አዲስ አበባ ከመሬት ጋር ተያይዞ የሚሰጥ አገልግሎት ላልተወሰነ ጊዜ ቆመ

ካፒታል – አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከህገወጥ መሬት ወረራ ጋር በተያያዘ እየወጡ ያሉ መረጃዎች አስኪጣሩ አና አሰራሮች እስኪስተካከሉ ከመሬት ጋር ተያይዞ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ላልተወሰነ ጊዜ አቆመ
በከተማ አስተዳደሩ የምክትል ከነቲባ ፅህፈት ቤት እና የካቢኔ ጉዳዮች ምክትል ሃላፊ የሆኑት አቶ ደረጄ ካሳ ለካፒታል ጋዜጣ አንደገለፁት የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ፣ የስም ማዞር፣ የኮንስትራክሽን ስራዎች አና የመሳሰሉትን የመሬት አስተዳደር የሚሰጣቸው አገልግሎቶች መረጃዎች ተጣርተው አሰራሮች አስኪስተካከሉ ድረስ ላልተወሰነ ጊዜ እንደቆሙ ገልፀዋል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ አደረኩት ባለው ጥናት በከተማዋ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ህገወጥ የመሬት ወረራ መኖሩን እንደገለፀ የሚታወስ ነው፡፡ እንደ ጥናቱ ገለፃ በህገወጥ መሬት ወረራ እና ያላግባብ የኮንዶሚኒየም ቤቶች እደላ ላይ በስልጣን ላይ ካሉ አመራሮች ጀምሮ ተሳታፊ እንደሆኑ ሲገልፅ በተጨማሪም በብሄር ተለይቶ ድርጊቶች እንደሚፈፀሙ ያትታል፡፡
የቀድሞ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ሲሰጡ በህገ ወጥ መንገድ የኮንዶሚኒየማ እደላ ተብሎ የተጠቀሰው 20000 ለሚሆኑ ለቤት ግንባታ ከእርሻ ቦታቸው ተፈናቃይ ለሆኑ አርሶ አደሮች የተሰጡ እንደሆኑ እና አነሱም በአጠቃላይ ተነሺ ከሆኑት 67000 አርሶ አደሮች በባሰ ሁኔታ ይገኛሉ ተብለው የተመረጡ እንደሆኑና ይሄም ከአንድ አመት ተኩል በፊት የተከናወነ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
በቅርቡ የቀድሞው ምክትል ከነቲባ ኢንጂነር ታከለ በከተማዋ ውስጥ እየተለመደ የመጣውን ህገወጥ የመሬት ወረራን ለመቆጣጠር የመሬት ምዝገባና ኦዲት አንዲሁም ለአርሶ አደሮች የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ እስከ ጥቅምት 2013 ድረስ አንዲሰጥ ለሁሉም ክፍለ ከተማ አስተዳደሮች ትእዛዝ ሰጥተው ነበር፡፡