በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈጠሩት ችግሮች በቂ የፖለቲካ ውክልና ካለመስጠት የመነጩ ናቸው

  • ትናንት ከጀርባ ሆነው ሀገር ሲመሩ የነበሩ ኃይሎች የታዩት ችግሮች ዛሬም ተረኞች ነን ብለው በሚያስቡ ኃይሎች እየተደገሙ ናቸው
  • በቅርቡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አካባቢ የተፈፀሙት ችግሮች የተስፋፊዎች ፍላጎት እንደሚስተዋልበት ….
  • በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈጠሩት ችግሮች በቂ የፖለቲካ ውክልና ካለመስጠት የመነጩ ናቸው
በተለያዩ አካባቢዎች በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈጠሩት ችግሮች በቂ የፖለቲካ ውክልና ካለመስጠት የመነጩ መሆናቸውን ምሁራንና ፖለቲከኞች ጠቆሙ፡፡
 (አብመድ) የታሪክ አጥኝዎች ትናንትን የሚመረምሩት ከትናንት ውስንነቶች ነፃ ለመውጣት ትምህርት ፍለጋ ነው፡፡ በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለው ግን ከታሪክ ትምህርት ከመውሰድ ይልቅ የታሪክ ቁርሾ ፈልጎ በችግሩ የመቀጠል ይመስላል፡፡ በኢትዮጵያ ዘውዳዊ ሥርዓት ተወግዶ ከውጭ በተቀዱ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለሞች ሀገሪቱ በተመራችባቸው ባለፉት ስድስት አስርት ዓመታት ብቻ ትናንት ከነበርንበት የሥርዓተ መንግሥታት ዝቅጠት መንጥቆ መውጣት የቻለ ኃይል አልተስተዋለም፡፡ ያለፈን ታሪክ መመርመር እና ማጥናት ለነገ ምን መምረጥ እንዳለብን ባይነግረን እንኳን በርከት ያሉ አማራጮች መኖራቸውን ሊያሳየን በተገባ ነበር፡፡ ነገር ግን አማራጮችን ከመጠቆም እና ከማሳየት ይልቅ በጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት አንዱ በገባበት መንገድ ሌላው ሊወጣ ሲጋፋ ነው የሚስተዋለው፤ ድሃው ሕዝብ የሕይወት መሥዋዕትነት ሲከፍል ማስተዋል ለዘመናት የተጣባን የሥነ መንግሥት ችግር ሆኖ ተስተውሏል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ትናንት ሕዝብ በብሔር እና በቋንቋ ልዩነት ተቧድኖ በፍርሃት እና በጥርጣሬ እንዲተያይ ተፈረደበት፤ ለውጥ መጣ በተባለ ማግስት በየአካባቢው የተቀበሩት ፈንጅዎች እየፈነዱ ጥርጣሬውን ወደ ህልውና ስጋት ሲያንሩት እየተመለከትን ነው፡፡ በተለይም የተወሰኑ ብሔሮችን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶች በአራቱም አቅጣጫ ሲወረወሩ መመልከት የትናንት የቤት ሥራዎቹ እርማት መሆናቸውን ያመላክታል፡፡ የእነዚህ ችግሮች ገፈት ቀማሽ ደግሞ አማራ ግንባር ቀደም ሆኗል፡፡ ለመሆኑ ችግሮቹን በዘላቂነት መፍታት እንዴት ይቻላል? ስንል ምሁራንን እና ፖለቲከኞችን አነጋግረናል፡፡
ሁሉም አስተያየት ሰጪዎች ለችግሮቹ ዋና ምክንያት ሀገሪቱ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የተመራችበት እና እየተመራችበት ያለው ሕገ መንግሥት ስለመሆኑ ይስማማሉ፤ ምንም እንኳን በአፈፃፀሙ ላይ ልዩነቶች ቢኖሯቸውም፡፡ “የክልሎች ሕገ መንግሥቶች ከፌዴራሉ ሕገ መንግሥት ጋር በምንም መልኩ ሊጣረሱ አይገባም ነበር” የሚሉት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር እምቢያለ በየነ ናቸው፤ የሚስተዋለው ግን በተቃራኒው ሲጣረሱ መመልከት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በየሚኖሩበት አካባቢ ተገቢው የፖለቲካ ውክልና ስሌላቸው ተቋማዊ ጥቃት ሲፈፀምባቸው እንደሚስተዋልም ጠቅሰዋል፡፡ በአንድ አካባቢ ማን ይሂድ ማን ይምጣ በግልፅ በማይታወቅበት ሁኔታ መጤ እና ነባር የሚል ደረጃ በሚሰጥ የክልሎች ሕገ መንግሥት ዘላቂ ሰላም ማሰብ ውጤት እንደማያመጣ ነው ረዳት ፕሮፌሰር እምቢያለ የጠቆሙት፡፡
