በሱዳን ጦር እና በጎንደር ገበሬዎች መካከል ጦርነቱ ተፋፍሟል።

“መንግስት” አልባው ሕዝብ ከሱዳን ጋር ሊገጥም ነው (ጌታቸው ሽፈራው)

ባለፉት ሳምንታት የሱዳን ጦር በአማራ ገበሬዎች ላይ ጦርነት ከፍቷል። ትናንት ሰኔ 25/2010 ዓም ገበሬዎች ከሱዳን ሰራዊት ጋር ውሏቸውን ሲታኮሱ ውለዋል። የሱዳን ጦር አፈና የፈፀመባቸውን 70 ያህል ገበሬዎች ነፃ ለማውጣት በተደረገ ጦርነት ብዙ ገበሬዎች ተገድለዋል። ቆስለዋል።

በጦርነቱ የተሰውት ላቀው ሰለሞንና ገብሬ አውለው አስከሬን ወደ ቤተሰብ ሲላክ ከአምስት በላይ ገበሬዎች ቁስለኛ ሆነዋል።

የአቶ ለቀው ሰለሞን እና የገብሬ አውለው መገደል ከተሰማ በኋላ የመተማ፣ የሸህዲና የአርማጭሆ ህዝብ ከሱዳን ጦር ጋር ለመግጠውም መወሰኑ ተሰምቷል። በዛሬው ዕለት የመተማ ነዋሪዎች በአይሱዚ መኪና ጦርነት ወደተነሳበት ደለሎ እየሄዱ መሆኑን ገልፀውልኛል።

የ”ኢትዮጵያ መከላከያ” ሰሞኑን ወደ ደንበር ቢጠጋም የኢትዮጵያ ገበሬዎች በሱዳን ጦር ሲዘመትባቸው ዳር ዳር ተመልካች ሆኗል። ዛሬ ሰኔ 26/2010 ዓም የአማራ ልዩ ሀይል ከሕዝቡ ጋር ወደ ደለሎ መሄዱም ተጠቁሟል።

የአማራ ገበሬዎች የሀገር ዳር ድንበር ጥሶ የመጣው ጦር ጋር ፊት ለፊት ገጥመው የመከላከያ ሰራዊቱ ከድንበር ርቆ ከርሟል። መንግስት ነኝ የሚል አካልም ሆነ ስለ ሀገር ዳር ድንበር ያገባኛል የሚል አካል ስለ ገበሬዎቹ ሞት ጆሮ አልሰጡም። የአማራ ገበሬ የድጋፍ ሰልፍ ሲወጣ ኢትዮጵያዊ ይባል፣ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በቃታ ብረት እየጠበቀ ሲሰዋ ግን ሞቱን የሚያወራ የለም። በወራሪ ጦር ሲገደል አማራ ነው!