የኢትዮጵያ ፖለቲካ የለውጥ ጉዞ: ከትናንት ዛሬ ቢሻልም ነገ ላይ ጥርጣሬ አለን ( ሙልጌታ ቢ. ተፈሪ )

የሽግግር ወቅት ሁሌም በተስፋ የተሞላ ነው፡፡ በርግጠኝነትም ትላንትን ለኖረ ዛሬ ከትናነት የተሻለ ነው፡፡ ነገር ግን ምንም ከትናንት የተሻሉ ተስፋ ብንሰንቅም፤ ከሁሉም ጊዜ ይልቅ ስለ ነገ እርግጠኛ አይደለንም፡፡ በሽግግር ወቅት ላይ ስለሆንን፡፡ ሽግግር ሲባል ከመንግስት ለውጥ ጋር ብቻ የማያያዝ ታሪክ ስላለን “ማን ሄዶ ማን መጣ?” የሚል አይጠፋም፡፡

በዚህ ወቅት እየተሻገርን ያለው እንደከዚህ ቀደሙ ከአንድ ገዥ ወደ ሌላ ገዥ አይደለም፡፡ ይልቅስ በተለያዩ ንጉሳዊ፣ ወታደራዊ እና ኮሚኒስታዊ ቡድኖች ከመተዳደር እራሳችንን በራሳችን ወደ ማስተዳደር ነው፡፡ የመገዳደል እና የመጠላለፍ ታሪካችን ቀብረን የይቅርታ እና የመተባበር ችግኝ እያፀደቅን ነው፡፡ እኔ አውቅላችኋለሁ የሚል ስርዓት አስወግደን የህዝብ ፍላጎት የሚያዳምጥ ስርዓት እያነፅን ነው፡፡

ሰኔ 16/2010 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ በከፊል

በነገራችን ላይ ሙህራዊ ትንታኔን በራሳቸው መንገድ እንስጣችሁ እያሉ እንደሚያስቸግሩን ቡድኖች ትንታኔ የሕዝብን ፍላጎት ማዳመጥ ሕዝባዊነት ሳይሆን ሕዝበኝነት ነው፡፡ ለነርሱ ዲሞክራዊ ራሱ ሕዝበኛ ነው፤ ማለትም የሕዝብ ድጋፍ ለማግኘት ብቻ በረዥም ጊዜ ሀገርን እና ህዝብን የሚጎዱ ፖሊሲዎች የሚተገበሩበት ለማለት ነው፡፡ በዚህ አመት ውስጥ የጊዜው የሕወሓት ፖለቲካ ተቀኝ የሆነው አቶ ጌታቸው ረዳ ፋና ቴሌቪዥን ላይ ቀርቦ “የራስን ሀሳብ ይዞ ሕዝብ እንዲቀበልህ በማድረግ ማታገል ከባድ ነው፡፡ ነገር ግን ሕዝብ ያነሳውን ሀሳብ ይዞ መጓዝ ለአንድ ፖለቲካ ድርጅት ቀላል ነው፣ ስለዚህ የፖለቲካ ድርጅት የመጀመሪያውን ሲያደርግ ነው የሚወደሰው” ሲል ሰምቸዋለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ ፀረ-ዲሞክራሲያዊነት የታለ ታድያ፡፡

ለማንኛውም በረዥም ጊዜ ሀገርን የሚጎዳ ፖሊሲ የተገበረው ማን እንደሆነ የሚታይ ሀቅ ነው፡፡ አሁን ሀገር ለ27 አመት ከነበረችበት አዚም ለማላቀቅ አዲስ ስልት የምንከተልበት ወቅት ነው፡፡ ይህ አዲስ ስልት በእርቅና በይቅርባይነት የሚመራ በመሆኑ አጥፊዎችን እንደቀደሙት ማሰር፣ መግረፍ፣ ብሎም መግደል አይችልም፡፡ በዚህ ምክንያ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ለውጡ ይቀለበሳል የሚል ስጋት ውስጥ ናቸው፡፡ ግን በትክክል ካሰብነው ከህዝብ ውጭ ያለ እና የቀደመ ስርዓቱን ኑ ልጫንባችሁ የሚል አካል ባይታሰር፣ ባይሳደድ ምን ሊያመጣ ይችላል? ይህ ማለት ግን በትክክል ማስረጃ ሲረጋገጥ አይያዙም ማለት አይደለም፡፡

