በትግራይ ምርጫ ዛሬ ጠዋቱ ከ12 ሰዓት ጀምሮ ኅብረተሰቡ ድምፅ እየሰጠ ነው፡፡

ምርጫ በትግራይ ክልል
ረቡዕ ጳጉሜ 4 ቀን፣ 2012 ዓ:ም
DW : በትግራይ ምርጫ ዛሬ ጠዋቱ ከ12 ሰዓት ጀምሮ ኅብረተሰቡ ድምፅ እየሰጠ ነው፡፡
ጠንካራ ፉክክር ይኖርባቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ የትግራይ ከተሞች አንዷ በሆነችው ዓዲግራት ሕዝብነዋሪው ከንጋቱ 11 ሰዓት ጀምሮ ድምፁን ለመስጠት ተሰልፎ ሲጠባበቅ እንደነበር በሥፍራው የሚገኘው የዶይቸ ቬለ (DW) የአማርኛው ክፍል ዘጋቢያችን ተመልክቷል፡፡
ከተቀረው ኢትዮጵያ ተለይታ ክልላዊ ምርጫ በምታካሂደው ትግራይ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የመሪ ድርጅቱ ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ /ህወሓት መሪ እና የክልሉ ፕሬዚዳንት ደብረፂዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ለመወዳደር በተመዘገቡበት አደዋ የምርጫ ክልል በመገኘት በማለዳው ድምፃቸውን ሰጥተዋል፡፡
ዶክተር ደብረፂዮን ድምፃቸውን ከሰጡ በኋላ በስፍራው ለተገኙ ሚዲያዎች “የትግራይ ክልላዊ ምርጫ የማንንም ወገን ዕውቅና እና ይሁንታ የማይፈልግ የትግራይ ህዝብ ብቻ የሚወስንበት ዴሞክራሲያዊ ሂደት ነው” ብለዋል፡፡
2.7 ሚሊየን መራጮች በተመዘገቡበት የትግራይ ምርጫ ገዢ ድርጅቱ ህወሓትን ጨምሮ 5 የፖለቲካ ፓርቲዎች እየተሳተፉ ይገኛል፡፡
የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ እስካሁን ሠላማዊ መሆኑን የክልሉ መገናኛ ብዙሃን የዘገቡ ሲሆን መራጩ ህዝብም ከንጋቱ ጀምሮ በየምርጫ ጣቢያዎች ተገኝቶ ለቀጣይ 5 ዓመታት ትግራይን ያስተዳድርልኛል ብሎ ላመነበት ፓርቲ ድምፁን እየሰጠ ይገኛል፡፡