“መልካም ተመኝ፤ መልካም እንድታገኝ” እንዲሉ ሰው የአስተሳሰቡ ስሪት ነው – አዲስ ዓመትና ተስፋ፣ አዎንታዊ አስተሳሰብና ስኬት!

አዲስ ዓመት፣ አዲስ ተስፋ፣ አዎንታዊ አስተሳሰብ እና ስኬት!
አእምሯችን እጅግ ሀያል ነው፤ ራሳችንን በመልካም አስተሳሰብ ውስጥ መሆን ፈልገን ካዘዝነው እናደርገዋለን። አመለካከታችንን መቀያየር እና ከገባንበት አዘቅት መውጣት እና አለመውጣት የራሳችን ውሳኔ ነው፡፡ “መልካም ተመኝ፤ መልካም እንድታገኝ” እንዲሉ ሰው የአስተሳሰቡ ስሪት ነው፡፡
ዛሬ አዲስ ቀን ነው፤ አዲስ፤ ለዚያውም የአዲስ ዓመት አዲስ ቀን፤ በምንም አይነት ፈተና ውስጥ ብንሆን እንኳን እኛ ኢትዮጵያውያንማ ቀናችንን ብሩህ ማድረግ እናውቅበታለን፤ በዛሬው እለት ከመኝታችን “እንኳን አደረስከን፤ በቸር አውለን፤ በቸር አክርመን” ብለን በብሩህ ምስጋና እና ጸሎት ቀናችንን ጀምረናል፡፡ ሁሉም ነገር የክት ነው፤ ሁሉም ነገር አዲስ፤ የነበረ ቢሆን እንኳን ለዛሬ አዲስ ነው፤ ራሳችንን ማሳመን ብቻ!
ነገሮችን የምናይበት መንገድ በራሱ አዲስ ነው። ዛሬ “የእንኳን አደረሳችሁ” መልካም ምኞት ቀን ነው፤ ምርቃት ይዥጎደጎዳል፤ ስጦታ እንሰጣለን፤ እንቀባበላለን፤ ቤቱ ተሰነዳድቷል፤ አለባበሳችን ውብ ነው፤ ለዚያውም በነጭ የሀገር ባህል ልብስ ( “ነጭ” ቀለም በኛ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ያለውን ትርጓሜ ልብ በሉልኝማ)። ግብዣ ነው፤ ደስታ፤ ሀሴት ማድረግ፤ ስንቱ ይወራል ዓመት በዓል….
አዎንታዊ አስተሳሰብ እንደ አዎንታዊ ምስል፣ አዎንታዊ የራስ-ንግግር ወይም አጠቃላይ ብሩህ ተስፋ ብለን ልንገልጸው እንችላለን፡፡
የቀና አስተሳሰብ አካላዊ እና አእምሯዊ ጥቅሞች በበርካታ ሳይንሳዊ ጥናቶች ተገልጠው አንብበን ይሆናል፡፡ በዓልን አስታከን ደግሞ እውቀት እንጨምርበት። በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት እና መምህር ሠው በሠው ይታይ (ዶክተር) እኛ ዛሬ እያጣጣምን ያለነውን አዎንታዊ አስተሳሰብ የሚሰጠንን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ በሳይንሳዊ ማብራሪያ አረጋግጠውልናል፡፡ እናም ዶክተሩ ጠቀሜታዎቹን ሲዘረዝሩ ቀና አስተሳሰብ የበለጠ በራስ መተማመንን ያጎናጽፋል፤ የተረበሸ ስሜትን ከማሻሻል አልፎ ተርፎም እንደ የደም ግፊት፣ ድብርት እና ሌሎች ከጭንቀት ጋር የተዛመዱ ውስብስብ ችግሮች ሊታደገን ይችላል ነው ያሉት፡፡