የለውጥ አፍራሽ ቅሪቶች
የመጀመሪያው የብዙዎች የስጋት ምንጭ መከላከያው ነው፡፡ አሁንም አብዛኞች እንደሚሉት ስጋቱ በመከላከያው ውስጥ የሚበዙት ተጋሩ ጀነራሎች መኖራቸው ሳይሆን የነፃ አውጭ ግንባር አባል የነበሩ፣ በዚያ ላይ የነፃ አውጭው የፖለቲካ ክንፍ የነበረው የማርክሲስት ሌኒኒስት ሊግኦፍ ትግራይ (ማልሊት) ካድሬ የነበሩ ናቸው፡፡ በእውነት ከተነጋገርን እነዚህ ሰዎች በትክክለኛው ወታደራዊ ሳይንስ መለኪያ ጀኔራል መሆን ያማይገባቸው ጀኔራሎች ናቸው፡፡

ሰኔ 23/2010 ዓ.ም በባህር ዳር ስታዲዮም የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ በከፊል

የመጀመሪያው ነጥብ አብዛኞቹ ትምህርት ያልተማሩና ዘመናዊ የመከላከያ ሰራዊት እንዴት እንደሚገነባ እና እንደሚመራ የማያቁ ናቸው፡፡ ለዚህም የቀድሞው ኢታማጆር ሹም ጀኔራል ፃድቃን ገብረተንሳይ የተናገሩትን እንደአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ አብዛኞቹ ተምረዋል እንዲባል ብቻ በአመት ሁለት እና ሶስት ክፍል እያለፉ ወረቀት እንዲኖራቸው የተደረጉ ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያት መከላከያ ሰራዊቱ ደካማ እንደሆነ ለማሳየት በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ግጭት ላይ በኛ በኩል ያለቀውን የሰው ቁጥር መጥቀስ በቂ ነው፡፡ በተነፃፃሪው ወገን በኩል በአንፃሩ ትንሽ ሰው ሞቶባቸዋል፡፡

ሁለተኛው ነጥብ እነዚህ ሰዎች ጀኔራል ሊሆኑ የማይገባቸው አሁንም ድረስ የፖለቲካ በአመለካከት በትጥቅ ትግል ከነበሩበት የማሌሊት አስተሳሰብ እና በተግባር ከዚሁ ቡድን የእዝ ሰንሰለት አልተላቀቁም፡፡ በትጥቅ ትግል የፖለቲካ ትምህርት ሲያሰተምሯቸው የነበሩ የማሌሊት አመራሮች አሁንም ተፅዕኖ ስለሚያሳድሩባቸው ገለልተኛ ሆነው ህዝብን የማገልገል እና የሀገር መከላከያ ሰራዊት የመገንባት ብቃታቸው አነስተኛ ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ በቅርቡ የቀድሞው የኢንሳ ዳይሬክተር ሜጄር ጀኔራል ዶክተር… የተናገሩትን ነገር ልጥቀስ፡፡ እኒህ ሰው ቃለ መጠይቅ ሲጀምሩ የፖለቲካ ጉዳይ እንደማያገባቸው እና እርሳቸው ወታደር መሆናቸውን ቢጠቅሱም ሁለት ሶስት ደቂቃ ሳቆዩ ሙሉ በሙሉ ስለፖለቲካ ስልጣን፣ ስለአይዶዎሎጂ ብዙ ዘባርቀዋል፡፡ ሶስተኛው ነጥብ በአሁኑ ሰዓት አብዛኞቹ ጀኔራሎች ያረጁ እና አዲስ አስተሳሰብ ለመቀበል የሚያዳግታቸው መሆኑ ነው፡፡

