የተደፈሩ አንበሶች ፤ የከተማ ቅርሶች

“የተደፈሩ አንበሶች” ስንታየሁ ሀይሉ

ከጊዜያት በፊት የኢቲቪ ጋዜጠኛ ከነበረው ወዳጄ ደራሲ ዳዊት ንጉሱ ተቀምጠን ይህንን ጠየቀኝ

“የአዲስ አበባ ቀለም ምንድነው ? ”

ስለሸገር የመጡልኝን ምላሾች ባቀርብም ትክክል አልነበርኩም። እሱ ቀጠለ
” ድሬዳዋን ስታስብ የፈረስ ጋሪዎችና ጣፋጮች፣ ባህርዳርን ስታስብ ባለዘንባባ የመንገድ አካፋዮች፣ አዋሳን ስታስብ ሀይቅና ባይስክሎች፣ ሀረርን ስታስብ ነጭ ግንብና ታክሲዎቿ (የመኪኖቹ ስም ጠፋኝ) ትዝ እንደሚለን ሁሉ አዲስ አበባ ደግሞ በአንበሳ አውቶቢሶች ትታወሳለች፤ ያ የከተማዋ ቀለም ነው።” ብሎኝ ያላሰብኩትን የከተማ ቅርስ አስተዋወቀኝ።

አንበሳ አውቶቢስ ለሸገር ህዝቦችም ሆነ ለእንግዶች ብዙ ትዝታ እና ጥቅም የሰጠ መገልገያችን ነው። ከታሪፉ ቅናሽነት፣ ካለው ተደራሽነት፣ ከሚጭነው የሠው ብዛት እና ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ጋር በተለይ በመንግስት ስራተኞችና በተማሪዎች ተመራጭና ያለን አንድ አማራጭ ነበር።

የጠብቅነው የአውቶቢስ ቁጥር ሲመጣ እናቱ ከገበያ እንደመጣችለት ህፃን በደስታ ሰፍ ብለን ከመሳፈር ጀምሮ፤ የቆጠብነውን የኪስ ገንዘብ “ሿ ሿ” ተስርተን በሀዘን ባዶ ኪስ ሆነን እስከመውረድ እንዲሁም ለታላላቆችና ለሴቶች በክብር ወንበር ከመልቀቅ በግፊያና በወሬ አሳስቆ ቺክ እስከመጥበስ ያደረሱ ብዙ ትዝታዎች ያሉበት የአዲስ አበባ ቀለም አንበሳ አውቶቢስ ነው።

የሆነ ሆኖ ዛሬ ይህ አንበሳ አውቶቢስ አርጅቶ እና በከፊል በቢሾፍቱ ባስ ተተክቶ በወሩ ወላልቆ ከአገልግሎት ውጪ ከመሆኑም በላይ ከሠሞኑ በ#sheger_fm ላይ የሠማሁት ከባድ የቀን ጅቦች ዝርፊያ ሳዳምጥ ያረጀን አንበሳ ከዝንብ መጫወቻነት የሚያድነው የአንበሳው ባለቤትና የአንበሳውን ጉልበት በደጉ ጊዜ የተጠቀመበት ህዝብና መንግስት ይመስለኛል።

– ብዛታቸው 120 የሆኑ ሊብሬ የሌላቸው አውቶቢሶች መገኘታቸው
– ከ24 ሚሊዮን ብር በላይ ለውድመት የተዳረጉ መቀያየሪያዎች መበስበሳቸው
– ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ የተገዙ መለዋወጫዎች አገልግሎት ማቆማቸውን ይህንን ሁሉ ብልሹ አሰራርና ሙሰኝነት ስትሰማ አዲስ አበባ ማነው አስተዳዳሪዋ ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን።

 

በተያያዘ ወሬ ሌላው የአዲስ አበባ ትዝታ የሆነው የ6ኪሎው አንበሳ ጊቢም በተመሳሳይ የቀን ጅቦች ቁጥጥር ውስጥ ውሎ በእድሳት ስም ከሚደረጉ የጊዜና የበጀት ቅጥፈቶች ተጨማሪ በአንዲት የሽቦ ሳጥን ውስጥ ለሚያኖሩት አንበሳ ቁመና በመጨነቅ “በዶክተር ትዕዛዝ” ከሚበላው ስጋ ላይ ፈርቅና ሙድ እየያዙ መሆኑንም በ#etv ሠምተናል።

☆አዲስ አበባ በቀለምና ትዝታዋ ትኑር !!!☆


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE