ሁለት ጊዜ ነው የታሰርኩት : ያሳሰረኝ ለህወሓት የሰጠኝ ኦነግ ሸኔ ነው – አቶ ታዬ ደንደአ

የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊው አቶ ታዬ ደንደአ በህወሓት እና በኦነግ ሸኔ መካከል ከትናንት እስከ ዛሬ ያለውን ዝምድና እና የስራ ግንኙነት ከራሳቸው የግል እስርና እንግልት በመነሳት ጭምር በሰፊው አብራርተው ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ተናግረዋል።
ትልቁ ጉዳይ የጀርባ ታሪካቸውን ማየት ነው። ለምሳሌ፣ እኔ እንደ ግለሰብ ኦነግ ውስጥ ነው የነበርኩት። ኦነግ ውስጥ ሆኜ ኦነግ ብዙ ድጋፍ ነበረው። እኔ ወደ አባልነት ከመቀላቀሌ በፊትም እደግፈው ነበር። ነገር ግን ይሄ ሁሉ ድጋፍ እያለው የዚህ ድርጅት ትግል ለምንድን ነው ወደፊት ገፍቶ የማይመጣው? የሚል ጥያቄ ነበረኝ። በርካታ ወጣቶች፤ በርካታ ምሁራንና መምህራንም ይሄንኑ ይጠይቃሉ። ምክንያቱም በየጊዜው ዘመን መለወጫ ላይ “ገዳን ገዳ ቢሊሱማቲ” (ቀጣዩ ዘመን የነጻነት ዘመን ነው) ይላሉ። ይሄ ደግሞ ዘመን በተለወጠ ቁጥር በቃል ብቻ የሚባል ፍሬ አልባ ጉዞ ነበረ። እናም ምክንያቱ ምንድን ነው? ብለን ብናስብም በወቅቱ ሊገባን አልቻለም። ከዛ በኋላ ኦነግን ተቀላቀንንና ውስጡ ገባን። ስንገባ ነገሩን ተረዳን።
ነገሩ ምንድን ነው ካልክ፤ ኦነግ ሸኔ እና ህወሓት አብረው ሲሰሩ ነበር። ኦነግ ሸኔ ህወሓት የሚጠቀምበት የራሱ መጠቀሚያ ነው። በእርግጥ ኦሮሞ ጠባብ፣ አማራ ደግሞ ትምክህተኛ ይባላል፤ ትምክህተኛና ጠባብ በፍረጃ ደረጃ ነበር የነበሩት። ኦነግነት ደግሞ የህወሓት ትልቁ መጠቀሚያ ነበረ። እንዴት ነው የሚጠቀምበት ካልከኝ ደግሞ፤ አንደኛ፣ የኦሮሞ ህዝብ ነጸነት ይፈልጋል፤ (ኦሮሞ ብቻም ሳይሆን ኢትዮጵያውያንም ነጻነት ፈልገው ዋጋ ሲከፍሉ ነበር፤)፤ ነገር ግን ይሄን ነጻነት ማን ያመጣልኛል ብሎ ሲያስብ አንድ በነጻነት ስም የተደራጀ ድርጅት አለ። ይሄ ድርጅት ግን ጭንቅላቱ በህወሓት ተይዟል።
ህዝቡ ደግሞ ይሄ ድርጅት በወያኔ እጅ የተያዘ መሆኑን አያውቅም፤ እናም አንድ ቀን ይመጣልኛል ብሎ ይጠብቃል። ሆኖም ይህ ድርጅት ጭንቅላቱ ተይዞ በያዘው አካል ፍላጎት የሚንቀሳቀስ እንደመሆኑ ይህ ድርጅት ሊመጣለት አይችልም ነበር። ስለዚህ ህወሓት ኦነግ ሸኔን ሆን ብሎ በዛ ደረጃ የኦሮሞ ህዝብ፣ የኦሮሞ ወጣት፣ የኦሮሞ ምሑር የሌለ ነገር እንዲጠብቅ፤ በሴራ ያስቀመጠው ነው። ይሄንንም ለሃያ ዓመታት ያህል የኖሩበት ሲሆን፤ በተለይም አቶ ገላሳ ዲልቦ ከስልጣን ወርደው የአሁኑ የሸኔ ሊቀመንበር ስልጣን ከያዘ በኋላ በቀጥታ ትብብሩ ውስጥ ነው የነበሩት።
ሁለተኛው መታየት ያለበት ጉዳይ፣ ኦህዴድ ውስጥ ሆነህ ኦሮሞ ላይ ጉዳት ደርሷል ብለህ ካነሳህ ኦነግ ትባላለህ። የኦሮሞ ባለሀብት ሆነህ ሊዘርፉህ ከፈለጉ ኦነግ ይሉሃል። ይሄን የሚያደርጉት ደግሞ ኦነግ የሌለ ከሆነ የሚፈርጁበት ስለሌለ ስለሚቸገሩ ነው። ስለዚህ ኦነግ እንደሌለና በእነርሱ ስር እንዳለ ቢያውቁትም፤ በኦነግ ስም ተማሪን ለመደብደብም፣ መምህራንን ለማሰርም፣ ነገ ይገዳደረኛል ብሎ የሚያስቡንት ለመግደልም ይጠቀሙበታል። እናም ኦነግ ሸኔና ህወሓት በዛ ደረጃ አብረው ነበሩ።
በሶስተኛ መታየት ያለበት፣ ኦነግ ሸኔ የኦሮሞ ታጋዮች አንድ ወጥመድ መሆኑ ነው። ለምሳሌ፣ እኔ ሁለት ጊዜ ነው የታሰርኩት። አስር ዓመት ነው እስር ቤት የቆየሁት። ሁለት ጊዜ ስታሰር ሁለቱንም ጊዜ ያሳሰረኝ የኦነግ ሸኔ አባል ነው። ያሳሰረኝ ኦህዴድ አይደለም፤ ህወሓትም ራሱ ፈልጎ አላገኘኝም። ለህወሓት የሰጠኝ ኦነግ ሸኔ ነው። ይሄን የሚያደርጉት ደግሞ በአንድ በኩል አብረው ስለሚሰሩ ሲሆን፤ በገንዘብም ይሸጡሃል። እንደውም አንዳንዴ አደራጅተውና የኦነግን ባንዲራ አሲዘው አሳልፈው ይሰጣሉ።
ለምሳሌ፣ ግርማ ጥሩነህ የሚባል የሸኔ ተወካይ የነበረ 2008 አካባቢ ቦሌ ላይ 20 ሰዎችን ማህበር ብሎ በአንድ ጊዜ አደራጅቶና የኦነግ ሸኔ ባንዲራ አስቀምጦ ደህንነትን ጠርቶ አስይዟቸዋል። እናም በዛ ደረጃ ነው በሰው የሚጫወቱትና የሚነግዱት። እናም በገንዘብ ይሸጡሃል፤ ከተያዝክና ከታሰርክ በኋላ ደግሞ ጀግና ታሰረ ብለው ውጪ ያሉት አባሎቻቸው በስደት እያሉ የህዝቡን ነጻነት ከሚፈልጉ የዋሆች ላይ ገንዘብ ይሰበስባሉ።
ከዛ ባሻገር ደግሞ ሶሎሎ የሚባል አካባቢ እነሱ የመሸጉበት አለ። እዚህ መከራ ሲያይ፤ ሲታሰርና ሲገረፍ የተቸገረ ሰው በቃ ሄጄ ታጥቄ ልታገል ብሎ እዛ ይሄዳል። እዛም ይታይና ሃሳብ ያለው ከሆነና ጀግንነት ያለው ከሆነ እዛው ይገደላል፤ ወይ ይቃጠላል። ይሄን የሚያደርጉት ደግሞ ይህ ሰው ነገ ሪቮሉሽን (አብዮት) ሊያመጣ ይችላል ተብሎ ስለሚታሰብ ነው።
