አርቲስት አልአዛር ሳሙኤልና የደቡቡ ርእሰ መስተዳደር ኤርትራውያንን በማባረር ዘመቻ ወቅት

ቅምሻ !! ኢትዮጲያዊ ነኝ እያልኳቸው ኤርትራዊ ነህ ይሉኛል ፤ ሩሲያዊው ደራሲ በ1/8ኛ ደም በግድ ኢትዮጲያዊ ነህ ይሉታል

ከሃያ ዓመታት በፊት የኢትዮ-ኤርትራ ግጭት ሲጀመር፡ የነበረው የማባረር፣ የወከባና የትርምስ ጊዜን ዛሬ ላይ ሆኜ ሳስበው ቢያሳዝንም፡ በርካታ አስቂኝ ፍጻሜዎች ነበሩት፡፡ ምንም እንኳ ያለፈን ታሪክ አሁን ማንሳቱ ተገቢ ባይሆንም፡ አዝናኝና አሰተማሪ ሰለሆነ ቢቀረብ ምንም ክፋት የለውም፡፡

ታዲያ በዛ ቀውጢ ዘመን ከየቤታችን ተለቅመን፡ ፖሊስ ጣቢያ ከተሰበሰብን በኋላ፡ የአዲስ አበባ ኤርትራውያን ማቆያ ወደ ሆነው ሸጎሌ ተወሰድን፡፡ እዛ ስንደርስ እጅግ በርካታ ኤርትራዊያን ግቢ ውስጥ እንደ ፈንዲሻ ተበትነዋል፡፡ ብዙዎችን አውቃቸዋለው፡፡ የቅርብ ወዳጆቼ የተቀበሉኝ ክፍል ውስጥ፡ በአጋጣሚ ታዋቂው ተዋናይና ደራሲ አልኣዛር ሳሙኤል ነበር፡፡ የሚገርመው ነገር በወቅቱ እሱ ታስሮ እያለ ኢቲቪ በ120 የመዝናኛ ፕሮግራሙ፡ የአልአዛር ሳሙኤል ድርሰት የሆነ ተከታታይ ፊልም ያስተላልፍ ነበር፡፡ ይህ ለኢትዮጲያ ኪነ ጥበብ አጅግ በርካታ ምርጥ ሰራን የሰራ አርቲስት፡ በትውልድ ኤርትራዊ ቢሆንም፡ ኤርትራ ሄዶ በቅጡ እንኳን የማያውቃት፡ ተወልዶ ካደገበት ኢትዮጲያ በግድ ኤርትራዊ ነህ ተብሎ ከእኛ ጋር ታስሮ ነበር፡፡ እናም አንድ ቀን እየተጫወትን ሳለ ድንገት፦
.
“ይገርመሃል እኔ ኢትዮጲያዊ ነኝ እያልኳቸው አይደለህም ኤርትራዊ ነህ ይሉኛል፡፡ ሩሲያዊው ደራሲ አሌክሳንደር ፑሽኪን አንድ ስምንተኛ ኢትዮጲያዊ ደም ቢኖረው፡ በግድ ኢትዮጲያዊ ነህ ይሉታል !”

ሲል የተነገራት የምሬት ምጸት፡ በጣም ነበር በወቅቱ ያሳቀኝ፡፡ ደግነቱ ግን ከጥቂት ቀናት በኋላ እኛን ወደ ሌላ ቦታ ሲያዘዋውሩን፡ እሱ ግን እዛው ቆይቶ እንደተፈታ ቆይቼ ሰማው፡፡ አልኣዛር ሳሙኤል ማዘጋጃ ቤት የቲያትር መድረክ ላይ ጥረሱን ነቅሎ እድሜውን የፈጀ፡ አሁንም ድረስ በጥበብ ውስጥ እየተገ የሚገኝ ምርጥ ተዋናይ ነው፡፡ አልኣዛር ኦቴሎ ላይ ‘ቃሲዮን’ ሆኖ የሰራ ሲሆን፡ ከነ አበበ ባልቻ፣ ሱራፌል በጋሻው፣ ፍቃዱ ተክለማርያም ወዘተ ጋር፡ ከሶስት አሰርተ ዓመታት በላይ በኪነጥበብ ዘርፍ በርካታ ቴያትሮች፣ ፊልሞችና ተከታታይ የቴሌቪዥን ሙቪዎች ላይ በጥሩ ፐርፎርማንስ የተወነ፡ አሁንም በመተውን ላይ የሚገኝ ምርጥ አርቲስት ነው፡፡
.
ሌላው ደግሞ የሚገርመኝ፡ የደቡብ ክልል ርዕሰ መሰተዳድር የነበረው አባተ ኪሾ ነው፡፡
ከፌደራል መንግስት ሁሉም ክልሎች ኤርትራውያንን አንዲጠርዙ በተላለፈው ሴርኩላር መሰረት፡ አባተ ኪሾ ከደቡብ ክልል ኤርትራውያንን ሰብስቦ ወደ አዲስ አበባ እንዲልክ ሲታዘዝ፡ ትግርኛ ተናጋሪውን ሁሉ መልቀም ይጀምራል፡፡ ያኔ እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው የትግራይ ተወላጆች ታፈሰው ነበርና ” ኧረ እኛ ኢትዮጲያጲያውያን ነን፡ አድዋ አክሱም መቐለ ሽሬ ወዘተ…ነው አገራችን ቢሉ ማን ሰምቷቸው፡፡ አባተ ኪሾ ፦
“ለኔ ሁላችሁም ትግሬዎች ናችሁ፡ እንዴት ብዬ አውቃችኋለው፡ ሰለዚህ እዛው ራሱ መለስ ዜናዊ ይለያችሁ !” በማለት የነበሩትን ጥቂት ኤርትራዊያንና በርካታ ቁጥር ያላቸውን የትግራይ ተወላጆች ሰብስቦ ወደ አዲስ አበባ ላከ፡፡ አሰቂኝ የደቡብ ክልላዊ መንግስት ቀልድ ነበር !
.
እንሆ ዛሬ ያሁሉ የጦርነትና የመለያየት ምዕራፍ ተዘግቶ፡ አዲስ የፍቅርና የመደመር ምዕራፍ ከፍተን፡ የተለያየው እየተገናኘ ፤ ያለፈውን ለመዘከር በመብቃታችን፡ ፈጣሪ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ሰላም ለምድራችን !!

በረከት አብርሃም (ቲሞ)