጻፏ በፊት ለከተማው የአምቡላንስ ሹፌር ብትደውልም አሽከርካሪው ፈቃደኛ ሳይሆን ይቀራል።
ለሰዮ ወረዳ የጤና ቢሮ ሃላፊ ለአቶ ጫላ ዋቅጅራና ለምክትላቸው ቢደወልም ሁለቱም ስልካቸውን አይመልሱም። ከዚህ በሁዋላ አማራጭ ያጡት የነፍሰ ጡሯ ቤተሰቦች ባጃጅ ተከራይተው ጉዞ ወደ ደምቢዶሎ ሆነ።
– በሕዝብ ገንዘብ የተገዛ አምቡላንስ ለዚህ የችግር ቀን ካልሆነ ለመቼ ሊሆን ነው? አምቡላንስ እንዳይንቀሳቀስ የከለከለውስ ማነው?
ይህች ባጃጅ ደምቢዶሎ ከተማ ስትገባ በኦሮሚያ ፖሊስ ልዩ ሃይል ተኩስ እንደተከፈተባት የቄለም ወለጋ የጸጥታና ደህንነት ም/ሃላፊ የሆኑት አቶ ጸጋዬ ዋቅጅራ ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ አረጋግጠዋል። ለክስተቱ መንስኤ የነበረውም የከተማዋ የሰዓት ዕላፊ እስካሁን ያለመነሳቱ መሆኑንና ድርጊቱን ሳያጣሩ የፈጸሙት ፖሊሶች ሁኔታውን ካወቁ በሁዋላ በመደናገጥ ተጎጂዎቹን ወደሆስፒታል እንዲወሰዱ ቢያደርጉም እጅግ ዘግይተው ነበር።
በተኩሱ በምጥ ጣር ላይ የነበረችው ወ/ሮ ብርሃኔ ህይወቷን ስታጣ ድጋፍ ሲያደርጉላት የነበሩት የቤተሰቧ አባላት የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት ደርሶባቸዋል። በዛሬው ዕለትም ፍትሕን የሚጠይቁ ሰልፈኞች በደምቢዶሎ ከተማ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
የዞኑ የጸጥታ ቢሮ ድርጊቱን ያወገዘ ቢሆንም ዘግናኙን ወንጀል የፈጸሙት የፖሊስ አባላት ማንነት ስለሚታወቅ በአስቸኳይ በቁጥጥር ስር ውለው ለፍርድ እንዲቀርቡ ተጠይቋል። ፍትሕ ካልተበየነ ግን ሕዝቡ በራሱ መንገድ ፍትሕን ለማረጋገጥ ሊንቀሳቀስም ይችላል።
(የፎቶ መግለጫ ዛሬ በደምቢ ዶሎ የተደረገ የተቃውሞ ሰልፍ )
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ያስብ፤ ሕዝቧን ይባርክ!


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE