የአራት ቀን ሬሳ አስነሳለው ብሎ መቃብር ያስቆፈረው ‘ፓስተር ነብይ’ በቁጠጥጥር ሥር ዋለ

አቶ በላይ ቢፍቱ የሊሙ ወረዳ ገሊላ ከተማ ነዋሪ ነበሩ። ባሳለፈነው ሰኞ ነበር በድንገተኛ አደጋ ህይወታቸው ያለፈው።

ቤተሰብ ሃዘን ተቀምጦ ሳለ ጌታያውቃል አየለ የሚባል ግለሰብ ለሟች ቤተሰቦች የመጸሃፍ ቅዱሱን አላዛር ታሪክ ከነገራቸው በኋላ ሟቹ በላይን እንደሚያስነሳ ይነግራቸዋል።

ከዚያም በላይን ከሞት እንደሚያስነሳ የቤተሰብ አባላቱን ካሳመነ በኋላ በላይ ወደተቀበረበት ወደ ሙሉ ወንጌል የመቃብር ስፍራ ይዟቸው ሄደ።

በቤተክረስቲያኗ ቅጥር ግቢ የነበሩት የሙሉ ወንጌል ቤተክርስቲያን ሰራተኛ የሆኑት አቶ ዲንሳ ደበላ ”ከመቃብሩ ስፍራ በላይ ከሞት ይነሳል የሚል ተደጋጋሚ ድምጽ ሰምቼ ምን እየተከናወነ እነደሆነ ለማጣራት ወደ ስፍራው ሄድኩ” ይላሉ።

እሳቸው እንደሚሉት ድርጊቱ የቤተክረስቲያኒቷን ስርዓት እንደሚጻረረ በምንገር ድርጊቱ እንዲቆም ሲያሳስቡ ከግለሰቦቹ ጥቃት ሊሰነዘርባቸው ሲል ሸሽተዋል።

ከዚያም ጌታያውቃል የተባለው ግለሰብ መቃብሩን አስቆፍሮ የሬሳ ሳጥኑን ከከፈተ በኋላ በተደጋጋሚ ”በላይ ተነስ” እያለ ሲጮህ ነበር።

በዚህ ብቻ የልተቆጠበው ይህ ግለሰብ የሬሳ ሳጥኑ ላይ ተዘርግቶ በመተኛት ‘ተነስ’ እያለ በተደጋጋሚ ድምጹን አሰማ።

እራሱን ነብይ እያለ የሚጠራው ይህ ግለሰብ ከላይ የተጠቀሰን ድርጊት ሲፈጽም የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማህበራዊ ሚዲያ በርካቶች ሲቀባበሉት ውለዋል።

በመጨረሻም መልስ ያጣው ግለሰብ ”ምንም ማድረግ አይቻልም” ብሎ ከመቃብሩ ጉድጓድ ውስጥ ወጥቶ ሊሄድ ሲል ጉዳይን በአትኩሮት ሲከታተሉ የነበሩ የአከባቢው ሰዎች እና የቤተሰብ አባላት በግለሰቡ ድርጊት በመበሳጨታቸው ሊደበድቡት ተነሱ ሲሉ አቶ ዲንሳ ነግረውናል።

ዘግይቶ በአካባቢው የተገኘው ፖሊስ አቶ ጌታያውቃልን ከመደብደብ አትረፎት በቁጥጥር ስር አውሎታል። ”አሁን በቁጥጥር ስር ይገኛል” ሲሉ የሊሙ ወረዳ የፖሊስ አባል የሆኑት ኮማንደር ታደሰ አማኑ ነግረውናል።

”ግለሰቡ የፈጸመውን ድርጊት እያጣራን ነው። ነብይ ነኝ የሚለው ይህ ሰው በአካባቢው ያሉ የየትኛውም የቤተክረስቲያን አባል እንዳልሆነ አረጋግጠናል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህ ግለሰብ የወረዳው ጤና ቢሮ ባልደረባ ስለመሆኑም ከምንጮቻችን መረዳት ችለናል።