ፖሊስ የአስራት ሚዲያ ጋዜጠኞችን በኦሮሚያ ክልል አመጽ ቀስቅሰዋል በሚል ከሰሳቸው

ሐምሌ 29/2012 ዓ/ም ለእስር የተዳረጉት በላይ ማናዬ፣ ሙሉጌታ አንበርብር፣ ምስጋናው ከፈለኝና ዮናታን ሙሉጌታ በዛሬው ዕለት አራዳ ምድብ ችሎት ቀርበው የ13 ቀን ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል።
ፖሊስ አሥራት ሚዲያ ከሕዳር 12/2012 እስከ ሰኔ 2012 ዓ/ም የአማራ ሕዝብ በተለየ ሁኔታ እንደተበደለ፣ መንግስትም ለአማራ ሕዝብ መከላከል እንዳልቻለ ፕሮግራሞችን በማቅረቡና በመዘገቡ ደምቢዶሎን ጨምሮ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚገኙ ቦታዎች ብጥብጥ እንዲፈጠር በማድረግ የሰው ሕይወትና ንብረት ጠፍቷል ብሏል። ጋዜጠኞቹ በዚህ ወቅት የአሥራት ሰራተኞች ስለነበሩ እጃቸው አለበት ብሎ እንደጠረጠራቸው ተገልፆአል።
አሥራት ቴሌቪዥን በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲለሚታይና ደንቢዶሎን ጨምሮ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ መርማሪ ስለምልክ በሚል ፖሊስ 14 ቀን እንዲፈቀድለት ሲጠይቅ ፍርድ ቤቱ 13 ቀን የፈቀሰለት ሲሆን ለነሃሴ 13/2012 ዓ/ም ተቀጥሮባቸዋል።
በሌላ በኩል የአሥራት ጋዜጠኞች ወደ እስር ቤት ሲገቡ የኮሮና ምርመራ እንዳልተደረገላቸው፣ እስር ቤት አብረዋቸው የታሰሩት ሰዎችም ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው ሳይታወቅ አብረው እንደታሰሩ በመግለፅ ቅሬታቸውን ገልፀዋል። በተመሳሳይ ያሉበት እስር ቤት ከሽንት ቤት አጠገብና ንፁህ ባለመሆኑ በተለይ የሳይነስ ሕመም ያለበት ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ እስር ቤቱ ለጤናው ምቹ አለመሆኑን አቤቱታውን አቅርቧል።
የአሥራት ጋዜጠኞች ምግብ፣ ልብስና መድሃኒት እንዳይገባላቸው መከልከላቸውን መግለፃችን ይታወሳል።

አሥራት ሚዲያ