ታድያ እነዚህ ጀኔራሎችን ተማምኖ ህጋዊ የሆውን አስተዳደር ለመቀልበስ መሞከር ፍፁም የማይሰራ እና ኪሳራው የመዛ መንገድ ነው፡፡ ሲጀመር እነዚህ ጀኔራሎች ማለት ከ300 ሺህ የኢትዮጵያ ሰራዊት አይደሉም፡፡ የደርግን ስልጣን የተቆጣጡሩት የጦሩ የበታች ሹማምንቶች እና በኋላም በ1981ዓ.ም የነጀኔራል ደምሴ ቡልቶን መፈንቅለ መንግስት ያከሸፉ እና በጀኔራሎቹ ላይ እርምጃ የወሰዱ የበታች መኮንኖች እንደነበሩ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሐይል ሊያገለግል የሚችለው እንደእስካሁኑ የፖለቲካ መሪዎችን ሀሳብ ለማስቀየር ለማስፈራሪያ ብቻ ነው፡፡ ያ እንዳይሆን ደግሞ ዶ/ር አብይ አርፈው እንዲቀመጡ እና ፖለቲካ ላይ እንደማያገባቸው ነግሯቸዋል፡፡ ሲቀጥልም አርፈው እማይቀመጡ ከሆነ በሕገ-መንግስቱ በግልፅ የጦር ሠራዊቱ ጠቅላ አዛዥነት ስልጣን የተሰጠው ሰው የፈለገውን መሾምም ሆነ መሻር ይችላል፡፡ ከዚህ ውጭ ያለ ማንኛውም የመከላከያና የደህንነት መዋቅር ለአሰራር እንጅ በስልጣን ከጠቅላዩ እዝ ስረ በታች ነው፡፡ የመከላከያ ምክር ቤት አልያም ሌላ አሰራር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጦሩ ላይ ሊያካሂድ የሚፈልገውን ለውጥ አይገድብም፡፡ ነገር ግን አሁንም የመጠቃቃት እና የመጠላለፍ ፖለቲካን በማስወገድ በይቅርታ የተመሰረተ የፖለቲካ ባህል በመመስረት ለትውልድ ለማስተላለፍ ያለውን እድል ለመጠቀም ትግስት ያስፈልጋል፡፡

ፀጥታን በማደፍረስ የመንግስቱን ተዓማኒነት ማሳጣት

ይህ በዋነኛነት ከደህንነት መዋቅር የቆየ ቅርስ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የማሌሊት ከፍተኛ ሀዋሪያዎች የመንግስትን ስልጣን በኢህአዴግ በተመሰረተው መንግስት አማካኝነት እየመሩም ደህንነቱ ውስጥ የኢ-መደበኛ አመራርነት ሚና ነበራቸው፡፡ በዋነኛነት ደህንነቱ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ከማስከበር ይልቅ የዚህን ቡድን ፍላጎት ለማስጠበቅ እና የጨለማ ስራዎቻቸውን ለማከናወን ይንቀሳቀስ ነበር፡፡

ከዚህ በፊት እንደጠቀስኩት የደህንነቱን ተቋም አመራር መቀየር እንዲሁ በአንድ ደብዳቤ እና ሹመት የሚሆን አይደለም፡፡ በተፈጥሮው ይህ ዘርፍ ኢ-መደበኛ ስለሆነ የአመራር እና እዝ ሰንሰለቱ እንዲሁም ተግባራቱ ኢ-መደበኛነት ይጠናወታቸዋል፡፡ ስለሆነም ደህንነቱ ሶስት አራት ድርብ ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ በተለይም ቆየት ያሉት የማሌሊት አመራሮች ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል፡፡ በታዳጊ ክልሎች ያለው ያልዳበረ የመንግስት መዋቅርን እንዚህ የደህንነት ሰንሰቶች በቀላሉ ማጥቃት ይችላሉ፡፡ በዚህም ምክንያት አብዛኞቹ ታዳጊ ክልሎች የፀጥታ ችግር ሲገጥማቸው ተስተውሏል፡፡ አላማውም በዋነኛነት በአማራ፣ በኦሮሞ፣ በትግራዋይ አልያም በጉራጌ ብሔሮች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በመፈፀም ሕዝብ በመንግስቱ ላይ ያለውን እምነት ማዳከም ነው፡፡
የሕዝብ እምነት ግን እንዲሁ በቀላሉ በወራት ብጥብጥ የሚፈራርስ አይደለም፡፡ ለመገንባት ጊዜ እንደወሰደ ሁሉ ለማፍረስም ጊዜ ይወስዳል፡፡ የአብይ አስተዳደር በህዝብ ያለው እምነት እና ተቀባይነት ከፍ ያለ ነው፡፡ በቀላሉም የሚናወጥ አይደለም፡፡ በነዚህ አጋጣሚዎች ይልቅስ የፌዴራል መንግስቱን መዋቅር ተጠቅሞ አዳዲስ ግጭቶችን በመመርመር ኢ-መደበኛ የደህንነት ሰንሰለቱን በዚያ ውስጥ ለማወቅ እና ለማፈራረስ ምቹ እድል ይፈጥራል፡፡

