የታጠቁ ኃይሎች እስካሉ ድረስ ሰላም ሊሰፍን አይችልም !


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


  • “የታጠቁ ኃይሎች እስካሉ ድረስ ሰላም ሊሰፍን አይችልም፡፡” ምሁራን
  • በኢትዮጵያ የበሬ ወለደ ትርክቱ መሬት ላይ ያለ ነባራዊ ሁኔታን አይተካም፡፡
  • የፖለቲካ መዘውር የጨበጡ አካላት የፈጠሩት ምናባዊ ደዌ እንደሆነ መምህሩ ጠቅሰዋል፡፡
  • ኢሕአዴግን ጨምሮ የቅርብ ጊዜያት የኢትዮጵያ መንግሥታት የነበረውን አሻራ በማጥፋት ሀገርን እንደ አዲስ ለመመሥረት ሲፍጨረጨሩ ተስተውሏል፡፡
 (አብመድ) ኢትዮጵያን ምድረ ቀደምት በመባል እንድትጠራ ያደረጋት የሰው ልጅ መገኛ መሆኗ ብቻ አይደለም፡፡ የታሪክ እና የሥልጣኔ መብቀያ፣ የደጋጎች፣ የአስተዋይ እና ሰላም ወዳዶች፣ በክብራቸው ለመጣባቸው አልደፈር ባይ ጀግኖች፣ የጥበበኞች እና የአዋቂዎች፣ በጥቅሉ የመልካሞች መፍለቂያ በመሆኗም ጭምር እንጂ፡፡
ከስልጣኔ ማማ ላይ የደረሱ የዓለም ሀገራት የሀገረ መንግሥት ግንባታ ኢትዮጵያ ትመራበት የነበረው ሥርዓት የወለደው መሆኑን የታሪክ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፤ ሰነዶችም ያመላክተዋል፡፡ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና የቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል ተመራማሪና መምህር አየነው ማሞ (ዶክተር) እንዳሉት ጥንት ኢትዮጵያን ኃያላን ከሚባሉ ሀገራት መካከል ከቀዳሚዎቹ ተርታ እንድትሰለፍ ያደረጋት የመሪዎች እና የሕዝቦች መቻቻል፣ መከባበር እና መተባበር ነበር፡፡ ይህም ተፅዕኖ ፈጣሪነቷንና ዓለም አቀፍ ተሰሚነቷን በመጨመር በቅኝ ግዛት ሥር ከነበሩ የአፍሪካ ሀገራት በእጅጉ እንድትለይ አድርጓታል፡፡
ይሁን እንጂ በጊዜ ሂደት በዕድገት ማማ ላይ የደረሱ ሀገራትና ኢትዮጵያ የሄዱበትን መንገድ ልዩነት ውጤቱን ብቻ በማየት ለመረዳት በቂ ነው፡፡ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በሥነ ዜጋ እና ሥነ ምግባር ትምህርት ክፍል የሰላምና ደኅንነት ረዳት ፕሮፌሰር ግርማ መኮንን እንዳሉት ደግሞ አውሮፓውያን የቀደመ መንገዳቸውን ይዘው መቀጠላቸው፣ ካለ ፈጥፋታቸው መማራቸው፣ መልካም ተሞክሯቸውንም አስፍተውት መጓዛቸው አሁን ላሉበት ደረጃ አድርሷቸዋል፤ ይህ ልምድ ግን በኢትዮጵያ የለም፡፡ ኢሕአዴግን ጨምሮ የቅርብ ጊዜያት የኢትዮጵያ መንግሥታት የነበረውን አሻራ በማጥፋት ሀገርን እንደ አዲስ ለመመሥረት ሲፍጨረጨሩ ተስተውሏል፡፡ ሀገረ መንግሥት ምሥረታውን ለአንድነትና ለሀገር ዕድገት ሳይሆን ለግጭት በሚሆን መልኩ ያበጁ የፖለቲካ ተሳታፊዎች መኖራቸውንም ረዳት ፕሮፌሰር ግርማ አብራርተዋል፡፡
አስተያዬት ሰጪዎቹ እንዳሉት የፀጥታ ችግር መንስኤዎች በርካታ ናቸው፤ የሀገረ መንግሥት ምሥረታ ሥርዓቱም ለዚህ በጉልህ ይነሳል፡፡ የሰላምና ደኅንነት መምህሩ ግን በዚህ ሐሳብ ፈጽሞ አይስማሙም፡፡ በዕድገት ማማ ላይ ከፍ ብለው የታዩ ሀገራት በሀገረ መንግሥት ምሥረታ ሥርዓታቸው ከኢትዮጵያ ጋር እንደሚመሳሰሉም አስረድተዋል፡፡ እንደየዘመኑ የሚለያዩ ቢሆንም በሀገር ምሥረታ ሂደት ሚያጋጥሙ ውጣ ውረዶችና ስህተቶች በእነዚያ ሀገራትም ደርሰዋል፡፡ ከስሕተታቸው ትምህርት ወስደውበታል እንጂ በኢትዮጵያ ደረጃ የግጭት ምንጭ እንዲሆኑ ተደርገው በመዋቅር ደረጃ አልተተገበሩም፡፡ ይህም ተጨማሪ የተስፋ እና የድል ብርሃን እንዲጎናጸፉ አስችሏቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የበሬ ወለደ ትርክቱ መሬት ላይ ያለ ነባራዊ ሁኔታን አይተካም፡፡ ይልቁንም የፖለቲካ መዘውር የጨበጡ አካላት የፈጠሩት ምናባዊ ደዌ እንደሆነ መምህሩ ጠቅሰዋል፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያውያን በጠንካራ ትሥሥር ዘመናትን አልፈው መምጣታቸው ማሳያ አድርገው ያቀርባሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ትርክቱ ቅቡልነት ያገኘ ይመስላል፡፡ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ሥርዓቱ እና የጥራዝ ነጠቅ ምሁራን ኃይል አሰላለፍም ሀገሪቱን ተፈታትኗታል፡፡ የፖለቲካ ተዋንያን የፈጠሩት ዋልታ ረገጥ ትርክትም ለትውልዱ ጽንፈኝነትን አለማምዶታል፡፡ ሕገ-መንግሥታዊ እና መዋቅራዊ መሠረት ማግኘቱም ችግሩን አባብሶታል፡፡ የፖለቲካው የኃይል አሠላለፍ በአማራጭ ሐሳብ ላይ ሊመሠረት ሲገባው አንዱ ሌላውን በጠላትነት ፈርጆ እንዲነሳም በር ከፍቷል፡፡
በዚህም ሃይማኖትን እና ብሔርን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች መልካቸውን እየቀያየሩ ይቀሰቀሳሉ፤ የሰዎች ሕይወት መጥፋት፣ መቁሰል፣ ለንብረት ውድመት፣ ለመፈናቀል እና በሕዝቦች መካከል ጥርጣሬ መፈጠር ምክንያትም ሆኗል፡፡
መንግሥት የዜጎችን ሰላም የማስጠበቅ ኃላፊነት እስካለበት ድረስ ጊዜያዊና ዘላቂ የመፍትሔ አማራጮችን መፈለግ ይኖርበታል፡፡ በዘላቂነት ሊተገበሩ ከሚገባቸው ተግባራት መካከል ሕገ-መንግሥቱን ማሻሻል፣ የሰዎችን የአስተሳሰብ ዓድማስ ማሳደግ፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች አደረጃጀት እና እንቅስቃሴ ልጓም ማበጀት፣ የብሔርተኝነት ነባራዊ ሁኔታን ማስተካከል እንደሚገኙባት ምሁራኑ ይጠቅሳሉ፡፡ ሕገ መንግሥት ማሻሻል ብቻውን መፍትሔ ስለማይሆንም የሰዎችን አስተሳሰብ መቀየር እንደሚገባ መክረዋል፡፡
በወቅታዊነትም ተዓማኒና ሰላማዊ ምርጫ በማድረግ ሕዝባዊ ቅቡልነት ያለው መንግሥት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ በየዕለቱ በፍርሃት እና በሰቆቃ የሚኖሩ፣ ሀብት ለማፍራት የሚፈሩ መኖራቸውን በማመላከትም በተለይ ከአማራ ክልል ውጪ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች በፖለቲካል ኢኮኖሚ የመወሰን መብታቸውን ማስከበር እንደሚገባም ተመክሯል፡፡ ለዚህም የአማራ ክልል መንግሥት የመደራደርና አጀንዳ የማስቀመጥ አቅሙን ማሳደግ እንደሚኖርበት ጠቅሰዋል፡፡
የሰላምና ደኅንነት መምህሩ “የታጠቁ ኃይሎች እስካሉ ድረስ ሰላም ሊሰፍን አይችልም” ብለዋል፡፡ የየክልል እና ፌዴራል መንግሥታት አካባቢዎችን ከታጠቁ ኃይሎች ነጻ ማድረግን፣ ሰላማዊ ውይይት ማድረግን፣ የሰዎችን በሰላም ወጥቶ መግባት ስጋት ማረጋገጥን፣ ያልተመለሱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፍትሐዊነት ጥያቄዎችን በጊዜ መመለስ ችግሮቹን ለመከላከል በመፍትሔነት እንዲጠቀሙባቸውም መክረዋል፡፡
የማኅበራዊ አንቂዎችን መካረር ማስቀረትና የፀጥታ ችግር የፈጠሩ አካላትን ተጠያቂ በማድረግ ፍትሕን ማረጋገጥ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ የሲቪክ ማኅበራት፣ የሃይማኖት አባቶች እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በዕሴት ግንባታ ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩም መክረዋል፡፡ የሥራ ዕድል ፈጠራን ማስፋፋትና የወጣቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ በማሳደግ የቤት ሥራ መስጠት ተገቢ እንደሚሆንም አመላክተዋል፡፡ ለዚህም የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚናቸው የጎላ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ይህንን በማድረግም ሁሉም ኢተዮጵያዊ ለሀገሩ እኩል አተያይ እንዲኖረው በማድረግ የጋረ ሥዕል ይዞ ለመጓዝ እንደሚያግዝ አብራርተዋል፡፡ የሀገሪቱን ዕጣ ፈንታ በማመቻቸትም መሠረታዊ እና ሁለንተናዊ የለውጥ ተስፋ እንደሚፈነጥቅ ጠቁመዋል፡፡