የሱዳኑ ፕሬዚዳንት አልበሽር ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ የተላከላቸውን መልእክት ተቀበሉ።

የሱዳኑ ፕሬዚዳንት አልበሽር በድንበር አካባቢ የፀጥታ ችግር መከሰቱን ተከትሎ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ የተላከላቸውን መልእክት ተቀበሉ።

የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር ሰሞኑን በኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር አካባቢ ተስተውሎ የነበረውን የፀጥታ ችግር ተከትሎ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተላከላቸውን መልእክት ተቀብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለሱዳኑ ፕሬዚዳንት የላኩትን መልክእትም የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ናቸው ያደረሱት።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በዚሁ ወቅትም ከሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር ጋር ሰሞኑን በሁለቱ ሀገራት ድንበር ላይ በተስተዋለው የፀጥታ ችግር ዙሪያ ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር አካባቢ የተከሰተው ግጭት የሁለቱ ሀገራት ስትራቴጂካዊ ግንኙነት የማይጎዳ መሆኑን እና ግንኙነቱም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አስታውቀዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከሱዳኑ አቻቸው ኤል ዲልደሪ ሞሃመድ አህመድ ጋርም ተገናኝተው ተወያይተዋል።

ውይይቱን ተከትሎ በሰጡት መግለጫም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ፥ በሁለቱ ሀገራት መካከል ስትራቴጂካዊ ግንኙነት እንዳለ በመጥቀስ ኢትዮጵያ ከድንበር ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን በሙሉ ለመቅረፍ ትሰራለች ብለዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም በሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢ የሚነሱ ችግሮች እንዲፈቱ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ መግለፃቸውንም ዶክተር ወርቅነህ ተናግረዋል።

የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽርም በድንበር አካባቢ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ላይ ተፅእኖ በማይፈጥር መልኩ ለመፍታት እንደሚሰሩ አስታውቀዋልም ብለዋል።

የሱዳኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤል ዲልደሪ ሞሃመድ አህመድ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እና የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር ይህንን ችግር ለመቅረፍ በጋራ እንደሚሰሩ ማስታወቃቸውንም ገልፀዋል።

ኤፍቢሲ ሱዳን ትሪቡንን ጠቅሶ እንደዘገበው ኢትዮጵያን ከሱዳን በሚያዋስነው ደንበር አካባቢ የእርሻ መሬት ይገባኛል በሚል ምክንያት የፀጥታ ችግር ተከስቶ እንደነበር ይታወሳል።

ምንጭ፦ www.sudantribune.com


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE