የመደመር ተግዳሮቶች!? ( ከኬና ቀኖ)

ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ከመጡ ወዲህ በተደጋጋሚ ከምንሰማቸው ቃላት ዋነኛው መደመር የሚለው ነው፡፡ ትርጉሙም፤  በጠቅላይ ሚኒስትሩ በአጽንኦት ተብራርቷል። በፍቅርና በይቅርታ፣ ወደ አንድነትና መግባባት እንድንመጣ ለማሳሰብ ተጠቅመውበታል፡፡

ይሁን እንጂ መልካም ነገሮች ፈተና እንደሚኖራቸው ሁሉ መደመርም በተለያዩ መንገዶች በእጅጉ እየተፈተነ ይገኛል፡፡ ከፈተናው የጉልህ ድርሻ የሚወስደው የኛ የኢትዮጵያውያን የተቃርኖ ትርክት ነው፡፡ በተቃራኒ የቆሙና ጽንፍ የረገጡ አተያዮቻችን!
ይህንን ተቃርኖ ሁልጊዜ በሚያጋጥሙን ትናንሽ ሁነቶች፣ ለምሳሌ እገሌ የሚባል ዘፋኝ እንዲህ አይነት ባንዲራ ያዘ… ልንመልሳቸው በማንችለው የታሪክ ስህተቶች ምክንያት እየተናቆርንና እየተጨቃጨቅን መቀጠል እንደሌለብን አምናለሁ፡፡ ከዚህ አንጻር እንዴት ተቃርነን ሳይሆን ተግባብተን መደመር እንደምንችል  ለመጠቆም እሞክራለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ሀገር ምስረታን ያከናወኑት አፄ ምኒልክ፤ የግንባታውን ዘርፍ፣ ሁሉንም የሀገሪቱን ህዝቦች በሚያረካ መልኩ እንዳልፈጸሙት፣ ብዙዎቹ የታሪክ ምሁራን ይሞግታሉ፡፡  አፄው ከባድ የሆነውንና የመጀመሪያውን ዘርፍ ስላከናወኑ፣ ግንባታው ከሳቸው ይልቅ በተከታታይ ከመጡት ገዢዎች ይጠበቅ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ፤ አሁን ላይ ቆመን እንድትገነባ በምንፈልግበት ሁኔታ ሳትገነባ ቀረች፡፡ ብዙ ቁርሾዎች እንዲፈጠሩም ዕድል አገኙ። አብዛኛውም ተገለልን ብሎ አማረረ፡፡ ይህም ሄዶ ሄዶ፣ ኤርትራን አስገነጠላት፡፡ ሌሎቹም ይቺን ዳንዲ ተመኙ፡፡ እንዲህ አይነት ስሜቶች አሁንም ድረስ እኛ ዘንድ አሉ፡፡ ጉዳዩን ክደን ወይም ሸሽተን የትም አንደርስም፤ተግባብተን መፍትሔ መፈለግ እንጂ!
