የአስክሬን የላብራቶሪ ውጤት ከመምጣቱ በፊት የቀብር ሥነ-ሥርዓት መፈጸም አይቻልም የሚለው መመሪያ ተሻሻለ

ለ14 ቀናት የነበረውን አስገዳጅ የለይቶ ማቆያ ወደ 7 ቀናት ብቻ እንዲሆን ተወስኗል።
ኢዜአ  —  በተለያዩ ምክንያቶች ለሞት የሚዳረጉ ዜጎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ በማህበረሰቡ የቀብር ሥነ-ሥርዓት እንዲፈጸም ተፈቀደ።
የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር ባሉ አንዳንድ መመሪያዎች ላይ ማሻሻያ መደረጉን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ተናግረዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በዛሬው ዕለት ለኢዜአ በሰጡት መግለጫ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መመሪያዎች ላይ ማሻሻያ መደረጉን ተናግረዋል።
በማሻሻያው መሰረት በተለያዩ ምክንያቶች ለሞት የሚዳረጉ ዜጎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ በማህበረሰቡ የቀብር ሥነ-ሥርዓት መፈጸም ተፈቅዷል።
ይህም ከዚህ ቀደም የአስክሬን የላብራቶሪ ውጤት ከመምጣቱ በፊት የቀብር ሥነ-ሥርዓት መፈጸም አይቻልም የሚለውን መመሪያ መሻሻሉን ዶክተር ሊያ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ በቀብር ሥፍራ ላይ ከዚህ ቀደም የተቀመጠው 50 ሰዎች ብቻ ተገኝተው ሥርዓቱን ማካሄድ አለባቸው የሚለው መመሪያው አልተሻሻለም ብለዋል።
ግለሰቦች በኮሮና ቫይረስ ቢያዙ የሚያገለግሏቸው የቤተሰብ አባላትንና የራሳቸውን ፍላጎት ከግምት በማስገባት ተፈጻሚ የሚሆን መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የግሰለቦችን የአኗኗር ሁኔታ በተቀመጠው መመሪያ መሰረት አግባብ ከሆነ በቤታቸው እንዲቆዩ እንደሚደረጉም ተናግረዋል፡፡
ከውጭ የሚገቡ ሰዎች በተለይም ወደ አገር ከገቡ በኋላ ባለፉት 3 ቀናት ውስጥ ከመጡበት አገር ተመርምረው ነጻ መሆናቸውን የሚያሳይ መረጃ ይዘው ከመጡ ናሙና ተወስዶ በቤታቸወ 14 ቀናት እንዲቆዩ ይደረጋልም ተብሏል።
በሌላ በኩል ነጻ መሆናቸውን የሚያረጋገጥ ሪፖርት ይዘው ለማይመጡ መንገደኞች ናሙናቸው ተወስዶ ለሰባት ቀናት በለይቶ ማቆያ እንዲቆዩ ይደረጋል ብለዋል ዶክተር ሊያ።
ይህም ከዚህ ቀደም ለ14 ቀናት የነበረውን አስገዳጅ የለይቶ ማቆያ ወደ 7 ቀናት ብቻ እንዲሆን ተወስኗል።