ኢሳያስ ኢሳያስ ነው! — (ጌታቸው ሺፈራው)

ኢሳያስ ኢሳያስ ነው! (ጌታቸው ሺፈራው)

ጀብሃ የሚባል ግብፅ ኢትዮጵያ ለማፈራረስ የጠፈጠፈችው ቡድን ነበር። አሜሪካ ሙስሊሞች የበዙበትን ይህ ቡድን እንደስጋት አየችው። አጤ ኃይለስላሴ ከግዛት አንድነት አንፃር አደጋ ነው አሉ።

ኢሳያስ አፈወርቂ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መንግስት በድሎት ያስተምራቸው ከነበሩ የዛ ዘመን ተማሪዎች አንዱ ነው። ይህ ሰው ጀብሃን ለመበተን በሰላይነት እንደተመረጠ ይነገራል። አጤ ኃይለስላሴ የሀገር አንድነት ለማስጠበቅ አምነውት ነበሩ አሉ። እናም ሰላይ አደረጉት! አምነውት ነው።

ኢሳያስ ጀብሃ ላይ የታቀደውን ሰራበት። ጀብሃ ውስጥ ሻዕቢያ ፈጠረ። ቡድኑ ህልውና ያለው ሲሆን የተባለውን የሀገር አንድነት ሕልውና ማስጠበቅ ሳይሆን የሀገር አንድነት ለማፍረስ የመጀመርያው ሰባኪ ሆኖ አረፈው። በኢትዮጵያ በጀት የኢትዮጵያ ጠላት ሆነ።

ኢሳያስ አዲስ ሀገር ለመመስረት የኢትዮጵያ ጠላት ናቸው ያላቸው ጋር ተወዳጀ። የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት ይረብሻሉ ካላቸው ጋር ተወዳጀ። የመጀመርያው ትህነግ/ህወሓት ነበር። በዚሁ ሂደት አንድ ትልቅ ጠላት አድርጎ የፈረጀው ሕዝብ ነበር። አማራ!

አማራን እንደጭራቅ ማሳየት የመጀመርያው የእነ ኢሳያስ የፖለቲካ ቅስቀሳ ሆነ። ይህ ሕዝብ ላይ በዓለም ላይ ያለ ውንጀላን ሁሉ አቀረበ፣ የቻለውን ሁሉ ስድብና እርግማን አወረደ። ትህነግ/ህወሓት የተከተለው የእሱን ፈለግ ነበር!

ኢትዮጵያ በሻዕቢያና በትህነግ እጅ እንደወደቀች “የመቶ አመት የቤት ስራ እንሰጣቸዋለን” በሚለው ኢሳያስና የትህነግ ሰዎች እርስ በእርስ ማጋጨት ስልት እንደዋነኛ ስልት ተያዘ። አማራና ኦሮሞን ማባላት የመጀመርያው ስልት ሆነ። አማራን ማጥላላት፣ ማሰርና መግረፍ የኢሳያስና የመለስ ዋና ስራ ሆነ። የቻሉትን አደረጉ። እነ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ በታሰሩበት ወቅት አብዛኛዎቹ ገራፊዎች የሻዕቢያ ደሕንነቶች ነበሩ። የፕሮፌሰር አስራትን የፍርድ ቤት ሂደት የሚመራው ኤርትራዊ የሻዕቢያ ተላላኪ ነበር! ትህነግ ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረ በኋላ ኢትዮጵያውያን አሳር ሲያበላ የነበረው ሻዕቢያ ጭምር ነበር። ሻዕቢያ በኢትዮጵያውያን በተለይም በአማራ ላይ የቻለውን ሁሉ አድርጓል!

ኢሳያስ ኢሳያስ ነው! ለኢትዮጵያ አንድነት ይቆም ዘንድ ኢትዮጵያን ለመበተን የሰራ ከሃዲ ነው! ኢሳያስ አማርኛ አቀላጥፎ ይናገራል። አማርኛ መናገር ግን ሞት ይመስለዋል።

በአንድ ወቅት ኢሳት ኢሳያስን አናግሮት ነበር። የኢሳት ጋዜጠኞች በአማርኛ እየጠየቁት እሱ በእንግሊዘኛ ይመልሳል። እንግሊዘኛ ከአማርኛ ቀርቦት መሆኑ ነው። ከእንግሊዘኛ ይልቅ አማርኛ የቅኝ ገዥ ቋንቋ መሆኑ ነው።

ለኤርትራ የሰላም ጥሪ ያቀረበው ዶክተር አብይ ነው። ኢሳያስ አፈወርቂ በባድመ ጉዳይ አንገራግሮ ነበር። የዶክተር አብይ የሰላም ፍላጎት እንጅ ግትር ቢሆን ይህ ግንኙነት በቅርቡ የሚታሰብ አይመስለኝም።

ዶክተር አብይ አህመድ ያን የኢሳያስ ግትርነት ሰብሮ የሰላም መንገዱን ጀምሯል። በዚህ ሂደት የዶክተር አብይና የኢሳያስን ሁኔታ እኩል መገምገም አይቻልም።

ዶክተር አብይ ጎበዝ ዲፕሎማት ሆኖ ታይቷል። በትግርኛ ተናግሯል። ዶክተር አብይ ትግርኛ ከሚችለው በላይ ኢሳያስ አማርኛ ይችላል። ዶክተር አብይ የኢትዮጵያ የስራ ቋንቋ ከሆነው አማርኛ ትግርኛን አስቀድሞ ሲናገር ኢሳያስ አማርኛ ለመናገር አልዳዳውም።

ዶክተር አብይ በሁለቱ ሀገራት መካከል በተደረገው ጦርነት የተሳተፈው እንደ አንድ ተራ ወታደር ነው፣ ኢሳያስ ዋነኛ ተሳታፊ ነው። ተጠያቂ። ወታደር ሆኖ የተሰለፈው ዶክተር አብይ በጦርነቱ ልጆቻቸውን ያጡትንና የቆሰሉትን አፅናንቷል። ኢሳያስ በዛን ወቅት ጦርነቱን የማስቀረት አቅም ነበረው። ለተደረገው ጦርነት በኤርትራ በኩል አንደኛው ተጠያቂ ነው። ልጆቻቸው ላለቁባቸውና ለቆሰሉት ግን ሀዘኑን እንደ ዶክተር አብይ መግለፅ አልፈለገም።

የሁለቱ ሀገራት ሰላም መሆን በጣም በርካታ ጉዳዮችን ይቀርፋል። ጥቅም እንጅ ጉዳት የለውም። ይህን በማድረግ ትልቁን ሚና የተጫወተው ዶክተር አብይ ነው ማለት ያስደፍራል። እንደ ዶክተር አብይ ካደረገውና ከኢሳያስ ግብረ መልስ ማየት የሚቻለው ኢሳያስ ወደዚህ መድረክ የመጣው በዶክተር አብይ ትልቅ ጥረት ነው። ዶክተር አብይ ካሳየው የተለየ ዲሎማሲያዊ ጥረት ካልሆነ በስተቀር ኢሳያስስ የድሮው ኢሳያስ ነው። አማርኛ መናገርን የሚፀየፈው በጥላቻ የናወዘው ኢሳያስ፣ አማርኛ ሙዚቃ እንዳይሰማ የከለከለው ሰው በዶክተር አብይ ለየት ያለ የአቀራረብ ስልት እንኳ ሸብረክ አላለም። የጦርነቱ ዋና ቀያሽ ለይምሰል እንኳ የኢትዮጵያን እናቶች አላፅናናም። ዶክተር አብይ ሆኖ እንጅ ኢሳያስማ ኢሳያስ ነው!

ዶክተር አብይ ባሳየው ቀናኢ ዲፕሎማሲ ወደ ሰላም ያመጣውን ኢሳያስን ነገ ከድሮው ጥላቻው ሸብረክ ያደርገው ይሆን? አይመስለኝም። ምን አልባት ኢሳያስ አርጅቷል። ከኢሳያስ ይልቅ ሕዝብ ያሳየው ፈንጠዝያ ደስ የሚያሳይ ነው። ተስፋ ሰጭም ነው! ኢሳያስ ከእነ ጥላቻውም ይሁን በታዕምር በፍቅር ተሸንፎ አላፊ ነው። ሕዝብ ወደፊት ይኖራል። ከኢሳያስ ይልቅ የኤርትራ ሕዝብ ደስታ ለቀጣዩ የሁለቱ ሀገር ሰላም ተስፋ ሰጭ ይሆናል! ኢሳያስስ ኢሳያስ ነው! የዶክተር አብይ ቀናኢነት አሁንም አማርኛ ያላስናገረው፣ የኢትዮጵያ እናቶችን ለማፅናናት ያልደፈረው የድሮው ግትር ነው! ደግነቱ ኢሳያስ አላፊ ነው! ቶሎ ካላለፈ ግን ነገ የተሻለ ጥቅም ሲያገኝ ሊሸጠን አይጨንቀውም!