አንዳንድ ሚድያዎች በተለይ ሶሻል ሚድያው ላይ፤ ጥግ ይዞ ድንጋይ መወራወር ላይ ነው ያለው – ያ ድንጋይ የሚወረወረው ግን ሕዝብ ላይ ነው፤ ወገን ላይ ነው – አገር ላይ ነው።- ዶ/ር ዘነበ በየነ

BBC Amharic : ባለንበት ዘመን ማኅበራዊው የመገናኛ መድረክን ጨምሮ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ስፍር ቁጥር የሌለውን መረጃ በየደቂቃው ለታዳሚዎቻቸው ያቀርባሉ።

በዚህ ሂደት ውስጥ ጠቃሚና ሐቀኛ መረጃዎች የመቅረባቸውን ያህል አሳሳችና አደገኛ ወሬዎች ተሰራጭተው አለመግባባትና ጉዳትን ያስከትላሉ።

በተለይ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ቁጥራቸው የበዛ የተለያየ አላማ ያላቸው የመገናኛ ብዙሃን ወደ ሕዝቡ እየደረሱ ባሉበት ጊዜ ስጋት የሚፈጥሩባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት የሚባል አይደለም።

ከዚህ አንጻር የታዘቡትንና መደረግ አለበት የሚሉትን እንዲያካፍሉን ዘነበ በየነን (ዶ/ር) ጋብዘናል።

ዘነበ በየነ (ዶ/ር) አሜሪካ በሚገኘው የሚሲሲፒ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት መምህር ናቸው። በአብዛኛው ጥናቶቻቸው መገናኛ ብዙኀን ለሰላምና ለአገር ግንባታ ያላቸውን አስተዋጽኦን ይመለከታል።

በቅርቡ ደግሞ፤ ‘ሁሉ የሚያወራበት፤ አድማጭ የሌለበት’ የሚለው ጥናታቸው በተለይ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ አለ የሚሉትን ነባራዊ ሁኔታን እንደሚገልጽላቸው ይናገራሉ።

መገናኛ ብዙኀን የሚጠበቅባቸውን ከወገንተኝነት በራቀ ሁኔታ ሙያዊ በሆነ መልኩ የሚሰሩ ከሆነ በሕዝብ መካከል መግባባትን ለመፍጠር የመቻላቸውን ያህል በተቃራኒው ከሆኑ ደግሞ አለመግባባትና የሠላም መናጋትን ሊያስከትሉ ይችላሉ።

“ሚድያውን ደፍረን ማስተካከል ካልቻልን፤ ይህቺን አገር ነገ ላናገኛት እንችላለን” ዘነበ በየነ (ዶ/ር)ከዚህ አንጻር ቢቢሲ ለዘነበ (ዶክተር) የሕዝብን ሰላም ሊያናጉ የሚችሉ ዘገባዎች የሚሉዋቸው የትኞቹ እንደሆኑና ሕዝቡ ሐሰተኛውን ከሐቀኛ ዘገባ እንዴት ነው መለየት ይችላል? ለሚለው ጥያቄ መልስ በመስጠት ይጀምራሉ፡

ዘነበ (ዶ/ር)፡ ብዙ ነው። ሌላ አካባቢ የተደረጉ ነገሮችን ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ተደረገ አድርጎ ማቅረብ ኃላፊነት የጎደለው ነው። ከሁሉ በላይ ለአንድ ሚድያ ትልቁ ዋጋው እምነት ነው። አንድን ነገር ሲፈጸም አንዳንድ ሚድያዎች “የሆነው ነገር ምንድን ነው፤ መረጃ ከየት ነው የምናገኘው? ያገኘነው እንዴት ነው የምንጠቀምበት?” ብለው ሊያስቡበት ይገባል።

የሕብረተሰቡን ንቃተ ህሊና መጨመር ያስፈልጋል። ሕዝቡ፣ ውሸት የሚነዙ ሚድያዎችን እርግፍ አድርጎ የሚተዋቸው፤ ንቃተ ህሊናው ከፍ ያለ እንደሆነ ብቻ ነው።

የዛሬ ሦስት ዓመት የተደረጉትን ዛሬ እንደተደረጉ አድርጎ ማቅረብ ከማንም በላይ የሚጎዳው ራሱ ሚድያውን ነው። ለጊዜው ሕዝብን ሊያደናግር ይችላል፤ ከሁሉም በላይ ግን ራሱ ሚድያው ነው ተዓማኒነቱን የሚሸረሸረው።

መንግሥት፤ እንደዚህ ዓይነት ኃላፊነት የጎደላቸው የሚድያ አውታሮችን ተጠያቂ ሊያደርግ ይገባል። ያ ሚድያ መንግሥታዊ ሊሆን ይችላል የግል ሊሆን ይችላል። ምንም ለውጥ የለውም። ኃላፊነት የጎደለው ሥራ እስከሰራ ድረስ፣ መጠየቅ የመንግሥት ግዴታ ነው። መንግሥት የሕዝብን ደኅንነት የመጠበቅ ግዴታ አለበት

ቢቢሲ፡ ከዚህ በፊት በነበረው የኢህአዴግ ሥርዓት፡ ሚድያው የመንግሥት አፈቀላጤ ሆነ ተብሎ ሲተች ነበርና፣ አሁን በዚህ ሁለትና ሦስት ዓመታት ውስጥ በሚድያው ላይ ምን ለውጥ ተመለከቱ?

ዘነበ (ዶ/ር)፡ ይህ ተደጋግሞ ሲነሳ እሰማለሁ። “መንግሥት ተለውጧል፤ ሚድያውስ ለውጧል ወይ?” የሚል። አንድ ደረጃ ወደ ኋላ መሄድ ያለብን ይመስለኛል።

ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት ተቀይሯል ወይ? ሁላችንም ጥያቄ አለን። ምክንያቱም እርግጥ ነው አስተዳደሩ ተቀይሯል። ከአቶ መለስ ወደ አቶ ኃይለማርያም፤ ከአቶ ኃይለማርያም ወደ ዶክተር ዐብይ የስልጣን ሽግግር ተደርጓል።

መዘንጋት የሌለብን ግን ሁሉም ኢህአዴጎች መሆናቸውን ነው። በዶ/ር ዐብይ ጊዜ ብዙ ልናስባቸው የማንችላቸው አንዳንድ ለውጦችን እየተመለከትን ነው። እሱ ላይ ጥርጣሬ የለኝም።

‘ከዚያው አንጻር ሚድያው ተቀይሯል ወይ?’ የሚለው ጥያቄ ግን ልንመረምረው የሚገባ ጉዳይ ይመስለኛል። ምክንያቱም፣ ጋዜጠኞቹ እነዚያው ናቸው፣ መሰረተ ልማቱ ያው ነው። አስተሳሰቡ [ማይንድ ሴቱ] ያው ነው። ከሁሉም በላይ የፖለቲካ ባህል የምንለው ያው ነው።

ጋዜጠኛው የኅብረተሰቡ ውጤት ነው። ኅብረተሰቡ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ባህል ተቀይሯል ወይ? ብለን በምናስብበት ሰዓት እንደውም ጥግ የመያዝ ሁኔታ አሁን የባሰ እየጎላ የመጣ ይመስለናል።

ምክንያቱም አንዳንድ ሚድያዎች በተለይ ደግሞ ሶሻል ሚድያው ላይ፤ ጥግ ይዞ ድንጋይ መወራወር ላይ ነው ያለው። ያ ድንጋይ የሚወረወረው ግን ሕዝብ ላይ ነው፤ ወገን ላይ ነው። አገር ላይ ነው። አንዳንዴ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን መሆናችን የረሳን ይመስለኛል።

