ኢሳያስ ለኢትዮጵያ የመቶ አመት የቤት ስራ የሰጠ እንጅ ቤቴ ነች ብሎ አያስብም!

ኢሳያስ ለኢትዮጵያ የመቶ አመት የቤት ስራ የሰጠ እንጅ ቤቴ ነች ብሎ አያስብም!

ኢትዮጵያና ኤርትራን አንድ ለማድረግ ብዙ ተደክሟል። ብዙ ደም ፈሷል። የተዋለዱና የተዛመዱ ተነጣጥለው ቆይተዋል። በሌላ ጦርነት ብዙ ኪሳራ ደርሷል።

ኤርትራና ኢትዮጵያ መካከል ሰላም በመውረዱ ብዙ ችግሮች ይቀረፋሉ! ሰላም ከምንም በላይ ነው። ሌላው ይቀጥላል!

ይህ ሁሉ ሆኖ ግን!

“የመቶ አመት የቤት ስራ እንሰጣቸዋለን” ያለውን ኢሳያስ እያሞገሱ መቀበል ማስመሰል ነው። ኢሳያስን “ኢትዮጵያ ቤትህ ነች” ማለት ቀልድ ነው። እሱ ቤቴ ነች አይልም። የ100 አመት የቤት ስራ የሰጣት ሀገር እንጅ ሀገሬ ነች ብሎ አያምንም። “በዓለም ካሉት ሀገራት ሁሉ ማን ይበተን” ቢባል 1ኛ፣ 2ኛ፣ 3ኛ፣…ብሎ ኢትዮጵያን ይጠራ ነበር።

ሰው ከተቀበለም የኤርትራን ሕዝብ ቀጣይ አብሮነት ያጎለ ቢሆን ይሻል ነበር። ኢሳያስን ማሞገስ ግን ተገቢ አይደለም። ከአቶ መለስ በኋላ ኢትዮጵያ መልካም ነገር አይታለች። ኤርትራም ቢያንስ ከኢሳያስ በኋላ መሰል ጭላንጭል ልታይ ትችል ይሆናል።

ዛሬም ከኢትዮጵያ ዶክተር አብይ፣ ከኤርትራ ደግሞ አዲስ ሰው ሆኖ ቢሆን ሕዝብ እንደ አዲስ በተቀበለ ነበር። የዛሬው ግን የቆየውን ወይን በአዲስ አቁማዳ እንደሚሉት መሰለኝ! የኢሳያስን የጥላቻ ታሪክ የሚያውቅ ጨፍሮ የሚቀበለው አይመስለኝም። ኢሳያስ የበላበትን ወጭት የሰበረ ሰው ነው!

በግሌ መምጣቱን አልቃወምም። ማሰብ የምፈልገውም እንደ ኤርትራ ፕሬዝደንት እንጅ እንደ ኢሳያስ አፈወርቂ አይደለም። በግል እንደሚወደስና እንደሚወደድ ሰው አይደለም። ለኤርትራ ሕዝብ ሲባል እንጅ ይህን የበላበትን ወጭት ሰባሪና በጥላቻ ከመለስ ዜናዊ የባሰ ሰው አጨብጭቤ ብቀበል የሀገር ክህደት የፈፀምኩ ያህል ይሰማኛል!

ጌታቸው ሽፈራው