ዋጋዎችን ትክክለኛ ማድረግ (በጌታቸው አስፋው)

ዋጋዎችን ትክክለኛ ማድረግ
***
በጌታቸው አስፋው
(የብሔራዊ ኢኮኖሚ ዕቅድ ባለሙያ)
***

ባለፈው ጽሑፌ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት በግማሽ መቀነስ እንዳለበት ለኢኮኖሚ ባለሙያዎችና ለመንግሥት አስተያየት አቅርቤ ነበር፡፡ ዛሬም ይህንኑ አስተያየቴን የሚያበለጽግ ጽሑፍ ይዤ ቀርቤአለሁ፡፡ ግብዓተ ምርቶችና ምርቶች ትክክለኛ ዋጋቸውን ሳያገኙ በፊት ለማደግ የሚደረግ ሩጫ መጨረሻው ግብ ላይ ሳይደርሱ ተደነቃቅፎ መውደቅ ነው፡፡ ኢኮኖሚስቶች ይህንን እውነታ getting the prices right በማለት ይገልጹታል፡፡ የሠራተኛው የሥራ ዋጋ ደሞዝ፣ የካፒታል ዋጋ ወለድ፣ የመሬት ዋጋ ኪራይ፣ የድርጅት ዋጋ ትርፍ፣ የቁሳዊ ምርትና የአገልግሎት ምርት ዋጋዎች ሁሉም በተወዛገበ የዋጋ አወሳሰን ሥርዓት ውስጥ ሆነው የተረጋጋ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ሰማይን ለመቧጠጥ እንደመሞከር ነው፡፡

ሁላችንም ኢኮኖሚያችን እንዲያድግ እንፈልጋለን፡፡ ኢኮኖሚው በጤናማ ሁኔታ እንዲያድግ ግን በቅድሚያ የዋጋ አወሳሰን ሥርዓቱ መስተካከል አለበት፡፡ በገበያው ውስጥ ግብዓተምርቶችና ምርቶች ትክክለኛውን ዋጋቸውን እንዲያገኙ ማድረግ ከቻልን ስለዕድገቱ ገበያው ራሱ ያስብበት ነበር፡፡ ዐይናችንን ጨፍነን ወደ የማናውቀው ግብ ከመሮጥ ዕድገትን በዋጋ መረጋጋት ሥርዓት ውስጥ ለማምጣት ግብዓተ ምርቶችም ሆኑ ምርቶች ትክክለኛ ዋጋቸውን ማግኘት አለባቸው፡፡

ሠራተኛውም ካፒታሉም መሬቱም ድርጅቱም በምርታማነታቸው ልክ የሚገባቸውን ካላገኙ ግን የሚገኘው ተጨማሪ ገቢ ከዕድገት የመጣ ሳይሆን አንዱ ሌላውን እየበዘበዘው ነው፡፡ በአንድ ነጥብ ሁለት ሚልዮን ካሬ ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት ላይ ያለን፣ ከመቶ ሚልዮን በላይ የሆነ ሕዝብ በዝብዛ በፍጥነት ባደገች የአምስት መቶ ካሬ ኪሎ ሜትር የአዲስ አበባ ምድር ላይ የምንገኝ ጥቂት ሰዎች የራሳችንን ማደግ የአገሪቱ ዕድገት አድርገን እንቆጥራለን፡፡

በአዲስ አበባዋም ቢሆን ከጥቂት ተጠቃሚዎች በስተቀር የዋጋ አወሳሰን ሥርዓት መዛባት ያላስመረረው ኢትዮጵያዊ የለም፡፡ ቤተሰቦች በሸቀጦች ዋጋ አወሳሰን ሥርዓት ተማረዋል፤ ድርጅቶች በካፒታልና በጥሬ ዕቃ ዋጋ አወሳሰን ሥርዓት ተማረዋል፤ ሠራተኞች በደሞዝ አወሳሰን ሥርዓት ተማረዋል፡፡ የግብዓተ ምርቶችም ሆነ የምርት አገበያይ የሆነው ጥሬ ገንዘብ በሩጫ እንዲያድግ በመደረጉ በሩጫ በተወሰኑት ዋጋዎች ላይ መዛባትን አስከተለ፡፡ የአንዳንድ ግብዓተ ምርቶችና ምርቶች ዋጋዎች ከልክ በላይ ወደ ላይ ሲምዘገዘጉ የሌሎች ግብዓተ ምርቶችና ምርቶች ዋጋዎች ተንቀረፈፉ፡፡

ከግብዓተ ምርቶች ውስጥ የመሬት አገልግሎት ዋጋ ኪራይ ያለቅጥ ወደ ላይ ተምዘገዘገ፣ የካፒታል አገልግሎት ዋጋ ወለድ ለቆጣቢዎች ሲንቀረፈፈ ለባንኮች ግን ከሚገባው በላይ ወደ ላይ ተምዘገዘገ፣ የሠራተኛ አገልግሎት ደሞዝ በአንዳንድ የሙያ ሥራዎች ወደ ላይ ሲምዘገዘግ በአንዳንድ ሙያና ሙያ አልባ ሥራዎች ተንቀረፈፈ፣ የድርጅት አገልግሎት ክፍያ ትርፍም በአንዳንድ ሥራዎች ያለቅጥ ወደ ላይ ሲምዘገዘግ በሌሎች ዘርፎች ተንቀረፈፈ፡፡

የመሬት ዋጋ በካሬ ሜትር ከመቶ ሺሕ በላይ ሆኖ የአንዳንድ ሰዎች ወርሐዊ ደሞዝ ከመቶ ሺሕ ብር በላይ ሆኖ የአንዳንድ ንግዶች ትርፍ መቶ ከመቶ ሆኖ እነኚህ ዋጋዎች የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ሁኔታ በሚያንጸባርቅ ትክክለኛ የዋጋ አወሳሰን ሥርዓት ነው የተተመኑት ብሎ ማለት ይከብዳል፡፡ ይህ የዋጋ አወሳሰን ሥርዓት የተገነባው በምርታማነትና በውድድር ላይ በተመረኮዘ የገበያ ኢኮኖሚ ሳይሆን የጥሬ ገንዘብ ሥርጭትን በገፍ ባበዛው በተሳሳተ የኢሕአዴግ ልማታዊ ፖሊሲ ነው፡፡

ዋጋ የሀብት ድልድል አድራጊ መሣሪያ ነው፡፡ ማንኛውም ዓይነት ሸቀጥ ግብዓተምርትም ሆነ ምርት ከፍተኛ ዋጋ ማግኘት ይፈልጋል፡፡ ሰዎችም የሚሰማሩበትን የሥራ ዘርፍ የሚመርጡት ከፍተኛ ዋጋ በሚሰጣቸው የግብዓተ ምርትና የምርት ዓይነት መርጠው ነው፡፡

ዋጋዎች ሲዛቡና ትክክለኛ ሳይሆኑ ሲቀሩ ለረጅም ጊዜ ጸንተው መቆየት ይሳናቸዋል፣ በቀናትና በሰዓታት ውስጥ ያለምክንያት ይለዋወጣሉ ሰዎች የሚሰማሩበትን ዘርፍ መምረጥ ያቅታቸዋል ዋጋዎችም ትክክለኛውን የሀብት ድልድል ማድረግ ይሳናቸዋል፣ በዚህን ጊዜም የኢኮኖሚው እድገት ጠማማ ይሆናል፡፡ መመረት የሚገባው ሸቀጥ ሳይመረት መመረት የማይገባው ሸቀጥ ይመረታል፡፡

