በግድቡ ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች ካሉ እስከ ሕይወት መሰዋዕትነት ለመክፈል ዘወትር ዝግጁ ነን – የፌዴራል ፖሊስ ም/ኮ/ጀኔራል

በሕዳሴው ግድብ ላይ ለሚያጋጥሙ ችግሮች እስከ ሕይወት መሰዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን – የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል መላኩ ፋንታ

 (ኢዜአ) – በሕዳሴው ግድብ ላይ ለሚያጋጥሙ ችግሮች እስከ ሕይወት መሰዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ሆኖ እየሰራ መሆኑን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል መላኩ ፋንታ የሕዳሴ ግድብ ግንባታን በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በንግግራቸውም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ክንውን እንዲሳካ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ከአጋር የፀጥታ ኃይሎች ጋር ዘብ የቆሙለት ሀገራዊ ኃላፊነት ነው።
የፖሊስ አባላቱ ከፀጥታ ማስከበር ሥራቸው በተጓዳኝ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመሆን ለግድቡ ግንባታ እገዛና ድጋፍ እያደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል።ግድቡ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በገንዘብ፣ በጉልበትና በዕውቀት የተሳተፈበት መሆኑን የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሩ የፌዴራል ፖሊስ አባላትን ላለፉት ሰባት ዓመታት ከደሞዛቸው በማዋጣት አስተዋጽኦ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።ሠራዊቱ የሀገርን ሰላም በማስጠበቅ እንደ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ትልልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ግንባታ እንዲጠናቀቁ የማድረግ ኃላፊነቱን ይወጣል።በሌላ በኩል ደግሞ የማኅበረሰቡ አንድ አካል በመሆናቸው ቦንድ በመግዛትና ስጦታ በመለገስ ድርብ ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ሰፍኖ፣ የሕዝቦች ደህንነት ተጠብቆና የተወጠኑ የልማት ሥራዎች ሳይደናቀፉ እንዲጠናቀቁ ለማስቻል የተጣለበትን ድርብ ሀገራዊ ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጣ መሆኑንም አብራርተዋል።
በተለይም በግድቡ ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች ካሉ እስከ ሕይወት መሰዋዕትነት ለመክፈል ዘወትር ዝግጁ ሆኖ እንደሚጠብቅ አረጋግጠዋል።
ከዚህ አኳያ ሠራዊቱን በሥልጠና ለግዳጅ አፈጻጸም ከማዘጋጀት በተጨማሪ ለፀጥታ ሥራ በሚያስፈልጉ ዘመናዊ መሣሪያዎች የተደራጀ መሆኑን ኮሚሽነር ጀኔራል መላኩ ተናግረዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ እስካሁን 13 ነጥብ 54 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን ከግድቡ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የግንባታው አጠቃላይ አሁናዊ አፈጻጸምም 73 ነጥብ 7 በመቶ ላይ ይገኛል።