የኛ ነገር አብዛኛው በተቃራኒ መቆም ሆኖ አልፏል። አሁንም ከዚህ እንዳልወጣን የሚያሳዩን ምልክቶች አሉ። አንድ ሀገር ነው ያለን፡፡ በብሔራዊ ምልክቶቻችን ግን እንቃረናለን! ሀገራችን አንድ ናት፡፡ ነገር ግን በሀገራዊ ጀግኖቻችን አንግባባም! አንድ ሀገር ነው ያለን፡፡ ሆኖም በብሔራዊ የበዓላት ቀናት አንስማማም! የሁላችን ሀገር ኢትዮጵያ ናት፡፡ በታሪክ ግን  እንቃረናለን! ይህ ተቃርኖ እንግዲህ ሀገሪቱ በትክክል አለመገንባቷን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ ይህ በሽታችን በጊዜ ካልተፈወሰ፣ ለሁላችንም የሚበጅ አይደለም፡፡ አንድ ታዋቂ ምሁር፤ የኢትዮጵያን ህዝብ ለመግለፅ፣ የሹፌሮችን ምሳሌ በመውሰድ፣ አንድ ሹፌር ሌላኛው እንዳያልፍ መንገድ ከዘጋበት፣ ራሱም ለመቆም  እንደሚገደድ ያስታውሰናል፡፡ እነዚህ ተቃራኒ ትርክቶቻችን፤ በተለያዩ ኩነቶች ምክንያት በየጊዜው እያገረሹ፣ የክርክርና የጭቅጭቅ አጀንዳ ሲሆኑ ይታያል፡፡ እውነት ነው መከራከራችን፣ መወያየታችን፣ ወደ አንድ ግብ ሊወስደን ይችል ይሆናል፡፡ እንደዛ ከሆነ የሚበረታታ ነው፡፡ ሀገር በመነጋገርና በመወያየት ትገነባለችና! ይሁን እንጂ እንዲሁ ጎራ ለጎራ ተከፋፍለን መናቆር፣ አምና ያሉትን ዘንድሮም መድገም፣ እሰጣ-ገባ ውስጥ መግባት ውይይት ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ መግባባትን ሳይሆን የባሰ መቃቃርን ነው የሚጋብዘው። ስለዚህ እነዚህ ተቃርኖዎቻችንን ቦታ ማስያዝና ለወደፊቱም እንዳይረብሹን ለማድረግ ወገባችንን አጥብቀን መነሳት አለብን፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ፤ ከዚህ በኋላ ሊያፈርሳት የሚችል ምንም አይነት አደጋ የለም ካልን፣ የተሳሳተ ግምት ሊሆን ይችላል፡፡ አሁንም ኢትዮጵያን ሊያፈርሳት የሚችል የሸመገለ ተቃርኖ አለ፡፡ የገመድ ጉተታው ፖለቲካ አሁንም አልተቋጨም፡፡ ሸውራራ እውነታዎችና ትርክቶች በዙሪያችን ከበውናል፡፡ የከፋፈለን እገሌ ነው ምናምን የምንለው ብቻ አይደለም፤ በራሳችንም ተከፋፍለናል፡፡ አሁን ግን እርምጃችን ወደ መደመር ነው!! ያሉንን እሴቶች ይዘን አንድ ላይ መጨመር፤ የበለጠ ለመጠንከር- መተባበር! የኢትዮጵያን አንድነት ከአለት የጠነከረ መሰረት እንዲኖረው ከፈለግን፣ ልንሰራቸው የሚገቡን ብዙ የቤት ሥራዎች እንዳሉብን ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለብንም፡፡ ለዚህም አዲስ የሀገር ግንባታ ፕሮጀክት፣ እንቅስቃሴ መጀመር ይገባናል፡፡ ለወደፊቱም የማይናወጥ ቢቻል ሁሉም፣ ካልተቻለ፣ አብዛኛው የሀገሪቱ ህዝቦች የሚስማሙበት አይነት ግንባታ፡፡ ይህን ለማከናወን ወደ ኋላ ሄደን የምናገኘው ነገር የለም፤ ወደፊት እያየን የምንገነባትና ገናና የምናደርጋት ሀገር እንጂ!
ሰሞኑን በታዋቂ አርቲስቶቻችን ሥራዎች፤ በአንዳንድ ግለሰቦች ንግግርና ባንዲራን በመሳሰሉ ምክንያቶች ስንነታረክ ነበር፡፡ በዚህም የተለመደውን ትንተናዎች አንብበናል፡፡ የሰማነውን የመልስ ነቆራ ደግመን ሰምተናል፡፡ አሁን ግን እንዲህ አይነቱ መነቋቆር፣ በዐቢይ ስም ይብቃ!