ምንድነው እያደረገን ያለነው? እየሄድን ያለነው ወዴት ነው? የሚለውን ነገር በአግባቡ ልንመለከተው ይገባል።

ቀደም ሲል እንዳልኩት፤ የመንግሥት አስዳደር ለውጥ የፖለቲካ ባህሉና ባህሪው እስካልቀየረው ድረስ ያ በድሮ ‘ማይንድ ሴት’ ውስጥ ያለው ሚድያ አዲስ ነገር ያመነጫል ብሎ መጠበቅ በጣም ከባድ ነው።

ከሁሉ በላይ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ አስቸጋሪ የሚያደርገው ሁኔታ ሁሉም በየአካባቢው ሶሻል ሚድያ አለው፤ ወይም ደግሞ ጠንካራ የሆነ የራሱ ሚድያ አለው። ስም መጥቀስ አያስፈልግም። ሁላችንም የምናውቃቸው ናቸው። በነገራችን ላይ ሚድያው ዛሬ በአግባቡ ካልተገራ ነገ ዋጋ ያስከፍለናል።

ቢቢሲ፡ የመገናኛ ብዙሃን ሁኔታ በዚህ ከቀጠለ ምን ሊያስከትል ይችላል ይላሉ?

ዘነበ (ዶ/ር)፡ ምሳሌ ለመጥቀስ ኬንያ በ2007/8 (እኤአ) ከምርጫው በኋላ የተከሰተው ግጭት በአብዛኛው እሳት ያቀጣጥሉ የነበሩት፤ ለግጭቱ ከፍተኛ አስተዋጸኦ ሲያደርጉ የነበሩት የሬድዮ ጣብያዎች ናቸው።

ለምሳሌ ሪፍት ቫሊ አካባቢ የነበረው የሬድዮ ጣብያ ትልቁን ሚና ተጫውቷል። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ነባራዊ ሁኔታም መንግሥት አስፈላጊውን ትኩረት ሰጥቶ ሚድያዎቹን ማስተካከል ካልቻለ ነገ ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍሉናል።

ስለዚህ “የመንግሥት ለውጥ ተደርጓል፤ ሃሌ ሉያ ስለዚህ የሚድያ ለውጥ ይኖራል፤ ወደ ተስፋይቱ ምድር እየገሰገስን ነው፤ ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ ሆነዋል” ብለን የምናስብ ከሆነ ራሳችንን እያታለልን ነው።

ከሁሉ በላይ ሶሻል ሚድያው እየፈጠረው ያለው አደጋ ቀላል አይደለም። ሚድያው አንዳንድ ጊዜ የሚሰነዝራቸው ነገሮች ለሶሻል ሚድያ መልስ የመስጠት እስከሚመስል ድረስ ነው። ማይንማር [በርማ] የተፈጠረው ከፍተኛ ዘር ተኮር ጥቃት [ዘር ማጥፋት] በማኅበራዊ ሚድያው ዋና መሪነት የተካሄደ መሆኑን ልናውቅ ይገባል።

እኛ አካባቢስ ሚድያዎቻችን ምን እየሰሩ ነው ያሉት ብሎ መመርመር ያስፈልጋል። በሌሎች ሚድያዎች የማየው ነገር ችግሩ እንዳለ ነው። አፈቀላጤ የመሆን፣ ኃላፊዎችን የመፍራት፣ በአንድ አቅጣጫ የመሄድ ነገር ይታያል።

ከዚያ በዘለለ የሕዝቡ የልቡ ትርታ ማደመጥና ብዙ ሥራ መስራት የሚጠበቅብን ይመስለኛል። ይህንን ስል በፌዴራል ላይ ያሉትንም በክልል ላይ ያሉትንም ይመለከታል።

ቢቢሲ፡ አሁን በተጨባጭ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ካነሱዋቸው ችግሮች ኣንጻር ምን ይደርግ ይላሉ?

