የኤርትራውን ፕሬዝዳንት አቀባበል ለመዘገብ ሲጓዙ የነበሩት ጋዜጠኞች በመኢሶ ወረዳ ወጣቶች በደረሰባቸው ድብደባ ከተጎዱት አንዱ ሞተ።

ቅዳሜ ሐምሌ 7 ቀን 2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የተደረገውን የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን አቀባበል ሥነ ሥርዓት ለመዘገብ ከተለያየ የሃገሪቱ ክፍል ወደ አዲስ አበባ የተጓዙ ብዙ ጋዜጠኞች ወደ አዲስ አበባ መጥተዋል ። የድሬዳዋ ከተማ መገናኛ ብዙኃን የጋዜጠኞች ቡድንም ይህን የአቀባበል ስነ ስርአት ለመዘገብ ወደ አዲስ አበባ እየመጣ በነበረበት ወቅት ገንዘብ ተከፍሏችሁ ልትሰልሉ ነው በሚል ምክንያት ሚኤሶ ከተማ ላይ ሲደርሱ በተሰባሰቡ ወጣቶች ጥቃት ደርሶባቸው ነበር ።

ከነዚህ ጥቃት ከደረሰባቸው ሰወች መሃከል የጋዜጠኞቹን ቡድን ይዞ ወደ አዲስ አበባ የሚመጣውን መኪና ሾፈር የነበሩት አቶ ሱለይማን መሃመድ በወጣቶቹ በደረሰባቸው ድብደባ ጭንቅላታቸውና ጎናቸው ላይ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ደርሶባቸው በድሬዳዋ ድል ጮራ ሆስፒታልና በሐረር ከተማ ሕይወት ፋና ሆስፒታል የሕክምና ዕርዳታ ሲደረግላቸው ቢቆይም ሕይወታቸውን ማትረፍ ባለመቻሉ ዛሬ ህይወታቸው ሊያልፍ ችሏል ።


የ37 ዓመቱ አቶ ሱሌይማን የሦስት ልጆች አባት ሲሆኑ፣ ከነፍሰጡር ሚስታቸው አራተኛ ልጅ ይጠብቁ የነበሩትና ፈጽሞ ባላሰቡት ሁኔታ ህይወታቸው ያለፈውን አቶ ሱለይማንና የስራ ባልደረቦቻቸው ላይ ጥቃት ያደረሱት ወጣቶች ላይ እስካሁን ምንም አይነት ክስ አልተመሰረተባቸውም ። የዚህ ምስኪን ወገናችን ልጆች ግን ካሁን አሁን አባታቸው እንደሚመጣ እያሰቡ በር በሩን ያዩ ይሆናል ። ያሳዝናል ።


እንኳን ሰላማዊ ሰወችን ይቅርና ወንጀለኛን እንኳን በአግባቡ ይዞ ወደህግ ፊት ማቅረብ ሲገባ በጥርጣሬ የተያዙ ንፁሃን በጭካኔ እየተደበደቡና ለህልፈት እየተዳረጉ የምንዘልቀው እስከመቼ ነው ? በነዚህ ሰወች ላይ የደረሰው አሳዛኝ ነገርስ ነገ በማንኛውም ሰላማዊ ዜጋ ላይ እንደማይደርስ ዋስትናው ምን ይሆን ?


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE