ወልቃይት የአይቀሬው ጦርነት ግንባር!? – (ሙሉዓለም ገ/መድህን)

ወልቃይት የአይቀሬው ጦርነት ግንባር!? – (ሙሉዓለም ገ/መድህን)
****
የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ አነሳስ፣ የህዝባዊ ተጋድሎ መጠን መጨመር እና በዛኛው ጽንፍ የታዩ አጸፋዊ ምላሾች በተጣራሽ መስመር መሄዳቸው፤ በማንነት ጥያቄው አፈታት ላይ የሰላም አማራጮች የተዘጉ፣ አብሮነትን ከሚያድስ ተስፋ ይልቅ ጨለምተኝነትን አብዝቶ የሚያሸክም ‹ብሔራዊ አደጋ› አፍጥጦ መታየት ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡
በዚህ መጣጥፍ መሬት ላይ ያሉ እውነታዎችን በመጠኑም ቢሆን በመዳሰስ ወልቃይት የአይቀሬው ጦርነት ግንባር ስለመሆኗ ማጠየቅ የጸሐፊው ቀዳሚ ዓላማ ነው፡፡ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ስለጉዳዮ ክረትና አሳሳቢነት (ጎላ ያለ) ክብደት እንዲሰጡት እና ከፖለቲካ እና ከወታደራዊ እንቅስቃሴዎች አኳያ ተጨማሪ የሁኔታ ትንተናዎችን እንዲሰሩ ጥቁምታ መስጠትን ያለመ ጽሁፍ ነው፡፡
ወቅታዊ ሁኔታ!
‹‹አማራን ከወልቃይት ምድር ማጽዳት›› የሚል ድርጅታዊ መመሪያ ያነገበው የትግራይ ፋሽዝም አራማጁ ትህነግ፤ ዛሬም እንደትላንቱ በዘር ማጥራት (Ethnic cleansing) የወንጀል ተግባሩ እንደተጠመደ ነው፡፡ በምርጫ ስም በወልቃይት እና በአካባቢው ላይ እየፈጸማቸው ያሉ ግድያ እና የጅምላ እስር የቀደመው የዘር ማጥራት ተግባር ቅጥያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ የትግራይ ልዩ ኃይል አማራ (‹አማ›) አ.አ (አዲስ አበባ) ወዘተ የሚል የሰሌዳ ቁጥር መላያ ያላቸው ተሸከርካሪዎች ትግራይ ተብሎ ወደ ተከለለው አካባቢ እንዳይገቡ ከልክሏል፡፡ ይህ የምርጫ ደኀንነትን ለማስከበር የሚል ምክንያት የተሰጠው ዕቀባ ትሕነግ ሀገረ_ትግራይን የማወጅ ልምምዱ አካል ተደርጎ ይወሰዳል። በሌላ በኩል እስርና ወከባ እንደቀጠለ ነው። ባለፉት ሦስት ሳምንታት ብቻ በደጋማው የወልቃይት ክፍል፣ ከአርባ በላይ የሚሆኑ ወጣቶች (ብዙዎቹ ታዳጊዎች ናቸው) በጅምላ ታፍሰው ወደሁመራ አስር ቤት ተግዘዋል፡፡
በተለየ ሁኔታ የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዩች ኮሚሽን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሁንታ ከተቋቋመ ወዲህ ባሉ ጊዜያት ወልቃይት ውስጥ በሚኖሩ አማሮች ላይ የሚፈጸመው ሥርዓታዊ በደል ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በተለይም እንደ ዳንሻ፣ ከተማ ንጉሥ (ማክሰኞ ገበያ)፣ ማይካድራ፣ ቃፍቲያ፣ አዲጋባ፣ ብላንባ፣ ወፍ አርግፍ፣… በተባሉ የከተማ እና የወረዳ ገጠር ቀበሌዎች የሚኖሩ አማሮች መደበኛ ህይወታቸውን መምራት በማይችሉበት የደህንነት ስጋት ውስጥ ገብተዋል፡፡ የኢኮኖሚም ሆነ የማህበራዊ ግንኙነታቸው ተገድቦ ያሉት የወልቃይት አማሮች፣ ከምርጫው ጋር በተያያዘ አንመርጥም ማለታቸውን ተከትሎ የእስር ዘመቻ ተከፍቶባቸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በአማርኛ ቋንቋ የንግድ ድርጅቶቻቸውን የሰየሙና የጻፉ ነጋዴዎች ወደትግረኛ ቋንቋ እንዲቀይሩ ጫና ሲደረግባቸው የቆየ ሲሆን፤ አሁን ላይ ሁኔታዎች የፋሽስት ድርጊት ተላብሰው ወደንግድ ፈቃድ ነጠቃ (ስረዛ) እንዲሁም ንብረታቸው የአማራ (‹አማ›) የሆኑ ተሽከርካሪዎችን ያለአንዳች የሕግ አግባብ ወደ ማሰር ደርሷል፡፡ እነዚህ ተግባራት የፋሽዝም ወካይ ምልክቶች ናቸው፡፡ በእስካሁኑ ሥርዓታዊ በደል የወልቃይት አማሮች ልጆቻቸው በቋንቋቸው እንዳይማሩ በመደበኛ ትምህርት ቆይታቸው በግድ ትግረኛ እንዲማሩ መደረጉ፣ በየትኛውም የክልሉ መስሪያ ቤት በትግረኛ የሥራ ቋንቋ በግድ እንዲናገሩ መደረጋቸው፣ የአማራን ባህል ከሚያንጸባርቁ ማህበራዊ መለዮዎች ይልቅ የትግራይ ባህል በላያቸው ላይ ሲጫንባቸው መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡
በዚህ ሁሉ ፋሽዝም ሥርዓታዊ በደል ውስጥ የኖሩትን የወልቃይት አማሮች፣ ከሞት እና ከስደት የተረፉትን በኢኮኖሚ ለማዳከም ከመሬት ነጠቃ ጀምሮ በርካታ ወንጀሎች ተፈጽሞባቸዋል፡፡
ሕገወጡ ምርጫ እየገፋ ከመጣ ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ ነዋሪነታቸው በዳንሻ ከተማ የሆኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች፣ ወደ ሁመራ ከተማ ለቀው በመሄድ ላይ ናቸው፡፡ ይህን ተከትሎ ከዳንሻ ከተማ በሰባት ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኘው ‹‹ዲቪዥን›› ከተሰኘው አካባቢ የቀድሞ የትህነግ ታጋዮች ከሰፈሩበት ቦታ በመንቀሳቀስ ወደዳንሻ ከተማ በመግባት የሮንድ ስራ እንሲሩ በመደረጉ በከተማው ውስጥ በሚኖሩ አማሮች ላይ ስጋት ፈጥሯል፡፡
‹‹ትህነግ ምርጫውን ተገን አድርጎ በከተማው ላይ በሚኖሩ አማሮች ላይ ጭፍጨፋ ሊፈጽም ነው›› የሚል ስጋት ውስጥ ገብተዋል። ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ የወልቃይት አማሮች ወደአማራ ‹‹ክልል›› ጠገዴ ወረዳ- ሶረቃ ከተማ ተሰደዋል፡፡
ወደወልቃይት የሚሄዱ ተሸከርካሪዎች ማለፍ የማይችሉ በመሆኑ እንቅስቃሴዎች ተገትተዋል፡፡ የሰሞኑን የትህነግ ፋሽስታዊ ድርጊት ከቀደመው የተለየ የሚያደርገው ምርጫውን ተገን በማድረግ ከሕዝቡ አልፎ እየኮበለሉ ባስቸገሩት የልዩ ኃይሉ እና ሚሊሻዎች እንዲሁም ቤተሰቦቻቸው ላይ ጭምር ጥብቅ ክትትል እያደረገ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ የከፋ ክትትልና ውጥረት ያሰጋቸው ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ የትግራይ ተወላጆች ከዳንሻ ከተማ ለቀው መውጣታቸውና በምትኩ የቀድሞ ታጋዮች ከልዩ ኃይሉ እና ሚሊሻ ጎን መሰለፋቸው፣ ትህነግ ምርጫውን ተገን አድርጎ (ትንኮሳ ደረሰብኝ በሚል) በአካባቢው ላይ ወታደራዊ ጥቃት ለመፈጸም ያለመ አስመስሎታል፡፡
ወታደራዊ እንቅስቃሴ!