አሁን ተቃርኖአችንን እንዴት እንቋጨው? ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሆን ዘንድ የሚከተሉትን ምክረ-ሀሳብ እሰጣለሁ፡- 1) የአዕምሮ ዝግጅት፡- አዕምሮአችንን ለነጻ ውይይትና ጨዋ ንግግር ዝግጁ ማድረግ፡፡ ከኛ አዕምሮ ውጪ ሌሎች ቢሊዮን አዕምሮዎች በዚች አለም አሉ። ሁላችንም እንደ ግለሰብ በአስተሳሰብ እንለያያለን፡፡ ለነገሮች እኩል መረዳት የለንም፡፡ ሌሎች የሚሉትን ለመስማት አስፈላጊ ከሆነም ለመቀበል፣ ከራሳችን ከሆነ አስተሳሰብም ጭምር ፈቀቅ ለማለት ዝግጁ መሆን አለብን፡፡ ወደ ስሜታዊ ግልቢያ የሚወስደን ምንም አይነት ልዩነት ሊኖር አይችልም፡፡ ሁሉንም አይነት ሀሳብ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆን የስልጣኔ ምልክት ነው፡፡ አንድ ነገር ላይ ችክ ማለት ደግሞ ቆሞ ቀርነት ነው፡፡ “እኔ አያቴ ነኝ” ብሎ አጉል ፉከራ! አላያችሁም እንዴ ዶ/ር ዐቢይ፣ የሁሉንም ሀሳብ በፈገግታ ሲያዳምጥ? አልተመለከታችሁም እንዴ በተቃራኒው ከቆሙ ሀይሎች ጋር በፍቅር ሲያወራ? እስኪ ከሳጥናችን ወጥተን የሌሎች ኢትዮጵያውያንን ሃሳብ  ለመስማት እንዘጋጅ- ኢትዮጵያን የምንወዳት ከሆነ! 2) እውነታን መቀበል፡- ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚለው፤ እውነት አርነትን ታወጣለች! ኦሮሞም፡- dhugaan afaan qaban funyaaniin dubbatti  (እውነት አፏ ቢያዝ ባፍንጫዋ ትናገራለች) ይላል፡፡ አንዳንድ እውነታዎች መራራ ናቸው፡፡ ላይጣፍጡን ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ እንድንፈወስ ልንውጣቸው ይገባል፡፡ “መንጌ ሀገር ወዳድ ነው” ያለው እውነቱን እንደሆነ ሁሉ፣ “መንግስቱ  ጨፍጫፊ ነው” ያለም እውነቱን እንደሆነ ልንቀበል ይገባል፡፡ የሌሎቹንም እንዲሁ፡፡ ለአንዱ እውነት የሆነው ለሌላው ላይሆን ይችላል፡፡ እውነት አንፃራዊ ናትና፡፡ ስለዚህ እንድንደመር ያለን ብቸኛው አማራጭ እውነትን መቀበል ነው፡፡ ምን ይደረጋል ያለውን አንቀይር ነገር! 3) ወደ መሃል መምጣት፡- ወደ መሃል መንገድ ለመምጣት የራስህን ኢጎ ቀነስ ማድረግ ይጠይቃል፡፡ ከዚህ በፊት ችክ ያልክበት፣ የፎከርክበት፣ በጌረርሣ የገለፅከውንና የዘፈንክለትን አንዳንድ አቋምህን እንድታሻሽል የግድ ይላል፡፡ ለምሳሌ ይሄ ነው ባንዲራ ብለህ የጨፈርክበትን፣ ባንዲራው ይሄ ቢሆን ደስ ይለኛል- አንተስ? ወደሚለው እንድትለውጥ ያስገድዳል፡፡ ወደ መሃል መምጣት ባዶ ጉራና ቀረርቶን ትተህ፣ ስድቡን እዛ ማዶ አስቀምጥተህ፣ በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ በጨዋ ቋንቋ  እንድትወያይ ይፈልጋል። ወደ መሃል መምጣት በጥላቻ፣ በመናናቅና በቂም- በቀል መንፈስ በፍፁም ሊሳካ አይችልም! የተሳካ መግባባት ሊመጣ የሚችለው ውይይቱ፤ በፍቅርና በቅንነት መንፈስ ሲታጀብ ብቻ ነው፡፡ ዐቢይ  ኢሳያስን ያንበረከከው፣ ኤርትራውያንን የደስታ እንባ ያስነባው  በምን ነበር? በፍቅርና ቅንነት አይደለምን? ስለዚህ እኛ የተቃርኖ ግርዶሽ የጋረደን፣ የያ ትውልድ ወራሾች- የዛሬው ባለቤቶች በፍቅርና በቅንነት እንወያይ፡፡ 4) የነገው ላይ ማተኮር፡- የዚህ ትውልድ ሰዎች ሥራችን መሆን ያለበት ጀነራል ዋቆ ጉቱ እና አጼ ኃይለስላሴን ማስታረቅ አይደለም! ያ የአያቶቻችን ሀላፊነት ነበር። የኛ ሥራ ቱፋ ሙና እና አፄ ምኒልክን ማግባባትም አይደለም! ያ የቅድመ – አያቶቻችን ነበር፡፡ የኛ ቀዳሚ ስራ መሆን ያለበት፣ አሁን አንድ ላይ ያሉትን፣ እነ ኬና ቀኖ እና ፍሬንዶቹን( አለሙ እና ተወልደ…) እንዴት በአንድነት ሆኖ የድሃውን ኑሮ አሻሽሎ፣ ኢትዮጵያን ለውጦ፣ የአፍሪካንም ጨለማ መግፈፍ የሚችሉበት ሁኔታ መፍጠር ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ ማለት ታሪክ ምንም አይጠቅምም ማለት አይደለም፡፡ ታሪክማ ለትምህርታችን ነው- በጎውን ለመድገምና ከመጥፎው ለመጠንቀቅ! ነገር ግን መልካሙ ሰው ኦቦ ለማ መገርሣ እንዳሉት፤ ወደ ኋላ እያየን ወደፊት መሄድ አንችልም ነው ነገሩ፡፡ ትኩረታችን ወደፊት…ነገ…ከነገ ወዲያ! 5) የጋራ ማንነትን መገንባት፡- አዕምሮአችንን ለለውጥ ካዘጋጀን፣ በፍቅርና ቅንነት የታጀበ ውይይት አድርገን መግባባትን ከፈጠርንና ዋና ቁምነገርን፣ የነገዋ ኢትዮጵያ ላይ ካደረግን፣ የጋራ እሴቶቻችን ላይ ሰርተን፣ የጋራ ማንነታችንን ልናጎለብት እንችላለን፡፡ከዛ የሚያናቁሩን አጀንዳዎቻችን መሰረታቸው ይናዳል። የባንዲራው፣ የታሪካችን፣ የጀግኖቻችን፣ የብሔራዊ ቀናት፣ የቋንቋዎቻችን፣ የአስተዳደር አከላለላችን ሁሉም በየተራ ይፈታሉ! የጋራ ማንነታችንን በሚያስማማን መልኩ እንገነባለን፡፡ የኔ ብቻ ይሁን የሚለው አይሰራም! የኔ ብቻ ለሚስት እንጂ ለሀገር አይሰራም። ሀገር የሁላችን ናት! የጋራ እሴት ስንገነባ፣ አንተ የምትወደው እንኳን ባይሆን የምትጠላው አይሆንም፡፡ የምትወደው ነገ ከሚጠፋብህ፣ የምትጠላው ከአንተ ዘንድ ቢከርም ይሻልሃል፡፡
ለማጠቃለል፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ በተቃራኒ ጎራ ቆሞ በመናቆር የታወቀ ነው፡፡ ይህ ነገር በኢህአዴግ ዘመን በ11% ከአደጉ  ዘርፎች አንደኛው ነው፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ከመጡ ወዲህ ለጊዜው ረገብ ቢልም፣ በትናንሽ ነገሮች ለማገርሸት ሲከጅል እያየን ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ተቃርኖ አንድ ቦታ እንዲቆም ኢትዮጵያውያን መላ ሊያበጁለት ይገባል፡፡ በሰለጠነ መንገድ፡፡ እኔም በዚህ አጭር ጽሑፍ አጠቃላይ በሆነ መልኩ ሊወሰዱ የሚገቡ እርምጃዎችን ለመጥቀስ ሞክሬአለሁ፡፡ እነዚህን እርምጃዎች ከተገበርን የዶ/ር ዐቢይ  መደመር እውን ይሆናል፡፡ካልሆነ መደመራችን እኩል የሆኑ ቁጥሮች ግን ፖዘቲቭና ነጌቲቭ ከሆኑ፣ ድምራቸው ዜሮ እንደሚሆነው፣ ተደምረን ምንም እንሆናለን፡፡ ስለዚህ ተቃርነን ሳይሆን ተግባብተን እንደመር!!!
መልካም የመደመር ጊዜ!!
የአዘጋጁ ማስታወሻ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