ዘነበ (ዶ/ር)፡ ሚድያው ውስጥ ያሉት ሰዎች መሆናቸው አንዘንጋ። በተለያዩ ምክንያቶች ስህተት ይሰራሉ። ‘ኢትዮጵያ ውስጥ እንዴት ብቁ ጋዜጠኛ መፍጠር እንችላለን?’ ብለን ማሰብ አለብን። ሕንድ ለምሳሌ ትልቁ የዲሞክራሲ አገር እየተባለች የምትንቆለጳጰሰው ጥሩ የሚባል ሚድያ ስላላት ነው።

ጋና፣ ኬንያና ደቡብ አፍሪካ እነዚህ ሚድያዎች ከሌላ ጋር ሲነጻጸር ውጤታማ የሆነ ዲሞክራሲ እንዲፈጠር የራሳቸው ሚና ተጫውተዋል። ኢትዮጵያም ውስጥ የምንፈልገው ዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት አያየዝ እንዲመጣ ከፈለግን የሚድያው ሁኔታው መለወጥ አለብን። ማብቃት አለብን።

መጀመሪያ ነገር ሁልጊዜ በተደጋጋሚ ስልጠናዎች መስጠት ይገባል። ለምሳሌ በእርድ ሥራ ላይ የተሰማራ ሰው ቢላውን አስር ግዜ መሞረድ አለበት፤ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ መስራት ስለሚያቆም። ብዙ ነገሮች ስለሚለዋወጡ ሚድያውም እንደዚያ ነው።

ጋዜጠኞች አቅማቸውን የምንገነባ ከሆነ አስፈላጊውን ግብዓት የምናቀርብላቸው ከሆነ የማይቀየሩበት ምክንያት የለም። ይሄ ሁሉ ተደርጎ የማይቀየሩ ካሉ፤ ኬንያ ውስጥ አንድ የሚታወቁበት ነገር አላቸው። ‘ኔሚንግ ኤንድ ሼሚንግ’ [መጥፎ ድርጊትን ማጋለጥ] ይሉታል።

ጋዜጠኞች ሆኑ ፖለቲከኞች ኃላፊነት የጎደለው ሥራ በሚሰሩበት ጊዜ፣ ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት በሚሞክሩበት ጊዜ እንዲሸፈኑና እንዲደበቁ አይፈቅዱላቸውም።

አሜሪካ በምትመጣበት ጊዜ ሲቪክ ማኅበረሰቦች አሉ፤ ዘረኝነትን የሚሰብክ የሚድያ አውታሮችን ‘ኔሚንግ ኤንድ ሼሚንግ’ የሚለው ዘዴ እየተከተሉ ይሰራሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ እንደዚህ ካልተደረገ በስተቀር፤ የእኔን ፍላጎት ስለአንጸባረቀልኝ ብቻ ይሄኛው ሚድያ ትክክል ነው የምል ከሆነ፤ ልክ አይደለም።

ዛሬ ምናልባት ሴቶችን ብቻ ለይቶ የሚያጠቃ ሚድያ ካለ፣ ‘እኔ ወንድ ነኝ፤ አይመለከተኝም’ ብለን የምናልፈው ከሆነ፤ ነገ እኔጋ ሲመጣ ሊያስቆመው የሚችል ኃይል አይኖርም።

ስለዚህ በአንድ ወገናችን ላይ የሚሰራው የሚድያ ጥቃትና ግፍ ሁላችንም ላይ እንደተሰራ አድርገን ልንቆጥረው ይገባል። ስለ እውነትና ስለልጆቻችን ስንል ሚድያውን ደፍረን ማስተካከል ካልቻልን፤ ይህቺን አገር ነገ ላናገኛት እንችላለን።

አሁን እየሄድንበት ያለው አቅጣጫ፤ በጣም መጥፎ አቅጣጫ ነው። ምናልባትም ‘እውን ኢትያጵያውያን ሁላችንም የአንድ አገር ሰዎች ነን’ የሚያስብል ሁኔታ ላይ ነው ያለነው። እየሆነ ያለው፤ ምራቃቸው ከዋጡ ሰዎች የሚጠበቅ አይደለም።