ዋጋዎች የሚወላገዱት በዋጋ አወሳሰን ሥርዓት አምራቹና ሸማቹ ተመጣጣኝ አቅም ሳይኖራቸው ሲቀር ነው፡፡ በሸማቹ እጅ ያለው ጥሬ ገንዘብ በበዛ ቁጥር ሸማቹ በዋጋ አወሳሰን ከአምራቹ እኩል ያለውን አቅም እያጣ ይመጣል ፍላጎትና አቅርቦት በጋራ የገበያ ዋጋን ይወስናሉ የሚለው የኢኮኖሚክስ ሕግ ጽንሰ ሐሳብ ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡ አምራቹ ምን ዓይነት ምርት ማምረት እንዳለበት አዛዥ የሆነው ሸማች በትክክል አምረቹን ማዘዝ ሲያቅተው መንግሥት አለቦታው ገብቶ አምራቹን በግድ ጎትቶ ወደ ምርት ሊያስገባው ይሞክራል፡፡

የታዳጊ አገራት የድህነት ቀለበት ውስጥ መዘፈቅም በቅድሚያ መመረት የሚገባው ሸቀጥ ሳይመረት መመረት የማይገባቸው ሸቀጦች መመረት ወይም ከውጭ አገር በውጭ ምንዛሪ እየተገዙ መግባት ነው፡፡ የዚህ ምክንያቱም ያደጉት አገራት በሚያሳድሩባቸው በፍጥነት የማደግ ጫና በሚሰጧቸው እርዳታዎችና ብድሮች የነርሱን ሸቀጦች እንዲሸምቱ አድርገው ስለሚቀርጹዋቸው ነው፡፡ የሚያዘጋጁን አምራች አንድንሆን ሳይሆን ሸማች እንድንሆን ነው፡፡

በቂ ገቢ አግኝተው የፈረንጆቹን ሸቀጦች ሸማቾች የሚሆኑትም በአገር ውስጥ ለግብዓተምርቶቻቸውና ለምርቶቻቸው ትክክለኛውን ዋጋ የሚያገኙ ሳይሆኑ የፈረንጆቹን ቀራቅንቦ የሚነግዱ ሰዎችና በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ተግባር ላይና በግል ንግድ አገልግሎት አሰጣጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ የከተማ አገልግሎት ሰጪዎች ወይም የፈረንጆቹን ለታዳጊ አገራት ተብሎ የተነደፉ ፖሊሲዎችን የሚያራምዱ ሰዎች ናቸው፡፡

ግን ምን ሌላ አማራጭ አለን፣ ልማታዊ የእስያ አገራት ቀን እስከሚያልፍ የአባትህ ባሪያ ይግዛህ አባባልን ተጠቅመው ጥርሳቸውን ነክሰው ለጥቂት ዓመታት አብረው ሰርተው ዛሬ ከእነርሱው እኩል የኢንዱስትሪ ምርቶች ኤክስፖርተር ሆነዋል፡፡ እኛ ጥርሳችንን መንከስ ያቃተን የፈረንጆቹ ምርቶች ሸማች ዘናጮች ሆነን መታየት እንፈልጋለን፣ ዝነጣችን የውጭ ምንዛሪው ተሟጦ እስከሚያልቅ ድረስ ብቻ ሆነና አረፍነው፡፡

በጥቂት ሣምንታት ውስጥ የእንቁላል የወተት የቅቤ ዋጋዎች የእጥፍ ያህል ሲጨምሩ፣ ሸማቹ ምንም የማድረግ አቅም አጥቶ የተጠየቀውን ይከፍላል፡፡ ከየት ያመጣዋል? አይባልም፡፡ እርሱም ትክክለኛ ባልሆነ የዋጋ አወሳሰን ሥርዓት ውስጥ ተሰማርቶ በሚያገኘው ገቢ የተጠየቀውን ከፍሎ መሸመት ችሏል፡፡

በሌሎች አገራት የነጻ ያህል ርካሽ የሆኑት ምግብ ነክ ምርቶች እኛ አገር እንደዚህ የሚወደዱት ለምንድን ነው? በእንስሳት ሀብት ከዓለም ዐሥረኛና ከአፍሪካ አንደኛ ሆነን በግብርና የተሰማራው ሕዝባችን ሰማንያ በመቶ ሆኖ ከዓለም ቁጥር አንድ የገበሬ አገር ሆነን በእንስሳት ተዋጽኦ አመጋገብ ከአፍሪካ ግማሽ ደረጃ ላይ እንኳ ያልደረስነው ለምንድን ነው፡፡

በእዚህ የዋጋ አወሳሰን ውዥንብር ውስጥ ሆነን የመንግሥት ድርጅቶችን ወደ ግል በማዞር ዘዴ ፈረንጆች ሊታደጉን ይሁን ለራሳቸው ሊከብሩብን ሸብ ረብ እያሉ ነው፡፡ የዋጋ አወሳሰን መዛባቱን ያስተካክሉልን ይሆን ወይስ ያባብሱብናል፡፡ እነርሱ የሚጠቀሙት ከማባባሱ ነው ወይስ ከማስተካከሉ ይህን በቅድሚያ ማወቅ የእኛ የቤት ሥራ ነው፡፡ እነርሱ ቤት ሥራውን አይሠሩልንም፤ እኛ በምናነጥፈው ምንጣፍ ላይ ዘለው ለመቀመጥ ነው ዝግጅታቸው፡፡

ስለ ነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ከመጠን በላይ አክብደው ቀስ በቀስ ከፈረንጆቹ ተምረን እንጂ ዛሬ ልንደርስበት አንችልም ብለው የሚያስቡ ብዙዎች ናቸው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ትክክል እንዳልሆነ በትንሹ ያልተማረ በትልቁ ሊገባው እንደማይችል በብዙ ጽሑፎቼ ገልጬአለሁ፡፡ ከበርካታ ጽሑፎቼ እንደ ምሳሌ የተጠቀምኩትን ያደኩበትን መንደር የዋጋ አወሳሰን የገበያ ሁኔታ ለግንዛቤ ያህል በድጋሚ አነሳለሁ፡፡

ዴዶ (ሼኪ) ከጂማ ከተማ ሃያ ኪሎሜትር የምትርቅ የወረዳ ከተማ ስትሆን ሰባት ዓመት ሞልቶኝ ለትምህርት ወደ ጂማ እስከመጣሁበት ጊዜ ያደኩባት ከተማ ናት፡፡ የዴዶ ከተማና የአካባቢዋ ቀበሌዎች ኗሪዎች የሚገበያዩት በሳምንት አንድ ቀን ቅዳሜ በሚውል ገበያ ነው፡፡ ቅዳሜ ገበያተኛው ከጧት ጀምሮ ወደ ገበያው ቦታ የተማል፡፡ ሦስት አራትና አምስት ሰዓት ላይ ገበያ ለመሄድ የቸኮሉ ወላጆችና ጎረቤቶች የመንደሩን ልጆች የገበያውን መሞቅ አለመሞቅ አማትራችሁ አይታችሁ ንገሩን ይሉን ነበር፡፡

ስድስት ሰባት ስምንትና ዘጠኝ ሰዓት ደርሶ ገበያው ሳይሞቅ፤ ሳይደራ ወይም ፈረንጆቹ እንደሚሉት ገበያው ሳይጠራ (Market Perfection) በፊት የገበያው መረጃ አነስተኛ ስለሚሆን ወይ ሻጩ ከገበያ በላይ በሆነ ዋጋ ሽጦ ሸማቹን ያሞኘዋል ወይ ሸማቹ ከገበያ በታች በሆነ ዋጋ ገዝቶ ሻጩን ያሞኘዋል፡፡ ከስድስት እስከ ዘጠኝ ባሉት ሰዓታት ግን ገበያው ይሞቃል ወይም ይደራል የገበያው መረጃም እንደልብ ይገኛል ወይም እንደፈረንጆቹ አጠራር ገበያው ይጠራል፣ አቅርቦትና ፍላጎትን እኩል የሚያደርጋቸው የገበያ ማጣሪያ ዋጋ (Market Clearing Price) ይፈጠራል፡፡ ሊመሽ ተቀርቦ ገበያው መነሳት ከጀመረበት ከዘጠኝ ሰዓት ጀምሮም የጠዋቱ የገበያ አለመጥራት ሁኔታ ይደገማል አብዛኛው ሸማችም ሻጭም ወደ ቤቱ በመሄድ ላይ ስለሚሆን ገበያው እንደገና ይቀዘቅዛል፤ ዋጋዎች ከነጋዴ ነጋዴ ይለያያሉ፤ ይዘበራረቃሉ፡፡

ይህን የገበያ ባሕርይ አጥንቶና አጠቃላይ መርህ አድርጎ ነው አዳም ስሚዝ የነጻ ገበያ ኢኮኖሚን ወይም የሊብራል ገበያ ኢኮኖሚን የተነተነው፡፡ አዳም ስሚዝ ከኹለት መቶ ሐምሳ ዓመት በፊት ተመራምሮ የጻፈውን ነው እኛ ዛሬ አንብበን መረዳት ያቃተን፣ የዴዶ ገበያ በሰባትና ስምንት ሰዓታት ላይ የተስተካከለው በሰው ትዕዛዝ አይደለም የነጻ ገበያ ወይም የሊብራል ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት ብሎ አዳም ስሚዝ በሚጠራው ስውር እጅ (The Invisible Hand) ነው፡፡

ዴዶ የኢትዮጵያ ገበያ ኢኮኖሚ ተምሳሌት ልትሆን የምትችል ናት፣ በዛሬው የአዲስ አበባ አትክልት ተራ ከስልሳ ዓመት በፊት በዴዶ ሰባት ስምንትና ዘጠኝ ሰዓት የሚፈጠረው የጠራ ገበያ ሥርዓት ጠፍቶ በቀናት ውስጥ ሽንኩርትና ቲማቲም ከአምስት ብር ወደ ሃያና ሠላሳ ብር መልሶ መላልሶ ሲቀያየርብን ይህን የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ አልተነተንም ምክንያቱንም አላወቅንም፡፡

ከስልሳ ዓመት በፊት እንደነበረው እንደ ዴዶ ገበያ ተሞክሮ ምን ጊዜም የገበያ ጉድለት የሚከሰተው በሸቀጥ ማነስ፣ በሸማችና በሻጭ ተገበያዮች ቁጥር አለመመጣጠን፣ ገበያው ሲጠብና የገበያው መረጃ ለገበያተኞች ሳይደርስ ሲቀር ሸማቾች ለመግዛት ሲስገበገቡና ሻጮችም ለመሸጥ ሲስገበገቡ ነው፡፡
ትክክለኛ የገበያ ዋጋ የሚፈጠረውም በሚያወጣው ወጪ ወይም በሚከፍለው ክፍያ ልክ ከሸቀጡ የሚያገኘውን ጥቅም የላቀ ለማድረግ የሚመርጥ አዋቂ ሸማችና ማምረት በሚችለው አቅም ልክ ትርፉን የላቀ ለማድረግ በሚሠራ አዋቂ አምራች መኖር ነው፡፡

በትናንሾቹ በምግብ ወጪዎቻችን እንኳ በሚከፍለው ልክ የሚያገኘውን ጥቅም የላቀ ለማድረግና ማምረት በሚችለው ልክ ትርፉን የላቀ ለማድረግ የሚጣጣር አዋቂ ሰው ሳይኖር ከተቀረው ዓለም እኩል የቴክኖሎጂ ምርቶችን ለመሸመትና አምርቶ ለመሸጥ የሚችል አዋቂ ሊሆን እንዴት እንደሚችል ማሰብ ይከብዳል፡፡ በእንቁላሉና በወተቱ የገበያ መር ኢኮኖሚን ሳናዳብር ከፈረንጆች ጋር የአክስዮን ገበያ ውድድር ውስጥ እንዴት ነው የምንገባው?