ትናንት በመጡበት መንገድ ዛሬም መሄድ የሚፈልጉ የፖለቲካ ልሂቃን እንዳሉ ረዳት ፕሮፌሰር እምቢያለ ጠቅሰዋል፤ በተለይም በቅርቡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አካባቢ የተፈፀሙት ችግሮች የተስፋፊዎች ፍላጎት እንደሚስተዋልበትም ተናግረዋል፡፡ ትናንት ከጀርባ ሆነው ሀገር ሲመሩ የነበሩ ኃይሎች የታዩት ችግሮች ዛሬም ተረኞች ነን ብለው በሚያስቡ ኃይሎች እየተደገሙ መሆናቸውን በመጠቆም፡፡
ሕገ መንግሥታዊ ችግሮቹ ተፈትሸው ምላሽ እና መፍትሔ የሚያገኙበት ሂደት አዳጋች አለመሆኑን የጠቆሙት ደግሞ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ በየነ ጴጥሮስ (ፕሮፌሰር) ናቸው፡፡ ከሕገ መንግሥቱ ችግሮች ይልቅ ክልል እና ሀገር የሚመሩት ፖለቲከኞች ፍላጎት ጉዳዩን አስቸጋሪ እንዳደረገው ጠቁመዋል፡፡ እንደሀገር ሲሰባሰቡ የሚነጋገሩበትን እና የተሰማሙትን ሐሳብ በክልሎቻቸው ሲተገብሩት እንደማይስተዋልም ገልጸዋል፡፡
ፕሮፌሰር በየነ እንደሚሉት ችግሮቹ ፅንፈኛ ኃይሎች፣ ጠባብ ፖለቲከኞች፣ የግል ፍላጎት ያላቸው የማኅበረሰብ አንቂዎች እና የግንዛቤ ልዩነት ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች መኖር የፈጠረው ምስቅልቅል ነው፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም የሰከነ እና አሳታፊ የፖለቲካ አውድ መፍጠር እንደሚያስፈልግ መክረዋል፡፡
የአማራ ብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አብርሃም አለኽኝ በበኩላቸው ችግሩ “የሕግ ሽፋን ያገኘ መዋቅራዊ መድሎ” የፈጠረው ሥርዓታዊ ችግር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት የአማራን ሕዝብ ያገለለ ብቻ ሳይሆን ያለስሙ ስም የሰጠ እንደሆነ በመጠቆም፤ የክልል ሕገ መንግሥታት ከዚህ የከፉ ሆነው መቀረፃቸውም ሌላው ምክንያት እንደሆነ አውስተዋል፡፡
እንደ ኃላፊው ማብራሪያ የቀድሞው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ወደ ብልፅግና ፓርቲ ሲዋሐድ የአማራን ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች ይዞ ነው፤ በመሆኑም በዚች ሀገር ውስጥ ሀቀኛ ሕገ መንግሥት እና ሀቀኛ የፌዴራል ሥርዓት እውን መሆን እንዳለበት መታመን አለበት፡፡ ይህም በፕሮግራም እና በሕገ ደንብ ዕውቅና ማግኘቱን ጠቁመው ወደመሬት ለማውረድ የሕግ እንቅፋቶችን ለማጥራት እየተሠራ መሆኑን አቶ አብርሃም ጠቁመዋል፡፡ በየትኛውም አካባቢ የሚኖር ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ እና የፖለቲካ ውክልና እንዲኖረው ብልፅግና እንደሚሠራም አረጋግጠዋል፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በአማራ ሕዝቦች ላይ የሚፈፀሙት ጥቃቶች ሥርዓታዊ እና መዋቅራዊ እንደሆኑ አቶ አብርሃም ገልጸዋል፡፡ መዋቅራዊ ችግሮችን በመዋቅር፤ ሥርዓታዊ ችግሮችን በሥርዓት ለመፍታት እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ መንግሥት ሕግ ባለማስከበሩ መተቸቱ አግባብ ቢሆንም ፈፃሚውን መንግሥት ማድረግ ግን አጥፊዎችን ተከታትሎ ለመያዝ በሚደረገው ጥረት ሽፋን ሆኖ እያገለገለ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