ትህነግ በወልቃይት ደጋማው እና ከፊል ቆላማው ክፍል (ከአማራ ‹‹ክልል›› ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች) በሚሊሻ እና በልዩ ኃይል አባላት (በተጨማሪነትም በቀድሞ ታጋዮች ተደራቢነት) የታጀበ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ሲያደርግ እንደቆየ የሚታወስ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ወደ ሁመራ በሚወስደው መንገድ፤ ማይደሌ፣ ዳንሻ፣ በአከር፣ ራዊያን የተባሉ ቦታዎች ላይ የነበሩ የፍተሻ ጣቢያዎች በአቅራቢያቸው ወደካምፕነት በማሳደግ፣ በዚሁ መስመር ላይ ተጨማሪ የፍተሸ ጣቢያዎች ተቋቁመዋል፡፡
በሁሉም የፍተሻ ጣቢያዎች በክልል ደረጃ ይኖራሉ ተብሎ የማይገመቱ የቡድን የጦር መሳሪዎች እና የወታደራዊ መገናኛዎች (ራዲዩ) አሉ፡፡ በሌላ በኩል ከአማራ ‹‹ክልል›› ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች ያሰፈረው የልዩ ኃይል እና የሚሊሻ ቁጥር መገመት የሚያዳግት ቢሆንም፣ መጠኑን በካምፖቹ እና በቆፈራቸው ምሽጎች ብዛት መረዳት ይቻላል፡፡
ለአብነት የሚጠቀሱት የትህነግ ምሽጎች የሚከተሉት ናቸው፡-
=> ካዛ ወንዝ አካባቢ
=> ደብረሃርያ ማይደሌ (ሹመሪ ጀርባ)
=> ጎቤ
=> ግጨው
=> ዳራ
=> ከተማ ንጉሥ (ማክሰኞ ገበያ) አቅራቢያ
=> እንዳማርያም፣…
በተለይም በተራ ቁጥር አንድ እና ሁለት ላይ በተጠቀሱት ቦታዎች ላይ የተሰሩ ምሽጎች፣ በኢትዩ-ኤርትራ የድንበር ግጭት ጊዜ ኢትዩጵያ ሰርታው የነበረ አይነት ዲዛይን አላቸው፡፡ በነገራችን ላይ ከ2009- 2012 ጥቅምት ወር ድረስ በምዕራብ ጎንደር ‹‹የቅማንት ኮሚቴ›› እየተባለ ለሚጠራው አካል እና በስሩ ለተደራጁት ተወርዋሪ አሸባሪ የቡድኑ አባላት የጦርነት ሎጀስቲክስ ሲያቀርብ የነበረው ሱር ኮንስትራክሽን፣ በከተማ ንጉሥ አቅራቢያ ‹‹ሸሐግኔ›› በተባለ ቦታ ባለው ካምፕ አማካኝነት በምሽግ ቁፋሮው ጊዜ አይነተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡
ከዚህ በላይ በተመለከቱት አካባቢዎች ያለው የሚሊሻ ስምሪት አንደአካባቢው ስፋት የጋንታው ብዛት የሚለያይ ቢሆንም በአንድ ጋንታ (እስከ አስራ ስድት የሰው ኃይል) ይመደባል፡፡ የልዮ ኃይሉ እንቅስቃሴ ደግሞ በሻለቃ ደረጃ እንደሆነ፤ በተጨማሪነትም በዋናነት ‹‹ዲቪዥን›› አካባቢ ሰፍረው መደበኛ ህይወት የሚኖሩ የቀድሞ ታጋዮች እንደአስፈላጊነቱ ተወርውረው የሚደርሱበት (የሚደረቡበት) የኃይል አደረጃጀት እንዳለ የአጠቃላይ ወታደራዊ እንቅስቃሴቸው ግምገማ (የአካባቢው የመረጃ ምንጫችን እይታ) ያመለከታል፡፡
በአንድ አካባቢ (የገጠር ቀበሌም ሆነ ከተማ) በጋንታ ደረጃ የተደራጀው ሚሊሻ ቁጠሩ ሊጨምርም ሊቀንስም ይችላል፡፡ ለአብነት እንደ ማይደሌ፣ ካዛ፣ ግጨው፣… ባሉ አካባቢዎች በእያንዳንዱ አካባቢ ከአርባ እስከ ሃምሳ አምስት የሚደረስ የጋንታ ብዛት ይኖራል፡፡ በአንድ ጋንታ ስር ከሚጠቃለሉ (እስከ 16) ሚሊሻዎች ውስጥ አንድ ስናይፐር፣ አንድ የእጅ መትረየስ እና የነፍስ ወከፍ አውቶማቲክ ክላሽኮቭ ከነሙሉ ትጥቁ (አራት ካርታ ጥይት፣ አራት የእጅ ቦምብ፣ የእጅ ባትሪ፣ገመድ፣…) በተሟላ ሁኔታ ይዘው ይታያሉ፡፡ በልዩ ኃይሉ በኩል ያለው ትጥቅ በቡድን ደረጃ የጸረ-ታንክ ፣ ጸረ-ተሸከርካሪ መሳሪያዎችን ጨምሮ ሮኬት፣ ሞርታር፣ ብሬል፣ አር. ፒ. ጂ. ፣ … በየደረጃው በተዋቀሩ የኃይል አደረጃጀቶች ታጥቀዋል፡፡
የሚሊሻ እና የልዩ ኃይል አደረጃጀት በየራሱ መዋቅር ሽሬ ላይ ላሉ የምዕራብ ትግራይ የኮር አመራሮች የጸጥታ ጉዳዮችን የተመለከቱ ነገሮችን ሪፖርት ያደርጋል፡፡ ከቀበሌ ገበሬ ማኀበር እስከ ወረዳ እና ከተማ አስተዳደር ድረስ ያለው የሲቪል አስተዳደሩ ህዝብን መሰብሰብ ጨምሮ የትኛውም አይነት እንቅስቃሴ ያለጸጥታ መዋቅሩ ይሁንታ አይከናወንም፡፡ ይፋዊ ባልሆነ መልኩ ትግራይ ክልል በኮማንድ ፖስት ስር እንደሚመራ ሲቪል ቢሮክራሲው በጽጥታ ኃይሉ መዋቅር ስር መያዙን እንደማሳያ ማቅረብ ይቻላል፡፡
ከሰሞኑ “መረፃ ትግራይ” በሚል ልፋፌ በገበያና በሃይማኖታዊ ቦታዎች ሳይቀር ‹‹የትግራይ ሕዝብ ራሱን ከታሪካዊ ጠላቶቹ እንዲከላከል››፣ ‹‹የትግራይን ዳር ድንበር እንዲያስከብር›› ወታደራዊ መመሪያ ተሰጥቷል፡፡
በአጠቃላይ ትሕነግ በተለየ ሁኔታ ከአማራ ‹‹ክልል›› ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች ያለው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ከፌዴራል አልያም ወንድም ከሆነ የጎረቤት ክልል ጋር ሊካሄድ ይችላል የሚባል ታሳቢ ግጭት ሳይሆን ከአንዲት ሉዓላዊት አገር ጋር ለሚካሄድ መደበኛ ጦርነት የሚደረግ ቅድመ ዘግጅት አስመስሎታል፡፡
