“ለክፋትና ለመግደል አንደመር” – ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ = “የከሰርነውን የምናካክስበት ጊዜ ነው”- ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ

በሚሊኒየም አዳራሽ ለኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ መቀበያ በተሰናዳው የሙዚቃ ዝግጅት ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ “እውነትና ፍቅር ከሁሉም ይልቃል” ብለዋል። “ከኢሳያስ ያላተረፍነው ነገር የለም፤ አሰባስቦናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ፕሬዝዳንቱን ደጋግመው “ኢሱ” በሚል ቁልምጫ ሲጠሯቸው ተሰምተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “ኢሱ የሰላምና የነፃንት ዋጋን ከጤና ጋራ ያመሳስለዋል። ከሰላምና ነፃነት ውጭ ብልፅግና የማይተገበር ሕልም ነው።” ብለዋል። አያይዘውም፤ “ሀገር እንደ ሰው ናት።እኛ እንደሆነው ትሆናለች፣ ስንከባበር ትከብራለች፣ ስናድግ ታድጋለች” የሚል ሐሳብ ያለው ንግግርም አድርገዋል።

ከመቶ ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ ክፉት የሚያስብ ሰው አይኖርም ማለት እንደማይቻል ገልፀው ፤ “የመደመር ሚስጥር ለፍቅርና ለደስታ ይሁን፤ ለክፋትና ለመግደል አንደመር” ብለዋል። “ክፉን ካልተጋራነው መክኖ ይቀራል” – ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

አያይዘው “የእኛ መደመር ለሌሎች ተስፋ እንጂ ጭንቀት ሊሆን አይገባም” ሲሉ የመደመር ሐሳባቸውን ሚስጥር አብራርተዋል።

በመድረክ ላይ በአማረኛ ንግግር ሲያደርጉ ከዚህ ቀደም የማይደመጡት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ መድረኩ ላይ ወጥተው ንግግራቸውን ሲጀመሩ ዝግጅቱን የሚታደመው በሺሕዎች የሚቆጠር ሕዝብ በከፍተኛ የድጋፍ ጩኸት ተቀብሏቸዋል።

ሁለቱ ሀገረሮች ያለፈውን ባሕላቸውንና ታሪካቸውን ታሳቢ አድርገው፣ ጥላቻና ቂምን አሸንፈው፣ በጋራ ለልማት እንዲሠሩ የጠየቁት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ለሰላም ያደረጉትን ጥረትና የሚከተሉትን አቅጣጫ አድንቀዋል።