ህወሓት ምርጫ ማሸነፉን ተከትሎ በትግራይ ክልል የተለያዩ ከተሞች የድጋፍ ሰልፍ ተደረገ

በትግራይ ክልል የተለያዩ ከተሞች ለህወሓት የድጋፍ ሰልፍ ተደረገ – DW
በቅርቡ በትግራይ ክልል በተደረገው ምርጫ ህወሓት ማሸነፉን ተከትሎ፤ አባላቶቹና ደጋፊዎቹ በመቐለና በተለያዩ የትግራይ ክልል ከተሞች ዛሬ ጠዋት የድጋፍ ሰልፍ አደረጉ፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ የተሳተፈባቸው እነኝህ ሰልፎች ከትግራይ ክልል ርእሰ ከተማ መቐለ ውጭ በውቅሮ፣ ማይጨው፣ አላማጣ፣ ሽረ፣ ሑመራና ሌሎች በርካታ ከተሞች ተካሂዷል፡፡ ሰልፉ የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ እየተስፋፋ ባለበት በአሁኑ ወቅት መደረጉን በማንሳት የተለያዩ አካላት ተችተውታል፡፡
Image may contain: one or more people, crowd and outdoorዛሬ ጠዋት ከ12 ሰዓት ጀምሮ በመቐለ ሐውልት ሰማእታት ግቢ በተደረገ ስነ ስርዓት የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተው ለህዝባቸው መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ የህወሓት ሊቀ መንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በትግራይ ምርጫ ህወሓት ያገኘው ከፍተኛ ድምፅ “የትግራይ ህዝብ ህወሓት ላይ ያለው እምነት ያሳየበት” በማለት ገልፀውታል፡፡ ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ክልሉን ያስተዳደረው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ባለፈው ሳምንት በትግራይ በተናጠል በተደረገ ምርጫ ከ98 በመቶ በላይ የህዝብ ድምፅ አግኝቶ ማሸነፉ የትግራይ ምርጫ ኮምሽን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
ሰልፈኞቹ ፤የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድርና የህወሓቱ ሊቀ መንበር ዶክተር ደብረፅዮንን ጨምሮ ትግራይ ላይ ያነጣጠረ ዘመቻ በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስትና በሌሎች አካላት እየተካሄደ ነው ያሉ ሲሆን “መንገድ በመዝጋትና በሚድያ በመፎከር የሚንበረከክ ህዝብ የለም” ይልቁንስ ትግራይ ላይ የተከፈተው ዘመቻ ገትቶ፣ የሁሉም ብሄሮች የፖለቲካ እስረኞች ተፈተው፣ ፓለቲካዊ ንግግር ይጀመር ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ዛሬ ጠዋት በሁሉም የትግራይ ከተሞች በተደረጉ ሰልፎች በፌደራል መንግስት ታሰሩ የተባሉ “የፖለቲካ እስረኞች” ይፈቱ፣ በቅርቡ ፌደሬሽን ምክርቤት በትግራይ ምርጫ ዙርያ ያስተላለፈው ውሳኔ ተቀባይነት የለውም የሚሉና ሌሎች መፈክሮች ሲስተጋቡ ነበር፡፡
በሌላ በኩል የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ እየተስፋፋ ባለበት በዚህ ወቅት በትግራይ በተደጋጋሚ ህዝባዊ ሰልፈኞች መደረጋቸው ተገቢ አይደለም በማለት ብዙዎች ተችተዋል፡፡ የትግራይ ጤና ቢሮ ትላንት ባወጣው ዕለታዊ የኮረና ቫይረስ ሪፖርት በክልሉ በ24 ሰዓት ምርመራ ከተደረገላቸው 706 ተጠርጣሪዎች 162ቱ ኮረና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል፡፡ ይህ ማለት ከተመረመሩት ሰዎች 22 ነጥብ 9 በመቶዎቹ በቫይረሱ የተለከፉ መሆናቸው ያሳያል፡፡ እስካሁን በአጠቃላይ በትግራይ 5267 ሰዎች በምርመራ ኮረና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የክልሉ ጤና ቢሮ መረጃ ያመለክታል፡፡- DW