ከዚህ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ጎን ለጎን ለጸጥታ መዋቅሩ መጋቢ የሆነ የመረጃ ግብዓት የሚሰጡ፤ ለመረጃ እና የደህንነት ስለላ ስራ የተመረጡ ወደአማራ ክልል በነጻነት ይገባሉ፤ ይወጣሉ፡፡ ለዚህ ጽሁፍ ግብዓት መረጃዎችን በመሰብሰብ ሂደት የታየው ተጨባጭ እውነታ በአካባቢው ያሉ የአማራ ክልል የዞንም ሆነ የወረዳ አመራሮች ለዚህ መሰል የጸጥታና ደህንነት የመረጃ ክትትል በአደጋው ልክ ትኩረት ሲሰጡ አይስተዋልም፡፡
የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችን ማደስና ማጠናከር እንደተጠበቀ ሆኖ በየትኛውም ማህበራዊ መለዮ ለእኩይ ዓላማ ሰርገው የሚገቡ አካላትን መንጥሮ ማውጣት የአመራሩ የቅድሚያ ትኩረት ጉዳይ ሊሆን ይገባል፡፡ ከጠገዴ ቅራቅር እስከ ‹‹ጸገዴ ከተማ ንጉሥ›› ድረስ ሰባት ኪሎ ሜትር ርቀት፤ ከጠገዴ- ሶረቃ እስከ ዳንሻ ከሃያ ስድስት ኪሎ ሜትር የማይበልጥ ርቀት አለው፡፡ በእነዚህ መስመሮች በመኪናም ይሁን በእግር በመጓዝ የሚፈልጉትን የመረጃ ስለላ ለማድረግ ይንቀሳቀሱ የነበሩ የትህነግ ‹ነጭ ለባሾች› አንድም ጊዜ ሳይያዙ ሰንብተዋል፡፡ በአንጻሩ ከአማራ ‹‹ክልል›› ወደ ትግራይ የሚሄዱ የአማራ ተወላጆች ቀርቶ እዛው ተወልደው ያደጉ የወልቃይት አማሮች መደበኛ ህይዋታቸውን መምራት በማይችሉበት ሽብር መር የምርጫ ደህንነት ስጋት ውስጥ ይገኛሉ፡፡
በዳንሻ እና አካባቢው እየታየ ያለው የትግራ ልዩ ኃይል ፋሽስታዊ ድርጊት በርካቶችን ከዳንሻ ከተማ ወደ ሶረቃ እንዲሰደዱ አድርጓቸዋል፡፡ በተለይም ሽመሪ (በዳንሻ እና በሶረቃ [በትግራይና አማራ] መካካል የምትገኝ) ንዑስ ወረዳ አካባቢ ያለው ውጥረት እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡
በአጠቃላይ ትህነግ በወልቃይት ላይ ትግራይን ለጦርነት እንዳዘጋጃት የተቆፈሩ ምሽጎች እና በአካባቢው የሚስተዋለው ወታደራዊ እንቅስቃሴና ትንኮሳዎቹ ምስክር ናቸው፡፡ በዛሬው ምሽትና በነገው ዕለት እስከ በዐል ማግስት ድረስ የተቀነባበረ ትንኮሳ በመፈጸም ጦርነት ተከፈተብኝ የሚል ፕሮፖጋንዳና የስም ማጥፋት ዘመቻ በመክፈት በሰበቡ የወልቃይት አማሮችን በጅምላ እንዳይፈጅ ተጨባጭ ስጋቶች አሉ፡፡