መንግሥት መሠረተልማቶችን ለውጭ መዋዕለንዋይ አፍሳሾች ለሽያጭ ማቅረቡን ብዙ ሰዎች በድጋፍም በተቃውሞም ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡ ከሥር መሠረቱ ይህ ዓይነት የውጭ መዋዕለንዋይ ከውጭ ቀጥታ መዋዕለንዋይ (Foreign Direct Investment) የተለየ ስለሆነ ምን እንደሆነና እንድምታው ምን ሊሆን እንደሚችል ግን የሚገባውን ያህል አልተብራራም፡፡ ይህ ዓይነት መዋዕለንዋይ የኪሣራ ስጋትን ለመቀነስ ሀብትን በተለያዩ የአክስዮንና ቦንድ ሰነዶች የተለያዩ ኪሶች ባሉት ቦርሳ መከፋፈል (Portfolio Investment) የኮሮጆ መዋዕለንዋይ ይባላል፡፡ በዚህ ዓይነት መዋዕለንዋይ ትርፍ የሚገኘው ምርት አምርቶ ለገበያ ከማቅረብ ብቻም ሳይሆን በግብዓተምርትና በምርቶች ዋጋዎች መለዋወጥ ምክንያት ከሚገኝ ንፋስ አመጣሽ ትርፍም ነው፡፡

ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ ገበያዎቿ ያልተረጋጉ ስለሆኑ በሸቀጦች ዋጋ አወሳሰን ሥርዓትም ሸማቹ አቅም የሌለውና አምራቹ ብቻውን ዋጋ ወሳኝ ስለሆነ ወደፊት የሰዎችን ገቢ ለመጨመር ወይም ለወጣቱ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ተብሎ የጥሬገንዘብ አቅርቦት በገፍ ሲጨምር የሸቀጦች ዋጋ የባሰ ይንራል፡፡ ይህም የብራችንን የመግዛት አቅም አዳክሞ በውጭ ምንዛሪ ገበያ ውስጥ የብር ዋጋ ስለሚረክስ አክስዮን የገዛ ወይም በቦንድ ብድር መዋዕለንዋይ ያፈሰሰ የውጭ ሰው በተሸጡት ድርጅቶች ከአምራችነት ባያተርፍም እንኳ ሌላው ቢቀር ከንፋስ አመጣሽ ትርፍ ብቻ የእኛ ሀብት ወደርሱ ይፈሳል፡፡

ለውጭ አገር ባለሀብቶች የኮሮጆ መዋዕለንዋይ ሽያጭ ዕድል መስጠት ማለት አክስዮኑን የገዛው ሰው ድርሻውን ይዞ ይቀመጣል ማለት ብቻም አይደለም፡፡ አክስዮኑን በኹለተኛ የአክስዮን ገበያ እንዲሸጥ ድርጅቶቹ በአገር ውስጥ በተቋቋመ ወይም በውጭ አገር ባለ ሁለተኛ የአክስዮን ገበያ (Stock Exchange) መመዝገብ አለባቸው፡፡

በዓለም ዐቀፍ ግብይይት ውስጥ አገሪቱ መግባቷን ብደግፍም አዋቂ ተገበያይ ኢኮኖሚያዊ ሰው ሆኖ በቅጡ ወተትና እንቁላል በነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት መገበያየት ያልቻለ የእኛ አገር ሰው ከፈረንጆቹ እኩል የድርጅቶችን ዋጋ የሚተምኑ የአክስዮን ዋጋዎችን በትክክል ተምኖ እንዴት ተወዳዳሪ ሊሆን እንደሚችል ግን ያሳስበኛል፡፡