የሕወሓት ከኢህአዴግ መነጠል፤ የትግራይ ከኢትዮጵያ መገለል
በለውጡ ምክንያት በአብዛኞቹ የሀገሪቱ ክልሎች ህዝቡ በነፃነት ሀሳቡን መግለፅ ችሏል፡፡ ከትግራይና ሌሎች የህወሓት ተፅዕኖ የጎላባቸው ክልሎች ውጭ፡፡ የትግራይ ግን የተለየ ነው፡፡ የህዝቡ ስሜት አሁንም በቅርብ ክትትል በህወሓት የሚቃኝ ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ የሚያዋጣውን እና የሚበጀውን ካለምንም ተፅእኖ ሊገልፅ አልቻለም፡፡ የአብዛኞቹ የሀገራችን እስርቤቶች ደጅ ሲከፈት እና ኢትዮጵያውያን በይቅርታ ሲዎጡ አሁንም የትግራይ ድብቅ እስርቤቶች በር አልተፈለቀቀም፡፡

በዚህ በኩል በጣም አክራሪ የሆነ ሀሳብ የሚራመደው ትግራይን ከሌላው የመነጠል አዝማሚያ ባላቸው ቡድኖች ነው፡፡ ይህ ሊሆን አይችልም እንደው ያበደ አመራር ተነስቶ እንኳን ይህን ሊያደርግ ቢሞክር ቅዥት ሆኖ ይቀራል፡፡ የትግራይ መሬት እንደ ሸዋ መሬት የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት ነው፡፡ በመሆኑም አኩርፎ በር ዘግቶ መቀመጥ አይቻልም፡፡ ጎጆ ልውጣ ቢባልም የማይሆን ነው፤ ሶማሌ ላንድን መሆን ነው አለና፡፡ ይህም እሚሆነው የትግራይ ህዝብ ያበደ አመራሩን በቃህ ማለት ካልቻለ ነው፤ ያ ደግሞ የማይታሰብ ነው ትግራይ ሲበቃው ጨዋታው ያበቃል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከዚህ ደረጃ ከደረስን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የአብይ አስተዳደር የማያውጅበት አልያም ወንጀል የፈፀሙ አመራሮችን ጠራርጎ የማያስርበት ምክንያት የለም፡፡ ህወሓትም ከኢህአዴግ ቢወጣ እሰየው የሚያስብል ነው፡፡ እንደውም አዝማሚያው የሚከፋ ከሆነ የትግራይን ህዝብ ለማዳን ሲባል መጀመሪያ ሊወሰድ የሚገባው እረምጃ ሕወሓትን ከኢህአዴግ አባልነት ማባረር ነው፡፡ እንደተፎካከሪ ፓርቲ ያለውን መቀመጫ ይዞ በፓርላማ ሊቀጥል ይችላል፣ ክልሉንም እስከሚቀጥለው ምርጫ ማስተዳደር ይችላል፡፡ እስካሁን ያለው ትዕግስት ግን መጀመሪያ ያልተኬደበትን መንግድ እንሞክረው ከማለት ነው፤ እርቅና ይቅርታ ለሁሉም፡፡

ለውጡን ለማስቀጠል
ከላይ ያየናቸው ስጋቶቻችን በሙሉ በምንም መመዘኛ ወደ ኋላ ሊመልሱን አይችሉም፡፡ ነገር ግን ለውጡ ስር እንዲሰድ እና ውጤት እንዲያመጣ የለውጡ ባለቤት የሆነው ሕዝብ እና ኢህአዴግ ውስጥ ያለው የለውጥ ሀይል እራሱን ማጠናከር ይገባዋል፡፡ ለውጡ ውጤት ካላመጣ አሁንም የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ አድሮ ቃሪያ መሆን ነው፡፡ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተገቡ ቃሎችና መና ሆነው የቀሩ ፕሮጀክቶች ያመጡትን መዘዝ ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ ለውጡን ለማጠናከር የመጀመሪያው ትኩረት ብአዴን ላይ መደረግ አለበት፡፡ ብአዴን ለለውጡ ወሳኝ ሚና ቢጫወትም አሁንም ግን ብአዴን ግማሽ በድን አካሉን ይዞ የሚጎተት ፓርቲ ነው፡፡ በሚስተዳድረው ክልል ውስጥ ለውጡን ለመቀልበስ የሚጥሩ ብዙ መስለው አዳሪ ካድሬዎች የታጨቁበት የበታች መዋቅር አለው፡፡ በፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም የበሰለና የጠለቀ ትንታኔ መስጠት የሚችል ከፍተኛ አመራር የለውም፡፡ እስካሁን በፀረ-አማራው በረከት የተቀረፀ የርዕዮተ አለም ትንታኔ አተያይ ነበረው፡፡ ኦሕዴድ በአንድ ቀን እነ አብይን፣ ለማን፣ አዲሱ አረጋን፣ ጠይባን፣ ታከለ ኡማን፣ ኢንጂነር ወርቁን፣ ደ/ር ተረጀ ገረፋ፣ ታየ ደንድአን… እና ሌሎች የቲም ለማ አባላትንና ደጋፊዎችን አላፈራም፡፡ እነዚህ ልጆች ወደመዋቅሩ እንዲገቡ አልያም ሀሳቡን እንዲደግፉ ቀደም ብሎ ሰርቷል፡፡ የብአዴንን አባለት ስብዕና ከራሱ ይልቅ ህወሓት ጠንቅቆ ያውቅ ነበር፡፡ ሕወሓትን የሚመስሉትን በብአዴን መዋቅር ሰግስጎ ለአማራ የሚቆረቆሩትን አስቀድሞ ሲመነጥር ኖሯልና፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ብአዴን አንድም የሚያውቀው ነገር የለም፤ እግሩ ቢቆረጥ እንኳ አይሰማውም ነበር፡፡ አሁን ባጭሩ በአጭሩ ብአዴን ለውጡን የሚመጥን አመራር ያስፈልገዋል፡፡ እራሱ ያመጣው ለውጥ እየጎተተው ነው፤ ፍጥነት ካላስተካከለ እራሱን ያጠፋል፡፡ ቢያንስ በቅርቡ ኦህዴድ ያደረገውን አይነት እርምጃ በሁለት እጥፍ መውሰድ አለበት፡፡ አዳዲስ ፋኖዎችን ከዝቅተኛ መዋቅሩ ጀምሮ ማስገባት፣ በብአዴን ውስጥ የህወሓት ወኪሎችን ማፅዳት፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ድሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) በአጋጣሚ ሆኖ በሀዋሳው ብጥብጥ ምክንያት የአመራር ለውጥ በመደረጉ እራሱን ለማደስ ተመቻችቷል፡፡ ሰዎች በፈቃዳቸው ስልጣን መልቀቃቸው ድርጅቱን በአዲስ ደም እና አስተሳሰብ ለመገንባት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ አንዳንዶች የአመራር ቀውስ እንዳያጋጥም ይሰጋሉ፤ እንደዛ የሚለው ክርክር ውሀ የሚቋጥረው የሚለቁት ሰዎች የማይተኩ ቢሆኑ ነበር ፡፡ ነገር ግን የሚለቁት አመራሮች አይደሉም ገዥዎች ነበሩ፤ ይህን ሕዝብ በይፋ ተናግሯል፡፡ ይልቅስ የሚለቁት ሰዎች ከኢ-መደበኛ የደህንነት መዋቅሩ ጋር እንዳይመሳጠሩ እና ግጭት እንዳይፈጥሩ ሀገራዊ ደህንነቱ ቶሎ ሪፎርም አድርጎ ሀገራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ቢጀምር ይሻላል፡፡

በመጨረሻም እንደ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ያሉ ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ ካላቸው ግለሰቦች እና ፓርቲዎቻቸው ጋር ትብብር መመስረት ሊሰመርለት ይገባል፡፡ የትግራይ ህዝብ አማራጭ እንዲያገኝ ማገዝ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች ይበልጥ ትግራይ ለ40 ዓመት በህወሓት ጭቆና ኖሯልና፣ ሌላ አማራጭ እንዳለ ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ በመጨረሻም “አሁን ፍቅር ካላሸነፈ፣ መቸም አያሸንፍም!” ብል ግብዝ አትበሉኝ፡፡


ለፀሃፊውን በፌስቡክ Mulugeta B. Teferiወይም በኢሜል [email protected] ማግኘት ይቸቻላል፡፡