እናም ህወሓትና ኦነግ ሸኔ አብረው የሚሰሩ፤ መረጃም የሚለዋወጡ ናቸው። ለአብነት፣ ህብረተሰቡ ሲያምጽ የወያኔ መልስ ጥይት ነው፤ ግድያ ነው። በተለያየ ጊዜ በተማሪ ደረጃ፣ በወጣት ደረጃ፣ በ2006 ከዛም በፊት በ1998፣ በ1996 እና በተለያየ ጊዜ የተለያዩ አመጾች በተለይ በኦሮሚያ ክልል ተደርገዋል። በጣም የሚያሳዝንህ ግን በዚህ ውስጥም የሴራ ፖለቲካ እንዲታይ ሆኗል። ሴራውም ህወሓት በአጠቃላይም የኢህአዴግ መንግስት ንጹሃን ኦሮሞዎችን ገድሏል፤ ሰብዓዊ መብትም ተጥሷል በሚል በዓለምአቀፍ ደረጃ (በአምኒስት ኢንተርናሽናል፣ ሂዩማን ራይትስ ዎችና ሌሎችም) ክስ ይቀርብበታል።
ይህ ክስ ሲቀርብ ህወሓት የሚያደርገው ነገር በእኔ ትዕዛዝ ነው ህዝቡ ያመጸው በልና መግለጫ አውጣ ብሎ የሚያነበውን መግለጫ ጽፎ ለኦነግ ሸኔ ይልክለታል። ኦነግ ሸኔም አስመራ ላይ ሆኖ በህወሓት ተጽፎ የቀረበለትን መግለጫ ያነብባል። የእኛ ትግል ነው ብሎ ያነበበውን የእርሱን መግለጫም እነ ቪኦኤና እንደ ዶቼቬሌ ጭምር ያስተላልፉታል። ህወሓት/ኢህአዴግ ደግሞ ይሄንን ተጠቅሞ እንቅስቃሴው የህዝብ አልነበረም፤ የአሸባሪው ኦነግ ነው ብሎ ራሱን ለመከላከል መልስ ይሰጣል። እናም በዚህ ደረጃ በረቀቀ መልኩ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ አብረው ነበሩ።
ይሄንን በደንብ ማየት የሚያስችልህ በኢሬቻ ጊዜ በርካታ ዜጎች ህይወታቸው አልፏል። በተቃውሞ ጊዜም በተለይ “ግራንድ ራሊ” ተብሎ በተደረገው ትልቅ ሰልፍ የብዙ ወጣቶች ህይወት አልፏል። የኦሮሞ ህዝብ በአብዲ ኢሌ እና በህወሓት ሴራ በሚሊዮን የሚቆጠር ከሶማሌ ክልል ተፈናቅሏል፤ ሞቷልም። እንግዲህ ተኩስ ቢያስፈልግ ያን ጊዜ ጀግና ወጥቶ መተኮስ ነበረበት። ወጣቱ በሰላማዊ መንገድ ወጥቶ ባዶ እጁን መንገድ ላይ ሲራገፍ ኦነግ ሸኔ የሚባለው አንድ ጥይት አይደለም ወደጠላት ወደ ሰማይ አልተኮሰም። ይሁን እንጂ እነ ጌታቸው አሰፋ ከስልጣን እንደወረዱ ጫካ ታያቸው። ይህ ምን ማለት ነው? ትግሉ የነጻነት ነው ወይስ ፀረ ነጻነት ነው? ያኔ ህዝቡ ለነጻነት ሲታገል የት ነበሩ? አዲስ አበባ ላይ፣ አማራ ክልል፣ ኦሮሚያ ክልል፣ ደቡብ ክልል፣ ሶማሌ ክልል ህዝቡ መከራ ሲያይ፣ ሲገረፍ፣ በግፍ ሲረግፍና ሲገደል አንድ ጥይት ለመተኮስ እንኳን አልሞከሩም።
በወቅቱ ከእነርሱ ጋር የነበረ ሰው አለ፤ ኮሎኔል አበበ ገረሱ። እንደምንም ለዚህ ህዝብ እንድረስለት ብለው ሲጠይቃቸው፣ አይ ኢትዮጵያን ሶሪያ አናደርጋትም፣ ተኩስ እዛ ቢካሄድ ሶሪያ ነው የምትሆነው፤ ህብረተሰቡ በራሱ ጊዜና በራሱ መንገድ በሰላማዊ መንገድ ቢታገል ነው የሚሻለው፤ ነው ያሉት። ታዲያ ትጥቅ፣ ተኩስና ግድያ ከዛ በኋላ ለምን አስፈለገ? የሚገድሉት ደግሞ እግር የቆረጠውን፤ ያኮላሸውን፤ ጥፍር የነቀለውንና ሌላም ግፍ ያደረሰውን አይደለም። ትናንት ይሄን ያደረገው ዛሬ የእነርሱ ወዳጅ ነው። አብረው ነው የሚሰሩት። እንደውም ሎጀስቲክስም ስትራቴጂም ከዛ ነው የሚቀበሉት። ስለዚህ ግንኙነታቸው ከድሮም ጀምሮ ያለ ነው።
ከዚህ ሁሉ በላይ ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ማወቅ የሚገባው እና በተለይም የኦሮሞ ህዝብ ሊነቃበት የሚገባው የኦነግ ሸኔ ፕሮፖጋንዳ የኦሮሞ ህዝብ እንደ ጭራቅና ገዳይ እንዲታይ፤ እንደ ሰይጣን እንዲፈራ እና እንዲጠረጠር የሚያደርግ ፕሮፖጋንዳ ሲያደርግ ነበር። የኦሮሞ ህዝብ የተለየ ጥያቄ እንዳለው እና ኦሮሞ ከኢትዮጵያ የተለየ እንደሆነ እንጂ፤ ከሌሎች ጋር ተስማምቶ ያለ እና ተመሳሳይ ጥያቄና ችግር ነው ያለን፣ መፍትሄውም በጋራ ብንታገልና በጋራ ብንሰራ ነው የምናገኘው፤ የሚል አስተሳሰብ እንዲመጣ አይፈልግም። በዚህም ለምሳሌ፣ በኦሮሞና ሶማሌ ነዋሪዎች መካከል ትንሽ እንኳን የግጦሽ ሳር ግጭት ብትፈጠር የፍረጃ ወሬን በማጋጋል ኦሮሞና ሶማሌን የሚያቃቅር፤ በተመሳሳይ በሲዳማና ኦሮሞ አዋሳኝ ላይ ትንሽ ግጭት ቢፈጠር እሱኑ አጋግሎ በኦሮሞና ሲዳማ መካከል ትልቅ ጥርጣሬ እንዲፈጠር ማድረግ ስራቸው ነው።
ሌላው ቀርቶ ራሳቸው በፈጠሩት ግርግር በቤንሻንጉል ጉሙዝና ኦሮሚያ አካባቢዎች ጉዳት በደረሰ ጊዜ የሚጠቀሙት ቃላት ለሌሎች ማህበረሰቦች እጅግ ፀያፍ፤ የሚያበሳጭና ግጭትና ቁርሾን የሚያባብስም ነበር። እናም በዚህ ደረጃ ይሄን አቃፊ እና የኢትዮጵያ ትልቅ መሰረት የሆነውን ማህበረሰብ፤ ኢትዮጵያውያንን ወዶና አክብሮ አብሮ ኢትዮጵያን የመሰረተ እና ብሎም ለማሳደግና ለማሻገር የሚፈልገውን ማህበረሰብ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር እንዳይስማማ፤ እሱ ተስማምቶ እየኖረም እነርሱ በሚሰሩት የፕሮፖጋንዳ ሴራ ሌሎች እንዲጠራጠሩት እየሆነ ነው። ይሄን ማድረግ ደግሞ የህወሓት ባህሪ ሲሆን፤ ይህ በራሱ የህወሓትና ኦነግ ሸኔ ግንኙነት የት ድረስ እንደሆነ የሚያሳይ ነው።