የምሁሩ ማብራሪያ ቀጥሏል፤ የትኛውም ድርጊት ከሀሳብ ይመነጫል፤ መልካም፣ ቀና ወይም አዎንታዊ አስተሳሰብ ደግሞ መልካም ፍሬ ነው የሚያፈራው፡፡ እናም በአዲስ ዓመት የምንሰንቀው አዲስ አስተሳሰብ ለነገ ስኬታችን መሰረት ነው፡፡ አይደለም ዓመቱን የእለት ውሏችንን የምንጀምርበት ሁኔታ የቀሪ ቀኑን ምን አልባትም የቀጣይ እድሜአችንን ዕጣ ፈንታ እስከ መወሰን የሚያስችል አቅም እንዳለው በአብነት ገልጸዋል፤ “ዛሬ ቀኑ ደስ ይላል!” ብለን በብሩህ አእምሮ ቀኑን ስንቀበለው አእምሮአችን ለሰውነታችን ሥራችንን በስኬት ለመከወን ሚያስችለንን ንጥረ ነገር እንዲያመነጭ ፈጣን ትእዛዝ ያስተላልፋል፡፡ እናም ተነሳሽ እንሆናለን፤ ለነገሮች ቀና ምላሽ ይኖረናል፤ ትኩረታችን ሁሉ ወደ መልካም ገጽታ ይሳባል፤ ከዚያማ በቃ ..“ዛሬ ቀኑ የኔ ነው” ማለት እንጀምራለን፡፡
እንደ ዶክተር ሰው በሰው ማብራሪያ የብሩህ ተስፋ፣ የአዎንታዊ ወይም ቀና አስተሳሰብ ውጤቱ ለግለሰቡ ብቻ አይደለም ትርፉ፤ ለቤተሰብ፣ ለማኅበረሰብ እና ለሀገርም ጭምር እንጂ፡፡ የአንድ ቀና ሰው ስኬት ከራሱ አልፎ ሌሎችንም ያረሰርሳል፡፡ ለዚህም ነባራዊ አብነት አላቸው ዶክተሩ፤ እኛ ኢትዮጵያውያን በተለይ በበዓላት ወቅት ከሌላው ጊዜ በተለየ ሌሎችን እናስባለን፤ ደስታችንን ሌሎች እንዲጋሩን በእጅጉ እንሻለን፤ ካለን እናካፍላለን፤ እንጠያየቃለን… ወዘተ፡፡
በዓል ሲባል በራሱ ቤተሰብ፣ ዘመድ፣ ጎረቤት፣ እንግዳ የሚታደምበት፣ የሌላቸው የሚታሰቡበትም ነው። በዚህ መልክ አዲስ ዓመት፣ አዲስ ተስፋ፣ አዎንታዊ አስተሳሰብ እና ስኬታችን በእጅጉ የተቆራኙ መሆናቸውን ከዶክተሩ ግልጽ ማብራሪያ ተረድተናል ብዬ በቀናነት ላስብ።
ይህ አስተሳሰባችን ዘወትር እንዳይለየን ምን እናድርግ ታዲያ? የሚል ጥያቄ እናንሳ፡፡ እንደ ዶክተር ሠው በሠው ምክር መጀመሪያ ለራስ ያለ አመለካከትን ከመቀየር መጀመር ግድ ይላል፡፡ በአሮጌው ዓመት ስኬትም ውድቀትም አስተናግደናል። ይሄ ደግሞ ያለ ነው፤ አንድ አፍታ ቀልባችንን ሰብሰብ አድርገን ማሰብ፤ ስለ ስኬታችን ራሳችንን እናበረታታ፤ ለሌሎችም እናጋራ፤ ስለ ጉድለታችን አናለቃቅስ፤ ችግሩን ለይተን እንማርበት፡፡
ለቀጣይ በምናሳካው ልክ እናቅድ፡፡ “ሰው አዋዋሉን ይመስላል” እንዲሉ አዋዋላችን እናስተካክል፡፡ ቀና አስተሳሰብ ካላቸው ጋር መዋል ለስኬታማነት መልካም ነው፡፡ ሁሌም በበዓላት ወቅት እንደምናደርገው ለሌሎች መልካም ከማሰብ ብሎም ከማድረግ አንቦዝን፡፡ እነዚህን እና መሰል አስተሳሰቦችን ወደ ተግባር በመቀየር መለማመድ ውስጥ ዓመቱን የምናሳልፍ ከሆነ በሚቀጥለው እንቁጣጣሽ በስኬት እንገናኛለን፡፡
መልካሙን ሁሉ ተመኘንላችሁ!
መረጃ፡- ሳይኮሎጂ ቱደይ / Amhara Mass Media Agency