ዘንካታው ጠሚ – ሸላይ ወግ – (ዳንኤል በቀለ )

ዘንካታው ጠሚ – ሸላይ ወግ – (ዳንኤል በቀለ )

መቼስ ዓብይ አህመድን በቁመት የሚስተካከል ኢትዮጵያዊ መሪ የለም። ቢኖርም ምናልባት የቁዋራው አንበሳ፥ አጼ ቴዎድሮስ ብቻ ናቸው።

ቆፍጣናው የዘመናይቱ ኢትዮጵያ መስራች ቁመታቸው በዛ ዘመን እንኩዋ ወደ ስድስት ጫማ (1.80m) ይደርስ እንደነበር ያነበብኩ ይመስለኛል። በዛ ዘመን የነበሩ ኢትዮጵየኖች ደሞ ካሁኖቹ ኢትዮጵያኖች አጠር ያሉ ናቸው።

ባለፉት 100 አመታት ውስጥ ስልጣን ላይ የነበሩት ግርማዊነታቸው፥ ኮሎኔል መንግስቱም ሆኑ ጠሚ መለስ ዘናዊ፥ ከዓብይ አህመድ ትከሻ ቢደርሱ እንጅ እንብዛም ከፍ አይሉም።

እዚህ ላይ ዋናው የሚያሳዝነው ነገር በ100 አመት ውስጥ ያየነው መሪ ሶስት ብቻ መሆናቸው ነው።

አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝን በመዝለሌ እንደማትቀየሙ ተስፋ አለኝ። ፖለቲካ በዚህ ፖስት ስለማናወራ ወደ ቁመቱ እንመለስ።

በዓብይ አህመድ የኤርትራ ጉብኝት ከታዘብኩዋቸው አንዱ ነገር የኢሳያስ አፈወርቂ ቁመት ነው።

ፕሬዚዳንቱ ረጅም እንደሆኑ ባውቅም ይሄን ያህል ረጅም እንደነበሩ ግን አላስተዋልኩም ነበር። ረጅም ከሚባሉት ጠሚም ዘለግ ብለው ሳያቸው ገርሞኛል።

ምን ያህል እንደሚመትሩ ለማወቅ ግን ጉግል አድርጌያቸው አልተሳካልኝም።

ዶክተር ጎልጉልም ብዙ መረጃ ያስፈልጋቸዋል።

ያሜሪካ አርባ አምስቱንም ፕሬዚዳንቶች ቁመት ጎልጉሎ ለማወቅ ግን ምንም አይነት ችግር የለም። ልዩነቱ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ውጤት ብቻ አይመስለኝም።

አንድ አሜሪካዊ ሰለ አሜሪካ ፕሬዚዳንት መጀመርያ የሚያውቀው የቆዳ ቀለሙን እና ቁመቱን ይመስለኛል።

ባሁን ዘመን ሜትር ከሰማንያ በታች ሆኖ ያሜሪካ ፕሬዚዳንትነት የማይታሰብ ነው።

ማጁም ሆኑ፥ መንጌና፥ መለስ በዚህ እጥረታቸው፥ የፈለጉትን ያህል የሰከኑ አገር ወዳድ አሜሪካዊ ፖለቲከኛ ቢሆኑ ዋይት ሐውስ የመግባት እድላቸው የመነመነ ነው።

ምናልባት አማካሪነት….

አሜሪካ ውስጥ ቁመት እጅግ አስፈላጊ ከመሆኑ የተነሳ፥ አንድ ኢንች ቁመት የአንድ አሜሪካዊ የአመት ገቢ ላይ on average የ 6500 የአሜሪካ ዶላር ልዩነት እንደሚያመጣ አንብቤአለሁ።

አጭሬዎች ኩራቱን ትተው ለግብር ቅነሳ ቢታገሉ እኔም እቀላቀል ነበር።

የፕሬዚዳንት ኢሳያስ ቤት

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ከልብ ሲስቁ ያየሁዋቸው በጠሚው ጉብኝት ወቅት ነው።

ጠሚው ምን ቀለድ ነግረዋቸው እንደሆነ እንደዚህ ሲንከተከቱ የታዩት ራሱን የቻለ የቀልድ ምንጭ ሁንዋል።

ኢሳያስ አፈወርቂ በወጣትነት ዘመናቸው በረሃ የገቡ ከዛም ለሚቀጥሉት 50 አመትም በኤርትራ ፖለቲካ የተጠመዱ በመሆኑ ስለ ግል ሕይወታ፲ው ከማውራት ይልቅ ስላገራቸው እና ስለ ድርጅታቸው ማውራት ይበልጥ ይቀናቸዋል።

ለ ዓብይ አህመድ ግን ገመናቸውን ከፍተው የግል መኖርያ ቤታቸው መጋበዛቸው ትልቅ ነገር ነው።

መኖርያ ቤታቸው ደሞ ቤተ መንግስት ሳይሆን እንደ መካከለኛ የመንግስት ሰራተኛ ቤት መሆኑም ገርሞኛል።

የባለቤታቸው simplicity ወይዘሮ ውባንቺን አስታውሶኛል።

በነገራችን ወይዘሮ ውባንቺ መቼ ነው አገራቸው ለጉብኝት እንኩዋን የሚመጡት?)

የፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጎረቤቶች እየተጋፉ ጠሚውን ሲስሙዋቸው ጠሚው ሊደብቁት ያልቻሉት እንባ በፊታቸው ኩልል ብሎ ሲወርድ አይቶ ልቡ የማይነካ የለም።

የቁልቁዋሉ ግብዣ

ኢሳያስ አፈወርቂና ዐብይ አህመድ የሰላም ስምምነት ለመድረሰ የ አሜሪካ፥ የአውሮጳ፥ የሩዋንዳ፥ የአፈሪቃ አንድነት ድርጅት ወይም የሌላ የቅብርጥሴ ድርጅት ገላጋይነትና ሽምግልና አላሰፈለጋቸውም።

አገር ያፈራውን ቁልቁዋል እየበሉ በቀጥታ እርስ በረስ ተነጋግረው ስንት መቶ ሺህ ዶላር የሚከፈላቸው ዲፕሎማቶች በአመታት ድርድር የማያመጡትን ሰላም ለሕዝባቸው አበርክተዋል።

አብሮ የበላ፥ አብሮ ማእድ የቆረሰ ጦርነት ውስጥ፥ ተመልሶ የመግባት እድሉ የጠበበ ነው።

እንግዲህ የተጀመረውን ሰላም ማጽናት የሁላችንም ጥረትን ይጠይቃል።

አንጎራጎሪዋ

እዚች ክሊፕ ላይ ስለ ሰላም የምታንጎራጉረውን ዘፋኝ ባውቃት ደስ ይለኛል።

ውስጤ ገብታ አልወጣ ካለች አንድ ቀን አለፈው።

በዚሁ ላብቃ።


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE