የመተጋገዝና የመረዳዳት ባህላችን በአዲሱ ዓመት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል¬- የኃይማኖት አባቶች

(ኤፍ.ቢ.ሲ) የመተጋገዝና የመረዳዳት ባህላችን በአዲሱ ዓመት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል አሉ የተለያዩ የእምነት ተቋማት የኃይማኖት አባቶች።
የ2013 ዓ.ም አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሰብሳቢ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ኡመር ኢንድሪስ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል እና የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ጸሃፊ ቄስ ደረጀ ጀምበሩ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
የኃይማኖት አባቶቹ በመልዕእክታቸው፥ ያለፈው ምጥፎ ነገር እንዳይደገም፤ መልካም ነገር ሀገርና ዜጋን ይወርስ ዘንድ እንደየ እምነታቸው የአዲስ ዓመት የመልካም ምኞት መግለጫቸውን አሰምተዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በመልእክታቸው፥ “እንኳን ከዘመነ ዮሃንስ ወደ ዘመነ ማቲዎስ በሰላም አሸጋገራችሁ” ብለዋል።
የጊዜ ሽክርክሪት በፈጣሪ ህግ እና ቁጥጥር ስር የሚሆን ፍጡራን ሊቆጣጠሩት ያልተፈቀደላቸው ግን በአግባቡ እንዲጠቀሙበት የተፈቀደላቸው ነው ብለዋል።
ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያዊነት አሴትን የሸረሸሩ ድርጊቶች ተፈጥረው ያለፉ መሆናቸውን ያነሱት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፥ ተሞክሮዎች ካለፉ ነገሮች እና ዓመታት የሚወሰዱ ቢሆኑም መልካም ነገሮችን መውሰድ ይገባል ብለዋል።
የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሰብሳቢ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ኡመር ኢንድሪስም እንኳን አደረሳችህ ያሉ ሲሆን፥ አኛ የሰው ልጆች የሰውነት ጠባይ ሰጥቶን የሚጠቅመንን የምንከተል ያድርገን ብለዋል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል፥ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በመልእክታቸውም፥ ፈጣሪ አዲስ ዓመት ሲሰጠን ለሰዎች ደስ ለሚያሰኝ ጥቅም እና እርሱ ለሚፈልገው ዓላማ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም ብለዋል።
ያለፈው ዓመት ግጭቶች፣ ኮቪድ 19፣ የጎርፍ አደጋ፣ አንበጣ እና ሌሎችም ከፊል ብርሃን ከፊል ጽልመት ሆኖ አመቱ እንዲያልፍ ሆኗል ነው ያሉት።
የሰው ልጅ ከራስ ከማሰብ በላይ ለሌሎች ወገኖቹም ማሰብ ፈጣሪ ከሚወደውም መካከል መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ፀሃፊ ቄስ ደረጀ ጀምበሩ፥ 2012 ዓ.ም በዛሬው እለት ሲቋጭ ትቷቸው ካለፋቸው መልካም ነገሮችም በተቃረነ ለ2013 የሚያልፍ መልካም ያልሆኑ ነገሮችም እንዳሉ ጠቅሰዋል።
ይህን ደግሞ በመተጋገዝ እና መደማመጥ ማለፍ እንደሚቻል ገልጸዋል።
ሁሉንም የምታቅፍ ሀገር ለመመስረትም አለመግባባቶችን በጦር መሳሪያ አፈሙዝ ከመፍታት በዘለለ የምክክር መድረኮችን ማስፋት እንደሚገባ በቤተክርስቲያናቸው ስም ጥሪ አቅርበዋል።
የሀይማኖት አባቶቹ በ2013 ዓ.ም አዲስ ዓመት የሰላም ዓመት ይሆን ዘንድ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም ጠይቀዋል።
የህዳሴ ግድብን ጨምሮ የተለያዩ የሀገር ፕሮጀክቶችም ላይ የተጀመሩ ተሳትፎዎችም በተጠናከረ መልኩ ይቀጥሉ ዘንድም ነው መልክት ያስተላለፉት።